ጳጉሜ 4 ፣ 2013

ኤምባሲዎችን የመዝጋት ሂደትና መዘዙ

City: Bahir Darፖለቲካ

አብዛኛዎቹ የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በመዘጋት ላይ ናቸው። በቻይና እና አሜሪካ በእያንዳንዳቸው ይገኙ የነበሩ፤ ሦስት ጽሕፈት ቤቶችን እዚህ ላይ በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ይህ ውሳኔ ምን ጉዳት አለው? የተጠናበት ውሳኔስ ነው?

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

ኤምባሲዎችን የመዝጋት ሂደትና መዘዙ
Camera Icon

FanaBC

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደመጠ የፓርላማ ንግግራቸው “እኔ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሆን [...] ኢምባሲ እና ዲፕሎማቶችን እቀንስ ነበር [...] ከትርፋቸው ወጫቸው አመዘነብን” ሲሉ ተደመጡ። ለሕዝብ ተወካዮች የውጭ ጉዳይና ዲፕሎማሲን የተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት በዚህ ንግግራቸው “…ዶላር በየቦታው ከምንበትን ለጊዜው ለስድስት ወርና ለዓመትም ቢሆን አሁን ካሉን ኤምባሲዎች ቢያንስ ሠላሳው መዘጋት አለባቸው” የሚለው ለውሳኔ ሐሳብ የቀረበ ንግግራቸው በርካቶችን አስደንግጧል። ኤምባሲዎቹ የሚዘጉት የወቅቱን የጆኦ-ፖለቲክስ ሁኔታ ከግምት በማስገባትና ወጪ ለመቀነስ እንደሆነም ተብራርቷል። ይህንን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚንስተር በዓለም ሐገራት ያሉ አምባሳደሮቹን፣ ዲፕሎማቶቹን እና የቆንስላ ጽ/ቤት ሰራተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ጠርቷል። አዲሱ አመዳደብም ይፋ ሆኗል። አገሪቱ የነበሯትን ወደ 60 የሚጠጉ የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በድጋሚ ተዋቅረው ቁጥራቸው ወደ 29 ቀንሷል። 

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የሕግ ምሁር የሆኑት አቶ ደጀን የማነ በቅርቡ መተግበር የጀመረው ኤምባሲዎችን የመቀነስ ሐሳብ አይዋጥላቸውም። “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ችግር መነሻው ከፖለቲካ አመራሩ ነው” የሚሉት አቶ ደጀን “በሀገር ውስጥ የደከመ ፖለቲከኛ እንዲያርፍ ወይም ገለል እንዲል በአምባሳደርነት አለያም በዲፕሎማትነት በሚሾምበት አሰራር ለውጥ እንዴት ይመጣል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

“በአምባሳደርነት ምደባ ወቅት አቅም፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሚመደብበት ሐገር መግባቢያ ቋንቋ ጋር ያለው ቅርበት መፈተሽ አለበት። የፖለቲካ አለመካከት ብቻ በቂ አይደለም። ምልመላው የፖለቲካ ቡድንን ወይም የፓርቲን ሳይሆን የሐገርን ጥቅም ማስቀደም ይገባዋል። በተለይ በመኖራቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ኤምባሲዎችን ከመዝጋት ይልቅ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መተካት ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ብለዋል። የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ምሁሩ፤ በተጨማሪም ከጊዜ በኋላ ኤምባሲዎቹን የመክፈት ፍላጎት ቢኖር እንደመዝጋቱ ቀላል እንደማይሆን ያስረዳሉ፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈጉ አምባሳደር ከአዲስ ዜይቤ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ “ኢትዮጵያ ረዥም የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን በመገንዘብ በተለይ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መሰረቱ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያውቅ እና የሚረዳ መሪ የላትም” የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። “አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ካልተጠናከሩ ኤምባሲዎችን መቀነስ ወይም መዝጋት ለውጥ አያመጣም” ያሉት አምባሳደሩ “ውሳኔው የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ዝግ ሊያደርገው ይችላል” የሚል ስጋታቸውን አጋርተዋል።

የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አተገባበሩን ባብራራበት መግለጫው “የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶቹ ታጥፈው ወደ ዋናው ኤምባሲ የሚሄዱበትን አሰራር እየተከተልን ነው” ብሏል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ጽሕፈት ቤቶቹ የሚዘጉት ብቁና ትክክለኛ ቁመና ያለው የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን ለማቋቋም በማሰብ ነው። አንዳንዶቹ፤ ነገሮች በወጉ ሳይጠኑ በግምት የተከፈቱና ለመዝጋት የከበዱ፤ ከሚገባውም በላይ የሰው ኃይል የያዙ ናቸው” ብለዋል።

በውሳኔው መሰረት አብዛኛዎቹ የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች በመዘጋት ላይ ናቸው። በቻይና እና አሜሪካ በእያንዳንዳቸው ይገኙ የነበሩ፤ ሦስት ጽሕፈት ቤቶችን እዚህ ላይ በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። የተዘጉት ጽ/ቤቶች ወደ ዋና ከተሞቹ ወደ ቤጂንግ እና ዋሽንግተን የመጨፍለቅ እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ማስተባበሪያ የነበሩትን አሜሪካ የሚገኙ የሎስአንጀለስ እና ሚኒያ ፖሊስ ቆንስላዎች ወደ ዋሽንግተን የመሰብሰብ ስራ ተሰርቷል። አምባዳደር ዲና አሰራሩ በሌሎች ሃገራት የተለመደ እንደሆነ ተናግረዋል።

እርምጃው አምባሳደሮች ወደ ሃገራቸው ተመልሰው፣ በብር እየተከፈላቸው፣ አስፈላጊ ሲሆን እየተመላለሱ በጥቂት ሰራተኞችና ባለሙያዎች የሚሰሩበትን አዲስ አሰራር ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሎለታል።

“የኤምባሲዎች መዘጋት የተጠና አይደለም” የሚሉት አቶ ጋሻው ዓይተነው የውጭ ጉዳይ ተመራማሪ ናቸው። “በኢትዮጵያ ሹመት ፖለቲካዊ ቅርበትን እንጂ ብቃት ላይ የተመሰረተ አይደለም። አምባሳደርነት ተሿሚውን ከፖለቲካ ሥልጣን ማግለያ ሆኖ ነው ያገለገለው። ይህንን ዐቢይ የሥልጣን ዘመንም እንደቀጠውን ችግር ለማስተካከል የተወሰደው መፍትሔ ግን ዋጋ የሚያስከፍል ይመስለኛል። ክትትልና ቁጥጥር እንጂ ቅነሳ የተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫ ይመስለኛል” ብለዋል።

የውጭ ግንኙኘት መምህሩ ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ በበኩላቸው “ኤምባሲዎች ይቀነሱ ማለት የሐገርንና የህዝብን ውክልና የመቀነስ ውሳኔ ነው። በጠቅላይ ሚንስትሩ ወጭው አሳሳቢ ከሆነባቸው ወጭውን የሚተካ ስራ መስጠት እንጂ በአካባቢው የፖለቲካ ሚዛን ላይ የተመሰረተ አሰራር በተለዋዋጭ የፖለቲካ አሰራር ውስጥ እንደ ሀገር ከሚደግፉንም ከማይደግፉንም ጎን ተገኝተን ራሳችንን ማስተዋወቅ፣ ገፅታ መገንባትና ግንኙነቶችን በህዝብ ለህዝብ እና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማጠናከር ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊና ግዴታ ነው” ሲሉ አሰተያየታቸውን ያጠናክራሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተማራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አበበ ዘገየ ሐሳባቸውን ሲሰጡ የውጭ ጉዳይን የስራ ሪፎርም እንደሚደግፉት በመግለጽ ቅነሳውን ግን አጥብቀው ይቃውሙታል። “በምስራቅ አፍሪካ፣ በኬንያ ያለውን አማባሳደር ጋዜጣ ያነባል ብሎ ማሰብ የግንዛቤ ችግር ነው። ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር የምትዋሰነውን ያህል ያሉትን ፖለቲካዊ እና የድንበር ግንኙነቶች በተዛባ መልኩ ሚዛናዊ ባልሆነ መልኩ ስዕል ተሰጥቷቸው እንዳይዘገቡ ምላሽ እየሰጠ፣ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነባው አምባሳደሯ ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ በኢኮኖሚ ካነሱት አገራት ሳይቀር ለመንግሥት ድጋፍ እያመጡ ያሉ በርካታ አብነት ያላቸው ኤምባሲዎች አሉ። በተመሳሳይም የኢትዮጵያዊነትን ስሜት በማያጠፋ መልኩ በባዕድ ሀገር ኢትዮጵያ ቅርባቸው እንድትሆን፣ በራቸውን ከፍተው የሚሰሩ አምባሳደሮችን አሉ።” ያሉት ፕሮፌሰሩ በእጅጉ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ የተሳሳተ ውሳኔ ይመስለኛል ብለዋል።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከአንድ ዓመት በፊት በኬንያ እና በጀርመን ባደረጋቸው ጉብኝቶች በሁለቱ ሀገራት ሰፊ መሬት ያላቸው፣ በሀገሬው አምባሳደሮቻው እጅግ ክብር የሚሰጣቸው ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ መሆኑናቸውን በአካል አረጋግጧል።

ስማቸው በዚህ ዘገባ ላይ እንዳይጠቀስ የጠየቁ አምባሳደር ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ እንደተናገሩት ኤምባሲዎችን ከመቀነስ የአዲስ አበባን ግማሽ መሬት የያዙ ኤምባሲዎችን ፍትሃዊ የመሬት ሪፎርም አካሂደው ቢቀንሷቸው የተሻለ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከ21 በላይ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች የሚገኙት በከፍተኛ የኪራይ ዋጋ በግለሰብ ተከራዮት ቢሮ እና መኖሪያ ቤቶች መሆኑን አክለዋል።

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ አስመላሽ በቀለ በተለያዩ ሀገራት ለተመዱ የኢትዮጵያ ሚስዮን ለዲያስፖራ አባላትና ዲፕሎማቶች በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ በነበራቸው ገለጻ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስለመኗ አንስተዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቀት የዲጅታል ዲፕሎማሲ፣ የዲያስፖራውን ተፅዕኖ በቅርበት መመለስ የሚችል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አደረጃጀት ካልተፈጠረ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት የውሃ፣ የጦር፣ የቱሪዝም፣ የፖለቲካ ርዕዩት፣ አገራዊ ደህንነት እና የውጭ ግንኙነት፣ የሐይማኖት ግንኙነት፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የኢኮኖሚ (የብድር፣ የድጋፍ፣ የእርዳታ) የትምህርት፣ የንግድ፣ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ አመራር እና አሰራር ፈተና ውስጥ ይወድቃል። በተለይም በዚህ ወቅት እየሻከረ በመጣው የአሜሪካ እና አውሮፓ ሃገራት የዲፐሎማሲያዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ ሁሌም ለሁሉም ነገር ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል” ሲሉ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ዶ/ር አልማው ክፍሌ ደግሞ የፈተና መውጫ መንገዷ ከጎረቤት እስከ ሌሎች ዓለማት በጠንካራ ዲፕሎማቶች የታገዘ ሥራን የሚጠይቅ ነው ይላሉ። 

መንግሥት በ2012 ዓ.ም. ካካሄደው ለውጥ ሳቢያ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር የተከለሰውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ የተሻሻለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሰነድ ሲያጠቃልሉ ‹‹የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የበፊቱን ስህተት ያረመ፣ ከውስጥ ዕይታ ወደ ውጭ ዕይታ ያመራ ነው። በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን ግልፅ የፖሊሲ የወረቀት ላይ ግርዶሽ የቀየረ ነው።

በ2013 ዓ.ም. ለተሰናባቹ ምክር ቤት የቀረበው የዲፕሎማሲ ማብራሪያ የተዛነፈው የውጭ ግንኙነት ማሰሪያ መሆኑ የስጋት አመላካች ነው። “በአዲሱ ለውጥ ቀደም ብለው የተቋረጡ ግንኙነቶች ወደቀድሞው ተመልሰዋል፤ ኤምባሲዎች ተከፍተዋል፣ የስልክና የትራንስፖርት መስመሮች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፣ የድንበር አካባቢ የንግድ ልውውጥ አንሰራርቷል፣ የአየር መንገድ በረራ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አዳብሮ፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የመተማመንና አብሮ የመሥራት መንፈስ ተፈጥሯል።”

ቢልም ከውጭ ግንኙነት አንጻር የመጀመርያው ምዕራፍ የለውጡ ስኬት በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ትስስር ከአገራቱ ጋር በመጠራጠር ሳይሆን በወዳጅነት፣ ተቃዋሚዎችን በማስታጠቅ ሳይሆን የጋራ የንግድ መስመሮችን ዘርግቶ አገራቱን በማገናኘት፣ ወደቦችን በጋራ በማልማት፣ ጠንካራ ቀጠና ለመፍጠር ምክክር የተደረገበት ጅማሬ በአዲሱ የመንግሥቱ አቅጣጫ ዝንፈት እንደገጠመው ዐሳይቷል።

በፖለቲካ ሳይንስ እንደሚባለው “ማንኛውም አገር ወዳጅ አገር የመምረጥ መብት አለው፤ ጎረቤት አገር ግን አይመርጥም። ዲፕሎማሲ የወዳጅ ማጥበቂያ የጠላትም ማስጠንቀቂያ ነው”

አስተያየት