መስከረም 4 ፣ 2013

የሀበሻ አልባሳት ዋጋ በአዲስ አበባ

ቃለመጠይቆችኑሮወቅታዊ ጉዳዮችታሪክንግድፊቸር

ምንም እንኳን በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ የሀበሻ ልብስ መልበስ የተለመደ ባይሆንም አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በበዓላት፣ ወደ ቤተእምነቶች…

የሀበሻ አልባሳት ዋጋ በአዲስ አበባ
ምንም እንኳን በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ የሀበሻ ልብስ መልበስ የተለመደ ባይሆንም አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በበዓላት፣ ወደ ቤተእምነቶች በሚያመሩበት ወቅትና በተለያዩ ሰርግና ዘመድ ጥየቃን በመሳሰሉ ማህበራዊ መሰባሰቦች ላይ የሀበሻ አልባሳትን ሲለብሱ ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁን የሀበሻ ልብስን ወይም በሀበሻ ልብስ አሰራርና ጥልፍ ላይ ተመስርተው በተሰሩ አልባሳት የደመቁ ሰዎችን መመልከት እየተለመደ የመጣ ነገር ነው። ዋጋቸው እንደናረ የሚነገርላቸው የሀበሻ አልባሳት በተለያዩ ዲዛይኖች ለወንዶች፣ ለሴቶችና ለህፃናት በሚሆን መልኩ ሲዘጋጁ ማየት እየተለመደ መጥቷል።አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የተለያዩ በከተማዋ የሚገኙ የሀበሻ አልባሳት መሸጫዎች እንደሚናገሩት ከሆነ አሁን አሁን ለወንዶች በተለያየ ዲዛይን የሚሰሩ የሀበሻ አልባሳት በገበያው መገኘታቸውን ተከትሎ ወንድ ደንበኞች ካለፉት ጊዜያት በተሻለ መልኩ ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም የሀበሻ አልባሳትን በቀዳሚነት የሚጠቀሙት ሴት ደንበኞች እንደሆኑ የሀበሻ አልባሳት መሸጫዎቹ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። በዚህም የተነሳ በእነዚህ  የሀበሻ አልባሳት መሸጫ ሱቆች ውስጥ ለሴት ተጠቃሚዎች የተዘጋጁ “የሀበሻ ቀሚሶችን” መመልከት የተለመደ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሀበሻ ቀሚስ የሚለው ቃል በሴት ተጠቃሚዎች የሚለበሱ የሀበሻ ልብሶችን ለመጥራት የሚውል ቃል ሆኖ እናገኘዋለን።ይሁን እንጂ “ቀሚስ” የሚለው ቃል ለሴቶች ብቻ የሚውል ቃል ነው ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ እጀ ሰፊ የቄስ ቀሚስ፣ የመነኩሴ ልብስ፣ ረዥም ጥብቆ የሸማ የሐር ልብስና የዳባ ልብሶችም ቀሚስ በመባል ይጠራሉ፡፡ የበቅሎ፣ የፈረስ ኮርቻ ልብስ፣ የመሶብ አልባሳትም መጠርያቸው ቀሚስ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተጨማሪም ከአምስት አስርት አመታት በፊት ለኅትመት በቀረበው የአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› በተሰኘው መዝገበ ቃላት ላይ “ቀሚስ” የተሰኘውን ቃል በየፈርጁ ይበይነዋል፡፡ በሐር የተጠለፈውንና የተዘመዘመውን ጥልፍ ቀሚስ በማለት ሲጠራው በጥልፍ የሚሰራውን የሀበሻ ቀሚስ ደግሞ የጥበብ ቀሚስ በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ በበዓል ሰሞን ደግሞ እነዚህ ሀገርኛ ልብሶች ተፈላጊነታቸው እጅግ ትልቅ ነው። እንደምሳሌነት ቀደም ባሉት ጊዜያት የጎጃም ልጃገረዶች የባህላዊ አለባበስ ባህልን ማንሳት ይቻላል። በአካባቢው ዙርያ የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞችና የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የጎጃም ልጃገረዶች በተለይም በበዓላት ሰሞን በተለያዩ የባህል አልባሳትንና የፀጉር አቆራረጦች አጊጠው መመልከት የተለመደ ነው። ጉንፍ በመባል የሚታወቀው የሀበሻ ቀሚስ አይነትን ጨምሮ ሽብሽቦና ጥልፍ ቀሚሶች በበዓላት ሰሞን የጎጃም ልጃገረዶች ምርጫ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በበዓላት ወቅት የጎጃም ልጃገረዶችን ቃሬናና ቁንጮ በተሰኙት የፀጉር አቆራረጦች ደምቀው መመልከት የተለመደ የአካባቢው  ገፅታ ነው።አሁን አሁን ከቀድሞው በተለየ የሀበሻ ልብስ ተጠቃሚ የሆኑ የህበረተሰቡ ክፍሎች ቁጥር መጨመሩን የተለያዩ ሰዎች ይናገራሉ። በከተሞች ውስጥ ከዚህ ቀደም በእናቶችና በተወሰኑ የማህበረሰቡ ክፍሎች ይዘወተሩ የነበሩት የሀበሻ ልብሶች አሁን አሁን በተለያዩ ዲዛይነሮችና ባለሙያዎች ተዘጋጅተው የወጣቱን ቀልብ እየሳቡ እንደሚገኙ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የተለያዩ የሀበሻ ልብስ ሻጮችና ተጠቃሚዎች ተናግረዋል። ባህላዊ ይዘቱን ባልለቀቀ መልኩ የሚሰሩት ልብሶች የሀበሻ ልብስን ከክት ልብስነት በማውጣት ህብረተሰቡ በቀን ተቀን ውሎው ላይ የሚጠቀማቸው አልባሳት እንዱሆኑ በማለት የአልባሳቱ ዲዛይነሮች ባለፉት ጥቂት አመታት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪው አለም ስራቸውን ሲያስተዋውቁ ይስተዋላሉ።  ይህንን ለማድረግ አልባሳቱ ለስራና ለአዘቦት ቀናት ውሎ አመቺ ሆነው እንዲቀርቡ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ይስተዋላሉ። በአዲስ አበባ ከተማ  የሚገኙ የተለያዩ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የሀበሻ አልባሰት ተጠቃሚዎች እንደነገሩን ከሆነ ማህበረሰቡ ወደ ባህል አልባሳት አትኩሮቱ መለስ ማለቱ መልካም ቢሆንም  የዋጋው ነገር ግን በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል። ወ/ሪት ምህረት ደጀኔ  “የባህላዊ ልብስ ዋጋ አንዳንዱ ተመጣጣኝ ቢሆንም አንዳንዱ ደግሞ እጅግ አስገራሚ ሆኖ አግኝቸዋለው። ጥራቱን የጠበቀ የባህል ልብስ ለመሸመት የሚፈልግ ሰው ከ700 ብር አንስቶ በርከት ያለ ገንዘብን ሊጠየቅ ይችላል። አቅም ላለው ግለሰብ ደግሞ ዋጋው እስከመቶ ሺዎች የሚደርስበት አጋጣሚ አለ።”  በማለት ስለ ሀብሻ አልባሳት ዋጋ መናር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በመገናኛ አካባቢ በሚገኘው የሾላ ገበያ ውስጥ የሀበሻ አልባሳትን በመሸጥ የሚተዳደሩት አቶ ዮናስ ጥፍጡ  ስራው በአመት በዓል ወቅቶች ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳለው ገልፀው ስለ ባህል አልባሳት አየተለመዱ መምጣት “የባህል አልባሳት ዲዛይነሮች በተለያዩ  ዘመናዊ እና ባህላዊ ቀመሮች የተሰሩ አልባሳትን ለማህበረሰቡ በማቅረባቸው የባህል አልባሳት በማህበረሰቡ ዘንድ እውቅና እና ተፈላጊነት እንዲጨምር አስተዋፅኦ አድርጓል።” በማለት የገለፁ ሲሆን የዋጋ መናሩን በተመለከተ  አለማችን እያስተናገደች  ባለችው በኮሮና ውረራሽኝ ምክንያት እንቅስቃሴ ቀንሶ ስለነባር በአሁኑ ሰአት የዋጋ ጭማሪ እንዳለ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ሸማቹም ማህበረሰብ  ጥራቱን የጠበቀ እቃን በቀነሰ ዋጋ መሸመት ስለሚፈልግ በነጋዴው ላይ የተውሰነ ጫና እንደሚያሳድርም አክለው ገልፀዋል። አቶ ዮናስን ጨምሮ የተለያዩ በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሀበሻ አልባሳት ዋጋ ለምን እንደዚህ እንደናረ ሲያስረዱ ከሽመና ዋጋ መጨመርና ከውጭ ምንዛሬ እጥረት በተጨማሪ አልባሳቱ የሚዘጋጁበትን ክር ጨምሮ የተለያዩ ግብአቶች ከውጭ መግባቱ እና በጨርቃ ጨርቆቹ መካከል ያለው የጥራት ልዩነት ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ ናቸው። በተጨማሪም ነጋዴዎቹ ተመሳስለው ተሰርተው ለገበያ እየቀረቡ ያሉ የባህል አልባሳት አይነቶች መብዛታቸው ከሽማኔው አልፎ ነጋዴውንም ኪሳራ ላይ እንደጣለ የሚናገሩት ነጋዴዎቹ ተመሳሰለው ገበያላይ ያሉ ከቻይና እና ከሌሎች የውጭ ሀገራት የሚገቡ አልባሳት በወረደ ዋጋ መሸጣቸው ትክክለኞቹ የሀበሻ አልባሳት እንዳይለበሱ ምክንይት እንደሆነ ይናገራሉ።  “በዚህም አማካኝነት የእለት ተእለት ኑሮአቸንን መግፈት ከብዶናል ሰርተን መግባት አልቻልንም ይላሉ።” በማለት ተመሳስለው የሚገቡ ምርቶች እየፈጠሩ ስላለው ጫና ያስረዳሉ። ከነጋዴዎች በተጨማሪ የሀበሻ አልባሳት ዲይነሮች ስራችው ጥራቱን ባልጠበቀ ጨርቅ ተምሳስሎ እየተሰራ በመሆኑ የልፋታቸውን ዋጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ነጋዴዎቹ ይናገራሉ። ።የዘናጭ ዲዛይን ባለቤት የሆኑት አቶ መስፍን በቀለ እንደግለጹት ከሆነ “በኮሮና ወረሽኝ ምክንያት ሁሉም ፕሮግራም እና ዝግጅቶች በመሰረዛቸው ምክንያት ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። ከዚህ በፊት ግን በበዓላት ሰሞን ብዙ ሰዎች እንደፍላጎታቸው ልብሱን ያሰሩ ነበር። አሁን ግን ይህ ቀርቷል” በማለት በኢንዱስትሪው ላይ የሚታየውን ክፍተት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ዋጋውን በተመለከተ አሁን ገበያ ላይ ያለው ዋጋ አልባሳቱን ለመስራት ከሚወጣው ወጪና ጉልበት አንፃር ተመጣጣኝ ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ መስፍን የተናገሩ ሲሆን አክለውም “ሸማቹ ማህበረሰብ ሊረዳ የሚገባው ጨርቆቹ ምንም ጥራታቸውን የጠበቁ ቢሆኑም ለማዘጋጀት ግን ረዝም ያለ ጊዜ እና ሀይለኛ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑን ነው።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።በዘርፉ የተሰማሩ ዲዛይነሮችና ነጋዴዎች እንዲሁም ሸማቾች የኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ ለሚስተዋለው ችግር መፍትሄ እንደሚሆን ይስማማሉ። ለዚህም እምነታቸው እንደክር የመሳሰሉ አልባሳቱን ለመስራት የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎች በአገር ውስጥ ቢመረቱ የሚያመጣውን የዋጋ ቅናሽና የሚያድነውን የውጪ ምንዛሬ እንደሚክንያትነት ያስቀምጣሉ።የሀበሻ አልባሳት ነጋዴዎች በበኩላቸው ተመሳስለው ከውጪ የሚገቡ የባህል ልብሶች ላይ ቁጥጥር መደረግ እንደሚኖርበት ይገልፃሉ። ይህ የአገሪቱን ባህላዊ አለባበስ ታሪካዊና ባህላዊ ዳራ ከመጠበቅም በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከመደገፍም አንፃር ወሳኝ ነው የሚሉት ነጋዴዎቹ፣ የሽመና ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ቦታ ቢሰጠው ማህበረሰቡ ለሙያው ያለው ክብር ይጨምራል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።