ኅዳር 4 ፣ 2014

ኢሰመኮ ወደ አማራ ክልል በተዛመተው ጦርነት እስከ ነሐሴ ድረስ ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አደረገ

City: Addis Ababaዜና

የኢሰመኮ ሪፖርት እንደሚያሳየው ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ኢሰመኮ ወደ አማራ ክልል በተዛመተው ጦርነት እስከ ነሐሴ ድረስ ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አደረገ
Camera Icon

ፎቶ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ በሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ ከሰኔ 21 እስከ ነሐሴ 22 ቀን 2013 ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን የምርመራ ቡድኑ 128 ቃለመጠይቆችን፣ ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሲቪል እና ከፀጥታ አካላት፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ እንዲሁም ከተራድዖ ድርጅቶች ጋር ማድረጉንና በተጨማሪም 21 የቡድን ውይይቶችን ማድረጉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ምርመራው በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማን፣ ፋርጣ ወረዳን፣ ጉና በጌምድር ወረዳብ፣ ነፋስ መውጫ ከተማን እና የላይ ጋይንት ወረዳን እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ሃራን፣ ወልዲያን፣ መርሳን፣ ሃብሩን፣ ኡርጌሳን እና ቆቦን እንዲሁም በደቡባዊ ትግራይ የአላማጣ ከተሞችን ያካተተ መሆኑን በመግለፅ በሰሜን ወሎ ዞን እና ደቡባዊ ትግራይ የሚገኙ ቦታዎችን በጦርነቱ ምክንያት መድረስ ባለመቻሉ ለምርመራ ሥራው የሚሆነውን መረጃ ያገኘው ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና ሃይቅ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ፣ ወልዲያ እና አካባቢው እንዲሁም ከደቡባዊ ትግራይ መሆኒ፣ ማይጨው እና አላማጣ አካባቢ የመጡ ተፈናቃዮችን በማነጋገር መሆኑን ጠቅሷል።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

በተለይ የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡባቸው ከተሞች በየአካባቢው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን የገዥው ፓርቲ ወይም የመንግስት ደጋፊ ናችሁ፣ መንገድ ወይም ቦታ አላሳያችሁንም፣ የቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን አስጠግታችኋል ወይም ደግፋችኋል፣ ንብረት አምጡ በሚሉ እና ለጊዜው ባልታወቁ ሌሎች ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች ጭምር መግደላቸውን በመጥቀስ ከተሞቹ ውስጥ የሚኖሩ የአዕምሮ ህማንን "ሰላይ ናችሁ" በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው በሕወሓት ታጣቂዎች መገደላቸውንም ሪፖርቱ አትቷል።

በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈፅሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና አካል ጉዳት እንዲደርስ እንዲሁም ንብረት እንዲወድም መሆኑም ተገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‹‹በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክት ነው›› ብለዋል።

ኮሚሽኑ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ላይ ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ በዚሁ ጉዳይ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

አስተያየት