ኅዳር 8 ፣ 2014

የዋጋ መረጋጋት ያመጣል የተባለለት የቅዳሜ እና እሁድ የአስቤዛ ገበያ

City: Addis Ababaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችንግድ

በኢትዮጵያ በከተሞች አካባቢ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ዋጋ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ በመንግስት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህ የቅዳሜ እና እሁድ የአስቤዛ ገበያ እውነት መረጋጋትን አምጥቷል?

Avatar: Henok Terecha
ሄኖክ ተሬቻ

Henok is a reporter at Addis Zeybe. He is passionate about storytelling and content creation.

የዋጋ መረጋጋት ያመጣል የተባለለት የቅዳሜ እና እሁድ የአስቤዛ ገበያ

ዓለምጸሐይ እና ትእግስት ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ የመስተንግዶ ባለሙያዎች ናቸው። የጠዋት ፈረቃ ተረኞች ስለነበሩ እኩለ ቀን ላይ ከስራ ለመውጣት ተቻኩለዋል። ከሳምንት በፊት ጓደኛሞቹ ከሰሞኑ በመዲናዋ ወደተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ግብይት አቅንተው ገበያውን ጎብኝተው የተመለሱ ሲሆን ዛሬ ሸመታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ይገልጻሉ።   

ለግብይት ለመውጣት በሚዘጋጁበት ወቀት በስፍራው የነበረው የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ የቅዳሜና እሁድ ገበያው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸው፤ ዓለምፀሀይ “እንደዚህ የምቻኮለው ጥሩ ሆኖ ስላገኘሁት እና የምፈልገውን አማርጬ መግዛት ስለምችል ነው፤ ደግሞ ከእሁድ ገበያ የምገዛበት ዋጋ ሰፈር ውስጥ ከማገኘው በጣም የተሻለ ሆኖ ነው ያገኘሁት” ስትል ታስረዳለች። ዓለምጸሐይ እንደገለጸችልን በምትኖርበት አካባቢ ከ20 እስከ 24ብር የሚሸጠውን አንድ ኪሎ ሽንኩርት በቅርቡ ስራ ከጀመሩት የቅዳሜና እሁድ ገበያ በ17ብር መግዛቷን ትናገራለች።

ትእግስት በበኩሏ “አዲስ የተጀመረው የገበያ አማራጭ ለእኛ በጣም መልካም ነገሮችን ይዞልን መጥቷል፤ ነገር ግን የቀጣይነቱ ጉዳይ ትንሽ ያሰጋኛል” ትላለች። አገልግሎቱን በዘላቂነት ማቅረብ ከቻሉ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ከተጋነነ ዋጋ ይታደጋቸዋል የምትለው ትእግስት “አስቤዛ ለመሸመት የምናወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ከመቀነስ ባለፈ በሳምንት ሁለት ቀን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድንገበያይ ይረዳናል” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።

አቶ አደም ሀሰን በመገናኛ አካባቢ በሚገኘው የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ተጠቃሚ ሲሆኑ ስለገበያው እንዲህ በማለት ያብራራሉ “በህብረት ስራ ኤጀንሲው እየተዘጋጀ ያለው የምርቶች ገበያ በመልካም ጎኑ ነው የተቀበልኩት ከዋጋ አንጻር ከሱቆች በጣም ትልቅ ልዩነት ነው ያለው” ይላሉ እንደምሳሌ ሲጠቅሱ ባለፈው ሳምንት ሙዝ በኪሎ 22 ብር እንደገዙ፣ ሰፈር ሱቅ ላይ ግን 40 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝና ሸንኩርትም እንዲሁ በትልቅ የዋጋ ልዩነት በሚያሳይ መልኩ ሲሸጥ እንደነበር ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ የግብይት ደይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ደብሪቱ ለአለም በበኩላቸው ይህ ገበያ የማህበረሰቡ ፍላጎት እየጨመረ ስለመጠጣ የገበያው ሁኔታ እስኪረጋጋ አገልግሎቱ በዘላቂነት መስጠታችንን እንቀጥላለን ብለዋል። ሀላፊዉ አክለዉም ለግብይት የሚቀርቡትን ምርቶች ከአምራች፣ ከአርሶአደሮች ፣ ከፋብሪካ/ከአቅራቢዎች  እንዲሁም ከነጋዴዎችም  እያመጣን እናቀርባለን ሲሉ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ነጋዴዎች ምርቶቻችዉን ራሳቸዉ እያቀረቡ እንደሚሸጡም ገልጸዋል።

የምናቀርባቸው ምርቶች የግብርናና የኢንደስትሪ ምርቶችን ሲሆን ከዚህ ባለፈም እሴትም እየጨመርን የምናቀርባቸዉ ምርቶች ይገኛሉ። ለምሳሌ ቀይ፤ ሰርገኛ እና ነጭ ከተሰኙት የጤፍ አይነቶች የተዘጋጀ ዱቄት እያቀረብን እንገኛለን ብለውናል። የግብርና ምርቶቹ አትክልት፤ ፍራፍሬ እና የእህል ምርቶች ሲሆኑ የኢንደስትሪ ምርቶቹ ፓስታ ፤ ማካሮኒ ፤ ዱቄት እና የመሳሰሉትን እንደሆኑ ተገልጿል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ከዋጋም አንጻር ከተለመደው ገበያ በጣም ትልቅ ልዩነት አለው፤ ቀይ ጤፍ 37 ብር፣ ሰርገኛ ጤፍ ከ40 እስከ 41 ብር ነው የሚሸጠው። በተጨማሪ የጤፍ ዱቄት የህብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ ከ5 ኪሎ ጀምሮ የሚቀርብ ሲሆን የተጋገረውን እንጀራ በ8 ብር ዋጋ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

አቶ ኩምሳ የመቂ ባቱ አምራቾች ህብረት ስራ ማህበር ዋና ሀላፊ ሲሆኑ ማህበራቸው በአራት የከተማዋ ቦታዎች ማለትም በሳር ቤት፤ መርካቶ፤ ቃሊቲ እና በጀሞ አካባቢዎች እንደ ቲማቲም፤ ሽንኩርት፤ ጥቅል ጎመን፤ ቃሪያ፤ ደበርጃን፤ ዝኩኒ፤ ፓፓያ እና ሌሎችንም አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ለሸማቹ ያቀርባል።  

“እንደሚታወቀው ቅዳሜና እሁድ ነው ምርቶቻችንን ለገበያ የምናቀርበው ፤ በራሳችን ትራንስፖርት ስለምናመጣው በቅናሽ ዋጋ ነው የምንሸጠው” የሚሉት ኩምሳ ማህበራቸው 152 መሰረታዊ ማህበራት እና ወደ 9ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች አሉን እነዚህን ምርቶች ከነሱ በማሰባሰብ ነው ለህብረተሰቡ ተደራሽ የምናደርገው ይሄም አንዱ የዋጋ መቀነስ ምክንያት ነው በማለት ነው ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ የገለጹልን።

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አያልሰው ወርቅነህ በበኩላቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ ስለሚከናወነው ግብይት ሲገልጹ የሚቀርቡት የተለያዩ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶች እንደሆኑና ቀጣይነቱን በተመለከተ ሲያብራሩ “በህብረተሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተና የከተማዋ የኢኮኖሚ ሁኔታ እስኪሻሻል/አስከሚረጋጋ አቅርቦታችንን እንቀጥላለን በቀጣይም የተለያዩ ምርቶችንም በመጨመር ተደራሽነታችንን ለማሰፋት እንሰራልን” ብለዋል።

ከተለመደው የግብይት አይነት የሚለየው የግብይት ሰንሰሉ ማጠሩ ነው የሚሉት ሀላፊዋ እሴት ጨምረን የህብረተሰቡ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ማቅረባችን ነው በማለት ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የምግብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቀረብ አላማ የሰነቁ የተለያዩ ድርጅቶች ወደ ስራ ገብተዋል ለገበያ ኦሮ-ፍሬሽ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ አክሲዮን ማህበር የተለያዩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶችን ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ከሁለት ሳምንት በፊት ማሳወቁና የከተማዋ ነዋሪዎችን አክሲዮን ማህበሩ አምራቹን ቀጥታ ከሸማቹ ጋር ለማገናኘት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለአዲስ አበባ ገበያ እንደሚያቀርብ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ ኤች በመዲናዋ በተመረጡ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ መሸጥ መጀመሩን ሲያስታውቅ መርሀግብሩን "ቀለብ ከገበሬው" መርሀግብርን አትክልትና ፍራፍሬ በቅናሽ ዋጋ ለማህበረሰቡ ማከፋፈል መጀመሩን አስታውቋል። 

በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም ካለፈው አመት ጀምሮ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ዋጋ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ በመንግስት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገበያውን ለማረጋጋት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የሚደረጉ ጥረቶች የሚበረታቱ እንደሆኑ ቢገልጹም በእንደዚህ አይነት ጥቃቅን ሙከራዎች ብቻ የዋጋ ንረቱን ሙሉ በሙሉ ይፈታዋል ብለው እንደማይጠብቁ ይናገራሉ። የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ጠለቅ ያለ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያና የበለጠ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን የሚፈልግ እንደሆነም ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።

አስተያየት