ሐምሌ 8 ፣ 2013

አሽከርካሪዎችን ያማረረዉ የፓርኪንግ ክፍያ

City: Addis Ababaየአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች የተጋነነ የፓርኪንግ ክፍያዎችን ያለደረሰኝ የሚጠይቁ፤ ደረሰኝ የሚቆርጡትም ቢሆን በደረሰኙ ከተቀመጠዉ ክፍያ በላይ ካልከፈላችሁ ብለዉ በየጎዳናዉ የሚከራከሩ መበራከታቸዉ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን እንዲያሰሙ አድርጓል።

Avatar: Solomon Yimer
ሰለሞን ይመር

Solomon is a content editor at Addis Zeybe. He has worked in print and web journalism for six years.

አሽከርካሪዎችን ያማረረዉ የፓርኪንግ ክፍያ

ለዓመታት የነዋሪዎቿ ቁጥር እያሻቀበ የመጣዉ አዲስ አበባ ከህዝብ ቁጥሯ አንጻር የተፈጠሩ እንደ መንገድ፤ መኖሪያ ቤት፤ መብራት ወ.ዘ.ተ ያሉ የመሰረተ ልማት ፍላጎቶችን ማሳካት ተስኗት ለዓመታት በበርካታ ችግሮች ተጠፍንጋ ዘልቃለች፡፡ ነዋሪዎቿም የባሰ ነገር ሲገጥማቸዉ አቤቱታቸዉን እያሰሙ አንዳንዴም ተስፋ በሚሰጡ ዉሳኔዎቿ ጮቤ እየረገጡ፤ ጆሮ ስትነሳቸዉ ደግሞ እየቆዘሙ እዚህ ደርሰዋል፡፡  

ሰሞኑንም በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በመንገድ ዳር የመኪና ማቆሚያዎች የተጋነነ የፓርኪንግ ክፍያ እየተጠየቅን ነዉ ያሉ አሽከርካሪዎች ቅሬታችን ይሰማልን ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አቤቱታቸዉን ተናግረዉ ነበር፡፡

ያለደረሰኝ የፓርኪንግ ክፍያዎችን የሚጠይቁ፤ ደረሰኝ የሚቆርጡትም ቢሆን በደረሰኙ ከተቀመጠዉ ክፍያ በላይ ካልከፈላችሁ ብለዉ በየጎዳናዉ የሚከራከሩ መበራከታቸዉን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዚህ የተነሳ በወር ለፓርኪንግ የምናወጣዉ ገንዘብ ከነዳጅ ወጪያችን ሊስተካከል ምንም አልቀረዉ ይላሉ፡፡

አንዱአለም ታደሰ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ካዛንችስ አካባቢ ሲሆን በግል ንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ጉዳዮቹን ለማስፈጸም ወደ ተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዘዉትሮ ይሄዳል፡፡ አንዱአለም በተለያዩ የከተማዋ አካቢዎች በሚንቀሳቀስበት ወቅት በመንገድ ዳር ያሉ የመኪና ማቆሚያዎቸን አንደሚጠቀምና በአገልግሎት አሰጣጥና ክፍያ ስርዓቱ ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳስተዋለ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡ 

“በፓርኪንግ ክፍያ በጣም ተማርሬያለሁ ሱቅ ዕቃ ለመግዛት እንኳን አንድ አፍታ ቆመህ ስትመለስ ትኬት ሳይቆርጡ የተጋነነ ገንዘብ ይጠይቁሀል፡፡ ጊዜያዊ ጭቅጭቁን ለማለፍና ቶሎ ወደ ስራየ ለመሄድ እያልኩ ስከፍል ኖሬያለሁ” የሚለዉ አንዷለም አሁን ግን ሁኔታዉ እሱንና መሰል አሽከርካሪዎችን አንዳማረራቸዉ ይናገራል፡፡ “ለፓርኪንግ የማወጣዉን ሳስበዉ በቀን ዉስጥ ከ80 እስከ 100 ብር ይደርሳል ይህም በወር እስከ 3000 ብር ድረስ ማለት ነዉ፡፡ ለነዳጅ ራሱ ከዚህ በላይ አላወጣም፡፡” ይላል አንዱአለም፡፡

ይህንን በተመለከተ ያነጋገርናቸዉ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጂመንት ኤጀንሲ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ብርሀኑ ኩማ ከፓርኪንግ አገልግሎትና ክፍያ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸዉን ገልጸዉ የፓርኪንግ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጁ ማህበራት ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር ዉል ወስደዉ እንዲሰሩ በህግ ይደነግጋል ይሁን እንጂ እስካሁን በከተማዋ ከኤጀንሲው ጋር ውል ገብተው ተቋሙ ባወጣው መመሪያ መሰረት እየሰሩ ያሉ የፓርኪንግ ማህበራት ከ163 እንደማይበልጡ ይጠቅሳሉ፡፡

በቅርቡ የኤጀንሲዉ ባለሙያዎች ባደረጉት ክትትል ያለደረሰኝ የሚሰሩና ከታሪፍ በላይ የሚጠይቁ የፓርኪንግ ማህበራት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም ከኤጀንሲዉ ዉጭ ያሉና በየወረዳዉ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተዉ የሚሰሩ ማህበራትን ለመቆጣጠር ግን እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

ይሁን አንጂ  ሀላፊዉ የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያ ሂደት ላይ ያሉ ችግሮች እንዲባባሱ በማድረግ ረገድ አሽከርካሪዎችንም ከመዉቀስ ወደ ኋላ አላሉም፡፡

“አንዳንድ ተጠቃሚዎች ክፍያ ከፍለዉ መልስ ሳይጠይቁ ይሄዳሉ በዚህ የተነሳ የፓርኪንግ ሰራተኞቹ ያልተገባ ክፍያ እንዲለምዱ አድርጓል፡፡ የሚሉት አቶ ብርሀኑ አሽከርካሪዎች ታሪፉን ጠይቀዉ መክፈልና ደረሰኙ የትራፊክ ማኔጂመንት ያዘጋጀዉ ትክክልኛ ደረሰኝ መሆኑን ማረጋገጥ አንደሚገባቸዉም ጠቁመዋል፡፡

በየመንደሩ በራሳቸዉ ፈቃድ ተሰባስበዉ የፈቀዳቸዉን ክፍያ እየጠየቁ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸዉንም እናዉቃለን ይህን ሁሉ ባንድ ጀምበር ለማስተካከል ግን ተቋሙ ያለዉ አቅም ዉስንነት ይገድበዋል፡፡ በሂደት ለማስተካከል እንደሚሰራ ሀላፊዉ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በስልክ በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከደረሰኝ ውጪ በሚሰሩ ማህበራት የቃልም የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዉ እንደነበር የሚገልጹት ሀላፊዉ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ማስተከከል ስላልቻሉ ውል እንዲቋረጥ እና በምትካቸው ሌላ ማህበር እንዲላክ ለስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ደብዳቤ መላካቸዉን ነግረዉናል፡፡

በከተማዋ የንግድ አንቅስቃሴ በሚበዛባቸዉ አንዳንድ የህንጻ ስር መኪና ማቆሚያዎች በሰዓት ከ50 ብር ጀምሮ ፤ 70 ብር አንዳንዴም እስከ 100 ብር ድረስ የሚጠይቁ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸዉን አንዳሉ አዲስ ዘይቤ ተረድታለች፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምን ይላል ስትል ጠይቃለች፡፡

“እኛ የምንቆጣጠረዉ ሕንጻዉ ለፓርኪንግ የገነባዉን ቦታ ለታሰበለት አላማ ማዋሉን ሲሆን በሚያስከፍለዉ የፓርኪንግ ታሪፈ ላይ ጣልቃ መግባት አንችልም፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጠዉ አካል ያዋጣኛል ያለዉን ታሪፍ ሊያስቀምጥ ይችላል” ብለዋል።

በያዝነው አመት በአዲስ አበባ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችን ለታለመለት ዓላማ ያዋሉ 137 ህንፃዎች የፓርኪንግ ብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት የተሰጣቸው ሲሆን 35 ህንፃዎች ለተሽከርካሪ ማቆሚያ የተዘጋጀውን የህንፃ ስር ፓርኪንግ ቦታ ከታለመለት ዓላማ ውጪ አድርገው በመገኘታቸው እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

አስተያየት