መስከረም 7 ፣ 2014

ከሰዓት በኋላ አገልግሎት የማትሰጥ ከተማ

City: Dire Dawaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

“ዕንደሚታየው ብዙ ሰው የሚሰራበት ቢሮ አሁን ባዶ ነው፤ በጊዜ አይገቡም። ብዙ ጊዜም እንደዚህ ነው። አለቆች ሳይቀሩ ከሰዓት ቢሮ አይገቡም። ጫታቸው ላይ ናቸው”...

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከሰዓት በኋላ አገልግሎት የማትሰጥ ከተማ

ወ/ሮ ነኢማ ኢድሪስ ትባላለች። የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ነች። የመንግሥት ተቋማትን በር እንድታንኳኳ የሚያስገድድ ጉዳይ ገጥሟት መመላለስ ከጀመረች 1 ወር እንዳለፋት ትናገራለች። “ጉዳዩን እንደጀመርኩ አካባቢ በየቀኑ ነበር የምመላለሰው። አሁን ግን ቢያንስ በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ቀን እመጣለሁ። ሱቅ የሚጠብቅልኝ ስለሌለ ጉዳዬን የምከታተለው ከሰዓት በኋላ ነው።” የምትለው ወ/ሮ ነኢማ የማይንቀሳቀስ ንብረት ስም ለማዘዋወር ከእርሷ የሚጠበቀውን ሁሉ አጠናቃ የሁለት ሰዎች ፊርማ እንደሚቀራት ለአዲስ ዘይቤ ድሬዳዋ ሪፖርተር ተናግራለች። ጉዳይዋ ይህንን ያህል ጊዜ የፈጀበትን ምክንያት ስታብራራ “ሠራተኞቹ የሥራ ገበታቸው ላይ የሉም። እንደምንም ብዬ በጠዋት ስመጣ ቶሎ አይገቡም። ጠብቄ ጠብቄ ሲሰለቸኝ እሄዳለሁ። ሙሉ ቀን እዚህ እንዳልውል ስራዬ ይበላሽብኛል። ከሰዓት በኋላማ የማይታሰብ ነው። አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ቢኖሩ ነው እንጂ አብዛኛው ሰው ቢሮ አይገባም” ትላለች።

ኦርቢት አካባቢ ያገኘናት ሌላዋ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ይርጋለም ካሳዬ ትባላለች። በዚያው አካባቢ በሚገኝ አንድ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋም ስትመላለስ ጥቂት ሳምንታት ማለፋቸውን ትናገራለች። በሥራ ጸባይዋ ምክንያት ከምሳ ሰዓት በፊት ጉዳይዋን ወደሚመለከተው ተቋም ቢሮ መሄድ እንደማትችል የምትናገረው ይርጋለም ስብሰባ፣ ስልጠና፣ ግምገማ በሚል ምክንያት በተለይ ከሰዓት በኋላ ብዙ ሰራተኞች ቢሮ እንደማይገቡ ትናገራለች።

በአንድ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘው አቶ ማርቆስ እሸቴ የሚሰራበትን ተቋም ስም ለዚህ ዘገባ ሳልጠቀም ሐሳቡን እንድወስድ ጠይቆኛል። “ዕንደምታይው ብዙ ሰው የሚሰራበት ቢሮ አሁን ባዶ ነው። ብዙ ጊዜም እንደዚህ ነው። አለቆች ሳይቀሩ ከሰዓት ቢሮ አይገቡም። ጫታቸው ላይ ናቸው” ሲል በፈገግታ የታጀበ ምላሽ ሰጥቶኛል። ከተቋሙ አጠቃላይ ሰራተኞች ውስጥ 1/4ኛ የሚሆኑት ከምሳ በኋላ የሥራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙም ከአቶ ማርቆስ ገለጻ እና ከሪፖርተራችን ምልከታ ተረድተናል። የሰዓት ቁጥጥር ፊርማ ስለ መኖሩ ጥያቄ ያቀረብንለት አቶ ማርቆስ በሰጠው ምላሽ “የግምገማ ሰሞን ወረቀት ይዘው ይመጣሉ። ቢበዛ ለአንድ ወር ቢፈረምበት ነው እንጂ ከዚያ በኋላ የት እንደሚገባ አይታወቅም” ብሎናል። 

ከምሳ ሰዓት በኋላ ያለውን የተቀጣሪ ሰራተኞችን የሥራ ባህል በተመለከተ የጫት ነጋዴ ለሆነው ለአቶ ሸሪፍ ጥያቄ አቅርበንለታል። “አብዛኛው ሰው ቃሚ ነው። ጫት ደግሞ መቀመጥ ይፈልጋል። ሱቅ ውስጥ፣ ትራንስፖርት ላይ ወይም ሌላ ቢሮ መቀመጥ የማይጠይቅ ስራ ያላቸው ሥራቸውን እያከናወኑ ሊቅሙ ይችላሉ። ለሌሎች ግን አስቸጋሪ ይመስለኛል” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል። ደንበኞቹን በተመለከተ ሲናገርም “ደንበኞቼ እንደዚህ ዐይነት ሰዎች ናቸው። ብዬ መናገር ይከብደኛል” ይላል። “የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ የግልና የመንግሥት ቢሮዎች ላይ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች ሁሉም ዐይነት አሉበት።” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል። አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በመቃሚያ ቤቶች የመቃም ልምድ እንደሌለው ከዚያ ይልቅ ቃሚዎች ሰብሰብ ብለው ቤታቸው ውስጥ እንደሚቅሙ ነግሮናል። “ነገር ግን አልፎ አልፎ እዚህ የሚቅሙ አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመንግሥት ሰራተኞችም ይገኛሉ። እኔ ጋር ቁጭ ብለው እየቃሙ በስልክ ለመስክ ስራ ወጥቼ ነው እያሉ የሚዋሹ ሰዎችም አጋጥመውኛል” ሲል ትዝብቱን አካፍሎናል።

የሕግ ባለሙያና በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ አቤል ልዑልሰገድ ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆነ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንድ ሰራተኛ በቀን ውስጥ ለ8- በሳምንት ለ48 ሰዓታት የመስራት ግዴታ እንዳለበት ይናገራሉ። እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ ይህንን ሕግ ደጋግሞ የጣሰ ተቀጣሪ እንደ ሥራው ሁኔታ እና እንደተጣለበት ኃላፊነት የሚለያይ ሆኖ ሥራውን እስከማጣት የሚያደርስ ቅጣት ሊጠብቀው ይችላል።

በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የማርኬቲንግ መምህር ዶ/ር ሙሉጌታ ግርማ በበኩላቸው “ድሬዳዋ ውስጥ ከፍተኛ የሰው ኃይል ብክነት አለ” ይላሉ። “ሞቃታማው የአየር ንብረት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ወጣቶች የበዛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ጫት ቤት ነው። የሙሉ ጊዜ ተቀጣሪዎች ሳይቀሩ የሥራ ሰዓታቸውን ጫት ላይ ያሳልፋሉ። ከዚያ የተረፈውን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ይወስደዋል። የዕውቀት፣ የሥራ፣ የንባብ፣ ራስን የመለወጥ ጊዜ የሚባል ነገር የለም” ብለዋል።

ዶ/ር ሙሉጌታ ሰራተኞች አብዝተው ከስራ ገበታቸው መቅረታቸው የሚሰሩበትን ተቋም ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ክፉኛ እንደሚጎዳ ገልፀዋል። ሀገራት በዓመት ውስጥ ሊያሳኳቸው የሚፈልጓቸውን እቅዶች ይነድፋሉ። እቅዱ ያላቸውን የሰው ኃይል፣ የተለያዩ ተቋማት ሊሰሯቸው የሚችሉትን ስራዎች፣ እንዲሁም ለሀገር እድገት አስተዋፅኦ ያላቸውን ነገሮች ባጠቃላይ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚነደፍ ነው።

እያንዳንዱ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝና በስራ ገበታ ላይ የሚገኝ ሰራተኛ የስራ ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን ለ8 ሰዓት የማይሰራ ከሆነ እንደሀገር ዝቅተኛ የዕቅድ አፈፃፀም እንዲኖር ያደርገዋል ብለዋል። በዚህ ዘገባ ላይ የከተማውን ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አስተያየት ለማስገባት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አስተያየት