ኅዳር 14 ፣ 2014

ኢትዮጵያ ውድ የኢንተርኔት ክፍያ ከሚያስከፍሉ ሐገራት በቀዳሚነት ተቀመጠች

City: Addis Ababaዜና

ውድ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ካለባቸዉ ሀገራት መካከል ለብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በወር 236.09ዩሮ የምታስከፍለዉ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ኢትዮጵያ ውድ የኢንተርኔት ክፍያ ከሚያስከፍሉ ሐገራት በቀዳሚነት ተቀመጠች

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ 'ፕራይስ ኮምፓሪዝን' የተሰኘ የምርምር ተቋም አደረግኩት ባለው አዲስ ጥናት በአለማችን ውድ የኢንተርኔት ክፍያ ከሚጠይቁ 10 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በአንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ጥናቱ በኢትዮጵያ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በወር በ307.84 ዩሮ ገደማ እንደሆነ በመግለጽ ይህ ዋጋ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ከሚገኙት ሀገራት ከፍተኛ ዋጋ የሚጠየቅባት ሀገር ያደርጋታል ብሏል።

ይህም ለወርሃዊ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ሽያጭ በአማካኝ 30.99 ዩሮ ከምትጠይቀዉ ዩናይትድ ኪንግደም ጋር በንፅፅር ሲቀመጥ የኢትዮጵያ ዋጋ ወደ አስር እጥፍ እንደሚጠጋ ተጠቁሟል።

ውድ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ ታሪፍ ካለባቸዉ ሀገራት መካከል ለብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በወር 236.09 ዩሮ የምታስከፍለዉ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

በተያያዘም በዚህ የብሮድባንድ አገልግሎት ውድ የሆነባቸውን ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚውን ተርታ የያዙት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሀገራት ሲሆኑ ኳታር፣ ዚምባብዌ እና ኦማን የሶስተኛ፣ የአራተኛ እና የአምስተኛ ደረጃን ይዘው ተቀምጠዋል።

በተቃራኒው በጥናቱ በአለም ላይ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በርካሽ ዋጋ ከሚገኝባቸው ሀገራት ተርታ መካከል ዩክሬን የአንደኝነት ደረጃን የያዘች ሲሆን ለአገልግሎቱ የሚከፈለዉ ወርሃዊ ክፍያ በአማካኝ 4.42 ፓውንድ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

በዚሁ በዝቅተኛ የዋጋ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሀገራት መካከል ለብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በወር 5.02 ዩሮ የምታወጣው ሩሲያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ሮማኒያ እና ሞልዶቫ ደግሞ ተከታትለው አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ። በዝቅተኛ የዋጋ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ቀዳሚ አምስት ሀገራት መካከል አራቱ ከአውሮፓ ሲሆኑ፣ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ከእስያ ተርታውን በተቀላቀለችው ህንድ ወርሃዊ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋ በአማካኝ  7.48 ፓውንድ መሆኑን የ 'ፕራይስ ኮምፓሪዝን' ጥናት ያሳያል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 4.66 ቢሊዮን የሚጠጉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን ይህም ከአለም ህዝብ 60% የሚሆነውን ይይዛል።

በከፍተኛ የፍጆታ ዝርዝር ላይ ቀዳሚውን ስፍራ ለያዘችው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ብቸኛ የኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅት የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም ታህሳስ ወር በብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉን ማስታወቁ ይታወሳል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለሆኑ መኖሪያ ቤቶች የ69 በመቶ ቅናሽ ሲደረግ በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ደግሞ የ65 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ መደረጉን እና ለቨርችዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ (ቪፒኤን) ተጠቃሚዎችም እንዲሁ የ72 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ኩባንያው ገልጾ ነበር።

ለተደረገው የታሪፍ ማሻሻያም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ባሳወቁበት ወቅት የተደረገው ማሻሻያ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል ማለታቸው አይዘነጋም።

አስተያየት