ኅዳር 16 ፣ 2014

ጥንቃቄ የጎደለው የበካይ ጋዞች አወጋገድ

City: Hawassaጤናማህበራዊ ጉዳዮች

በሐዋሳ የሚገኙ ፋብሪካዎች በምርት ሂደታቸው ወቅት በጋዝ፣ በጭስ፣ በፈሳሽና በልዩ ልዩ መልክ ተረፈ ምርታቸውን ያስወግዳሉ። በመሰል ድርጊቶች ከፍተኛ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ተቋማት መካከል ‘ኢታብ ሳሙና ፋብሪካ’ ቀዳሚው ነው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ጥንቃቄ የጎደለው የበካይ ጋዞች አወጋገድ

አቶ ፈለቀ ዱካ በሀዋሳ ከተማ ጉዬ ቀበሌ ጡሙራ መንደር ነዋሪ ናቸው። ከፋብሪካዎች የሚወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው ጭስ ለበሽታ እንደዳረጋቸው ይናገራሉ። በአካባቢው ከአራት ዓመታት በላይ ሲኖሩ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን ‘ችግሩ ይቀረፍልኝ’ ሲሉ ለቀበሌ አመልክተዋል። ተደጋጋሚ ውትወታና ማመልከቻቸው ፍሬ እንዳላፈራም በምሬት ይናገራሉ። “የጭሱ ኃይል ሲበረታብን የሕግ አካላት ጋር እንሄዳለን። ለጊዜው ተወት ያደርጉትና ከቆይታ በኋላ ወደ ነበረበት ይመልሱታል” የሚሉት አቶ ፈለቀ ጭሱ እና በካይ ጋዙ በተለይ በሕጻናት እና ነፍሰጡሮች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑን ማወቃቸው ለሰቀቀን እንደዳረጋቸው አልሸሸጉም።

የጡሙራ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማርፎ ገለቶ በአካባቢው ከሃያ ሦስት ዓመታት በላይ ስለመኖራቸው ይናገራሉ። በእነዚህ ዓመታት የፋብሪካዎቹ ጭስ እና በዘፈቀደ የሚለቀቅ ተረፈ ምርት እየጨመረ፣ እየተባባሰ ስለመሆኑ ታዝበዋል። “ፋብሪካዎቹ ለበርካታ ሰዎች የሥራ አድል መፍጠራቸው ይታወቃል። የዚያኑ ያህል ግን በአካባቢው ነዋሪ ላይ የጤና ቀውስ አስከትለዋል” ብለዋል።

መቀመጫቸውን ሀዋሳ ከተማን ያደረጉ በርካታ ፋብሪካዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ለምግብነት የሚውሉ ለስላሳ መጠጦች፣ ወተት እና ዱቄት ማቀነባበሪያዎች ይገኛሉ። ጨርቃጨርቅ እና የንጽሕና መጠበቂያ አምራቾች፣ የእንጨት ፋብሪካዎችም ዋና ዋና ተጠቃሾች ናቸው።

ፋብሪካዎቹ በምርት ሂደታቸው ወቅት በጋዝ፣ በጭስ፣ በፈሳሽና በልዩ ልዩ መልክ ተረፈ ምርታቸውን ያስወግዳሉ። መልክአ ምድሩን እና ከባቢ አየሩን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኝን ሕይወት ያለው ፍጡር የሚጎዱት በካይ ጋዞች እና ኬሚካሎች በጤና የመኖር ነጻነትን የሚጻረሩ ናቸው።

በመሰል ድርጊቶች ከፍተኛ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ተቋማት መካከል ‘ኢታብ ሳሙና ፋብሪካ’ ቀዳሚው ነው። ከ400 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች ያሉት ፋብሪካው እየቀረበበት ያለውን ቅሬታ አስመልክቶ ምላሽ የሰጡን ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ አሰግድ ተስፋዬ ናቸው።

“ፋብሪካችን የሚታወቅባቸውን ደረቅ እና ፈሳሽ ሳሙናዎች ለማምረት በጥሬ እቃነት የከብት ሞራ ይጠቀማል። ሞራው ‘ኮስቲክ ሶዳ’ ከተባለ ኬሚካል ጋር ስለሚዋሀድ አነስተኛ ሽታ ሊኖረው ይችላል” ያሉ ሲሆን። ነዋሪዎች እንዳይረበሹ የሞራ ማቅለጥ ሥራው የሚከናወነው ከምሽት አራት ሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ መሆኑንም ነግረውናል። ይህንን ጊዜያዊ መፍትሔ የወሰዱት ሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እየተሰራ ያለው ሥራ እስከሚጠናቀቅ በዙርያቸው የሚገኘውን ነዋሪ ላለመረበሽ እንደሆነም አብራርተዋል።

በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ከተቋቋሙ ግዙፍ ፋብሪካዎች አንዱ የሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ነው። በ1989 ዓ.ም. የተመሰረተው ፋብሪካው ስራ ካቆመ ከአምስት ዓመት በላይ ሆኖታል። በምርት ሂደት ውስጥ በነበረበት ወቅት ያስወገዳቸው ኬሚካሎች ነዋሪዎችን እንዳይጎዱ ከመኖርያ ርቆ እንዲገነባ እና በስፍራው የነበሩት ጥቂት ነዋሪዎችም ተመጣጣኝ ካሳ ተሰጥቷቸው መኖርያ እንዲቀይሩ መደረጉን የፋብሪካው መዛግብት ያስረዳሉ። ጨርቃጨርቅ ፋብሪካው ሥራ ካቆመ አምስት ዓመታት ቢያልፉም ኬሚካል የቀላቀለው ፍሳሽ አሁንም ይገኛል። ከዓመታት በፊት ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው የሚወጣው ፈሳሽ ትኩረት ያገኘ አይመስልም። የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ፣ የፍሳሹ ጠረን እየጠነከረ ይገኛል።

አቶ ዳሬቶ አበበ ይባላሉ። ላጎን አከባቢ ቤት ገዝተው ልጆች ወልደው መኖር ከጀመሩ አስራ አምስት ዓመታት አስቆጥረዋል። “በስፍራው መኖር የጀመርኩት ፋብሪካው ሥራ ማቆሙን ተከትዬ ነው። በምኖርበት አከባቢ አራት ሰፋፊ ጉድጓዶች አሉ። አሁን ፋብሪካው ምርቱን ቢያቆምም ከዚህ ቀደም ሳይጣራ የለቀቀው ኬሚካል ያለበት ፈሳሽ መጥፎ ጠረን ማስከተል ጀምሯል። በተለይ ከረር ባለ ፀሐይ እና በዝናብ ወቅት ይብሳል። ይደፈናል ተብሎ ሁለት ቢያጆ መኪና የኮንክሪት ድንጋይ ቢቀመጥም ያለ ምንም እንቅስቃሴ ሰባት ወር አልፎታል። እስከ አሁን ምንም የለም” ብለዋል።

አቶ ማኔ የተባሉ ነዋሪ “ሽታው ከባድ ነው። እንኳን ሰው ከብት እንኳን አይዋለድበትም። ችግኞች በኬሚካሉ ምክንያት ይደርቃሉ። አንድ  የጎረቤታችን ልጅ  ከቤተሰብ ተጣልቶ ወደ ጉድጓዱ በመሄድ እራሱን አጥፍቷል” ብለዋል።

በአሁን ሰዓት ፋብሪካው ሥራ ማቆሙን ተከትሎ ከሁለት መቶ በላይ አባወራዎች በአካባቢው ሰፍረዋል። ጠረኑ ከሚያስከትለው ጊዜያዊ እና ዘላቂ የጤና ችግር በተጨማሪ ሕጻናት እና ታዳጊዎቸ ጉድጓዱ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸውን እያጡበት ይገኛል። አገልግሎት ባቋረጠው ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ከጥበቃ ሰራተኞች ውጭ ጉዳዩን ሊያብራራ የሚችል አካል በዚህ ሰዓት የለም።

የሀዋሳ ዮንቨርሲቲ የተማሪዎች ክሊኒክ ጊዜያዊ ኃላፊ ዋሲሁን ዓለሙ ከፋብሪካዎች ከኬሚካል ጋር ተቀላቅለው የሚወጡ ጭሶች እና ፈሳሾች በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ያነሳሉ። “ማንኛውም ኬሚካል ያለበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት ያደርሳል። በተለይ ሳንባን የማፈን፣ ለጉንፋን፣ ለሳይነስ፣ እና ለተለያዩ ተያያዥ የሆኑ አለርጂዎች ያጋልጣል” ብለዋል።

በተመሳሳይ የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንደ ኬሚካሉ ዐይነት እና ባህርይ እንዲሁም ከኬሚካሉ ጋር እንደነበራቸው ቅርበት እና ቆይታ የሚያጋጥሟቸው ችግርም ይለያያል። የሰዎቹ የመከላከል አቅም እና የዶዝ መጠንም እንዲሁ የችግሩን ጥልቀት ከፍ እና ዝቅ የሚያደርጉ ጉዳዮች ስለመሆናቸው ከባለ ሙያዎች ጋር በነበረን ቆይታ ተረድተናል። የመጥፎ ሽታ እና ጎጂ ኬሚካሎች ተጋላጭነት በመተንፈሻ አካላት ላይ ከሚያስከትለው በተጨማሪ በነፍሰጡር እናቶች ተጋላጭነት ምክንያት ሙሉ አካል የሌላቸው ሕጻናት እንዲወለዱ፣ የአእምሮ እድገታቸው ዘገምተኛ እንዲሆን ሊያደርግ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በሕጻናት ላይም የቆዳና የጸጉር አካላት መሳሳት እና መነቃቀል፣ የዐይን ሕመም እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

የብክለት ቁጥጥር አዋጅ 300/2002 ላይ የፋብሪካ ወይም የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት የሆኑ ፈሳሾች ተገቢው የማጣራት ሥራ ሳይከናወንላቸው ወደ ማኅበረሰብ መልቀቅ እንደማይቻል ይደነግጋል። ከተጣራ በኋላም የጥራት ደረጃውን የሚያረጋግጥ ፍተሻ ተደርጎለት ፈዋድ ማግኘት እንደሚገባው ያነሳል።  

የሕግ ባለሙያው አቶ ዳዊት ታምራት “በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ሪፐብክ አዋጅ ቁጥር 1/1987 አንቀጽ 44 ላይ የአከባቢን ደህንነት መብት በሚመለከት የወጣ አዋጅ አለ። ይህም ሁሉም ሰዎች በንጽህና ጤናማ በሆነ አከባቢ የመኖር መብት አላቸው። ኢትዮጵያ እንደ ሰብአዊ መብት ከተቀበለቻቸው አንዱ በንጹህ አካባቢ መኖር የሚለው ይገኝበታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአከባቢ ጥበቃ ሕግን ሁሉም የዓለም ሀገራት እንዲያፀድቁ ጫና እያደረገ ቢገኝም ኢትዮጵያ ግን በሕገመንግስቷ ላይ አስፍራ ትገኛለች” ብሏል።

ተገቢ መሆኑን አንስተዋል። ችግር እንዳለባቸው የሚታወቁ አካባቢዎችን በአካል መጎብኘታቸውን ይናገራሉ። “መጥፎ ጠረን ያስከተለውን የፋብሪካ ተረፈ ምርት ለመድፈን ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በማዘጋጃ ቤት ክልከላ ምክንያት ተቋርጧል። አሁንም ሂደቱ አልተቋረጠም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በተጨማሪም “ነዋሪዎቹ በአካባቢው የሰፈሩት በሕጋዊ መንገድ ባለመሆኑ ካርታ ሰጥቶ ሕጋዊ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው” ብለዋል።

አስተያየት