ነሐሴ 27 ፣ 2013

የድሬዳዋ ምድር ባቡር ትዝታዎች

City: Dire Dawaታሪክ

በ1895 ዓ.ም. ታህሳስ 14 ምሽት ሁለት ሰዓት የመጀመሪያው ባቡር ከጅቡቲ በመነሳት በርካታ በረሀማና ሞቃታማ አካባቢዎችን አቋርጦ ድሬደዋ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ ለድሬደዋ መወለድ ምክንያት ሆነ፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋ ምድር ባቡር ትዝታዎች

አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ጋር በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት ሲያቅዱ በሁለቱ ሀገራት መሀል እንደ አማካኝ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ቦታ በአውሮፓውያኖቹ ይጠቆማሉ፡፡ ጥቆማውን ተቀብለው ከጅቡቲ ተነስቶ አዲስ አበባ የሚደርሰው የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ይከናወናል፡፡ በ1895 ዓ.ም. ታህሳስ 14 ምሽት ሁለት ሰዓት የመጀመሪያው ባቡር ከጅቡቲ በመነሳት በርካታ በረሀማና ሞቃታማ አካባቢዎችን አቋርጦ ድሬደዋ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ ለድሬደዋ መወለድ ምክንያት ሆነ፡፡

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ከማኅበራዊ መስተጋብሩ ባሻገር የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባቡር ጣቢያዎች አካባቢዎች እንደ ውሀ፣ ቆሎ፣ አትክልት ያሉ የምግብ ግብአቶችን ከሚሸጡት ጀምሮ አብዛኛው የሀገሪቱ የገቢ ወጪ ንግድ በዚሁ ባቡር ላይ የተመሰረተ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያብራራሉ፡፡ ድሬዳዋን በሚያቋርጠው የባቡር ሃዲድ አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የወጣትነት ዘመናቸውን እንዳሳለፉ የሚናገሩት ሀጂ መሀመድ ጅብሪል አዲሱ የባቡር ዝርጋታ እንደቀድሞው መሀል ከተማዋን የሚያቆራርጥ ስላልሆነ ህዝቡ ድባቡን መረዳት እንዳይችል ሆኗል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

“የአሁኑ የባቡር መስመር መሀል ከተማዋን በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ መልካ ላይ የተቋቋመ ነው›› ሲሉም ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹‹የቀድሞው ባቡር ወደ ከተማዋ ሲገባ በሚያሰማው ከፍ ያለ ድምጽ ስለሚታወቅ ነዋሪው ጓጉቶ ይጠብቅ ነበር ምክኒያቱም ሁሉም ሰው ይሰራል ሁሉም ገቢ ያገኛል” ይላሉ ሀጂ መሀመድ።

“የበርካታ የድሬደዋ ነዋሪዎች የኑሮ መሰረት የነበረው የባቡር ትራንስፖርት አትክልቶች፣ ልባሽ ጨርቆች፣ የታሸጉ ምግቦች፣ ዘይት እና ሌሎች በገቢና በወጪ ንግዱ የሚዘዋወሩ ሸቀጦች ይመላለሱበት ነበር” ያለችን ወ/ሮ አሰፉ ተስፋዬ መተዳደሪያዋ የባቡር ጣቢያ አነስተኛ ንግድ ነበር፡፡

“ባቡር ውስጥ ገብተን ወይም በመስኮት ተቀባብለን ነበር የምንሸጠው፡፡ ውሃ፣ ሙሸበክ፣ ሳምቡሳ፣ ቆሎ የመሳሰሉትን ለመንገደኛው እናቀርባለን፡፡ ከእርሱ በምናገኘው ገቢ ከራሳችን አልፈን ቤተሰባችንን እናስተዳድር ነበር” ብላናለች፡፡ የምትሸጠው ነገር ባላዘጋጀችበት ወቅትም ባዶ እጇን እንደማትገባ የምትናገረው ወ/ሮ አሰፉ ነጋዴዎች ያስመጧቸውን ሸቀጦች ከባቡር አውርደው ወይም ወደሌላ ተሸከርካሪ ጭነው እስከሚያጠናቅቁ ድረስ በመጠበቅ 10 ብር ይከፈላቸው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ አንድ ሰው የአንድ ነጋዴ እቃዎችን ብቻ ስለማይጠብቅ ከበሰሉ ምግቦች ንግዱ ያልተናነሰ ገቢ ይገኝበት እንደነበር አጫውታናለች፡፡ “ሌላው ደግሞ ለባቡር ተሳፋሪዎች አስቀድመን ቦታ እንይዝላቸዋለን፣ ጋሪ ወይም ታክሲ እንጠራላቸዋለን፣ ልባሽ ጨርቆችን ማሳለፍ እንዲችሉ አንዱን በአንዱ ላይ ደራርበን ለብሰን ከፊላንስ ፖሊሶች እናስመልጣቸዋለን ለዚህ አገልግሎታችን እስከ 50 ብር ድረስ ይከፈለናል፡፡ ይህንን ቋሚ ሥራቸው አድርገው የሚተዳደሩበት በርካታ ሰዎች ነበሩ” ስትል የትላንት ኑሮዋን፣ የዛሬ ትዝታዋን አጋርታናለች፡፡

“የባቡር ሃዲዱ በድሬደዋ በኩል ከመዘርጋቱ በፊት በሀረር በኩል እንዲሔድ ታስቦ ነበር፡፡ የመጀመያው ባቡር በእንፋሎት (በስቲም) የሚጓዝ በመሆኑ ውሃ አስፈላጊ ነበር፡፡ ድሬዳዋ የውሃ ክምችቷ ከሀረር የበለጠ መሆኑ፣ የመሬት አቀማመጧ ሜዳማ መሆኑ ለባቡር ዝርጋታው ተመራጭ እንድትሆን አድርጓል፡፡” ያሉን የድሬደዋ አስተዳደር ምድር ባቡር ድርጅት ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃ/ኢየሱስ ደምሰው ይገልፃሉ፡፡

ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ያለው የሀዲድ መስመር ወደ 35 ጣቢያዎች አሉት፡፡ ናዝሬት (አዳማ)፣ ደብረዘይት (ቢሾፍቱ)፣ መተሀራ፣ ድሬደዋ፣ ሚኤሶ፣ ኤረር፣ ሞጆ፣ ሁርሶ፣ ሽንሌ፣ አዲጋላ፣ ደወሌ፣ አይሻ የመሳሰሉትን ከተሞች የፈጠራቸው የባቡር ጣቢዎች መሆናቸው እንደነበር ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ 

በድሬደዋ የሼመንደፈርን መገንባት ተከትሎ ለሰራተኞቹ መኖሪያና ለእንግዶቹ ማረፊያ ይሆን ዘንድ የተሰሩት የቤት ግንባታዎች ለከዚራ መመስረት ምክንያት ሆኗል፡፡ ምድር ባቡር ለሰራተኞቹም የህክምና አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ዘመናዊ የሆነ የፈረንሳይ ሆስፒታልንም አቋቁሟል፡፡ ሆስፒታሉ ከ100 ዓመታትም በኋላ ለነዋሪዎቹና ለሰራተኞቹ ግልጋሎቱን አለማቋረጡን የገለፁት ኃላፊው በአሁኑ ሰዓትም ኩባንያው የተለያዩ ሁኔታዎች ከተመቻቹለት የድሮውን ያህል መስራት እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

የሀገር ባለውለታ የኢኮኖሚ ማገር የብዙ ዜጎች እንጀራ የሆነው ምድር ባቡር በተለይም ከዘጠናዎቹ ጀምሮ የነበረው መዳከም ሲታወስ ይከብዳል ያሉት በምድር ባቡር ውስጥ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ጥላሁን ወንዳፍራሽ የድርጅቱ መውደቅ የከተማዋን መውደቅ አስከትሏል የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ ከ35ቱ ጣቢያዎች መካከል አንዷና ዋናው ‹ወርክ ሾፕ› የሚገኘው ድሬደዋ ላይ ስለነበር ከተማዋ ድርጅቱ ሲያድግ ነበር ያደገችው፡፡ ለዛም ነበር በወቅቱ ከነበሩ ከአስመራና ከአዲስ አበባ እኩል በወቅቱ በወጣው ደረጃ ተቀምጣ ነበር ሲሉ ሀሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡

እውነት ምድር ባቡር አቅም አጥቶ መስራት አቅቶት ነው እንደዚህ ያንቀላፋው ወይስ መስራት እየቻለ እንዳይሰራ ተደርጎ ነው? የሚለው የበርካታ የድሬደዋ ነዋሪ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአሁን ሰዓት በድሬደዋ ምድር ባቡር ግቢ ውስጥ የሚገኙ ማሽነሪዎች ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ቢሆኑም ዛሬም አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ባቡሮቹ ረዥም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ተጉዘው ከተመለሱ በኋላ ጥገናዎች ሲያስፈልጉ ምንም ዓይነት የውጪ እገዛ ሳያስፈልግ የድሬደዋ ምድር ባቡር ውስጥ ሰባት የጥገና ክፍሎች ሲገኙ ከሰባቱ መካከል አንዱ ዲቦ የሚባለው በየቀኑ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች ሁሉ የሚፈተሹበት ዋነኛው ክፍል ነው፡፡ የእግሩ፣ የሞተሩ፣ የኤሌትሪኩ ክፍል ከሰባቱ ክፍሎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ በአጠቃላይ ለባቡር ግልጋሎት የሚውሉትን በሮች፣ ወንበሮች፣ መስኮቶች፣ የማእረግ የጋሪ ወንበሮች አጠቃላይ የፈርኒቸር ውጤቶች የሚሰሩበት ክፍል ሌላኛው ነው ሲሉ የገለፁት በምድር ባቡር ውስጥ ለ35 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ዓለሙ ሽፈራው የገለፁ ሲሆን እነዚህን ክፍሎች በአሁኑም ሰዓት አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡

አስተያየት