መስከረም 13 ፣ 2014

ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው አገራት የመደበው ሪፖርት

City: Addis Ababaዜና

መቀመጫዉን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገዉ ፍሪደም ሃዉስ የተሰኘው የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው አገራት ተርታ መድቧታል።

Avatar: Solomon Yimer
ሰለሞን ይመር

Solomon is a content editor at Addis Zeybe. He has worked in print and web journalism for six years.

ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው አገራት የመደበው ሪፖርት
Camera Icon

Photo: itweb.africa

መቀመጫዉን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገዉ ፍሪደም ሃዉስ የተሰኘው የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው አገራት ተርታ መድቧታል።

የኢንተርኔት ነፃነት ዳሰሳው የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የይዘት እቀባ እንዲሁም የተጠቃሚዎች መብት ጥሰት በሚሉት በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ በማተኮር የተከናወነ ሲሆን በእያንዳንዱ ነጥቦች ሥር ባሉ ሌሎች ዝርዝር መለኪያዎች በመመዘን ለሀገራቱ ከ100 ነጥብ ይሰጣል። በዚህም መሰረት ከ70-100 ነጥብ ያመጡ ሀገራት ነፃ፤ ከ40-69 በከፊል ነፃ፤ ከ0-39 ደግሞ የኢንተርኔት ነፃነት የሌለባቸው አገራት በሚል መድቧቸዋል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ 27 ነጥብ በማምጣት የኢንተርኔት ነፃነት ከሌለባቸው ሀገራት ተካታለች። ከ70 ሀገራት 61ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ከሠሀራ በታች ካሉና በጥናቱ ከተካተቱ 11 ሀገራት ደግሞ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከሰኔ 2012 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2013 ዓ.ም. ድረስ የአንድ ዓመት ጊዜ የሚሸፍነው የፍሪደም ሐውስ ሪፖርት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መጠቀም ነፃነት ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መሻሻል የታየበት እንደነበረ ይገልፃል። ይሁን እንጅ በዚሁ ዓመት በተለያዮ ፓለቲካዊ ምክንያቶች ሳቢያ በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የኢንተርኔት መቋረጥና የማህበራዊ ሚዲያ መዘጋት በስፋት የተስተዋለበት እንደነበር ተጠቅሷል።

በሀገሪቱ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በአካባቢው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ በክልሉ የመረጃ ፍሰትን፤ የኢንተርኔት ግንኙነትን እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ ስርጭትን ያስተጓጎለ ነበር ተብሏል።

በሌላ በኩል ዓመቱ በርካታ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮች በስፋት የተሰራጩበት ወቅት እንደነበርም ተጠቅሷል።

የመንግስት ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ከተሞች የስልክና የኢንተርኔት ሽፋን ላይ መሻሻል ማሳየቱን በበጎ ጎኑ ያነሳው ሪፖርቱ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁንም በዘርፉ አለም በዝቅተኛ  ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ መውጣት አለመቻሏን ይጠቅሳል።

ባለፈው አመት በሀገሪቱ የበይነ መረብ ጋዜጠኞችን ለእስር መዳረጋቸውን በማጥቀስ በዚህ ረገድ መንግስት የመረጃ ነፃነትን የሚገድብ ተግባር ፈፅሟል ሲል ሪፖርቱ ይወቅሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎት በየጊዜው ማቋረጡን አሁንም እንደቀጠለ ሪፖርቱ ጠቁሟል። ሆኖም ቀደም ሲል በመላው ሀገሪቱ ይደረግ ከነበረው የኢንተርኔት መዝጋት ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ ጊዜያዊ እና የተወሰኑ ቦታዎችን የሸፈነ ነው ብሏል ሪፓርቱ።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ፍጥነት መለስተኛ መሻሻል ያሳየ መሆኑን የሚገልፀው ይህ ሪፖርት ከአለም አቀፍ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በሀገሪቱ ያለው የኢንተርኔት ፍጥነት እጅግ ደካማ የሚባል እንደሆነና ሰኔ 2013 ዓ.ም. በተደረገ ልኬት መሰረት ኢትዮጵያ ከ158 ሀገራት 106ኛ ደረጃ እንደነበራት ይገልፃል።

ሪፖርቱ እንደሚለው ከሆነ በአለማችን ኢንተርኔት የመጠቀም ነፃነት ለ11ኛ ተከታታይ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ሪፖርቱ በ41 ሀገራት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በበይነ መረብ ላይ በነበራቸው ተግባር የተነሳ ለአካላዊ ጥቃት መዳረጋቸውን የገለፀው ሪፖርቱ ይህም በ11 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው እንደነበረ ጠቅሷል። በተመሳሳይ በጥናቱ  በተካተቱ 70 ሀገራት ውስጥ 56 ግለሰቦች ኢንተርኔትን በመጠቀም ባስተላለፉት መልዕክት ምክንያት ለእስር መዳረጋቸው ተገልጿል።

በጥናቱ ከተካተቱ ሀገራት መካከል አይስላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ካናዳና ኮስታሪካ በፍሪደም ሐውስ የኢንተርኔት ነፃነት መለኪያ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ሀገራት ሲሆኑ ኩባ፣ ማይናማር፣ ቻይና እና ኢራን መጥፎ ውጤት ካስመዘገቡት ውስጥ ተካትተዋል። 

ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት ነፃነት ካለባቸው ሀገራት የተካተተች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆና ስትመዘገብ ግብፅ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ዝቅተኛውን ነጥብ ይዛለች።

አስተያየት