የካቲት 5 ፣ 2014

የሐዋሳው ዋርካ ሆቴል ያልተነገሩ ታሪኮች

City: Hawassaታሪክ

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይተዳደር የነበረው የእርሻ መሬት በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ሱፍ እና ሌሎች የጥራ ጥሬ ምርቶች ይታፈሱበት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የሐዋሳው ዋርካ ሆቴል ያልተነገሩ ታሪኮች
Camera Icon

ፎቶ፡ እያሱ ዘካሪያስ

ከ50 ዓመት በላይ የኖረው “ዋርካ ሆቴል” በ1963 ዓ.ም. እንደተመሰረተ ይነገርለታል። ሲመሰረት በግለሰብ እጅ እንደነበረ እና መጠሪያውም “ዓለምዓየሁ ሆቴል” እንበር እድሜ ጠገብ የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል። ሐዋሳ ከተማ አሁን ያላትን የከተማነት ቅርጽ ከመያዟ በፊት አብዛኛው የመሬቷ ክፍል የእርሻ መሬት በነበረበት ወቅት ከተማዋን የማዘመን ከፍ ያለ ሚያ ከተጫወቱ ግምባር ቀደሞች መካከል “ዋርካ ሆቴል” ይጠቀሳል።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይተዳደር የነበረው የእርሻ መሬት በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ሱፍ እና ሌሎች የጥራ ጥሬ ምርቶች ይታፈሱበት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ከማረስ እስከ መውቃት ያለውን የእርሻ ሥራ የሚያከናውኑ የጠቅላይ ግዛት ወታደሮች ከትግራይ ውቕሮ፣ ከወሎ ኮረም፣ ከአዲስ አበባ እና ከሐረር ወታደሮች እንዲሰባሰቡ ተደረገ። ወታደሮቹ በተሰጣቸው 200 ካ.ሜ መሬት ላይ ሰፈሩ። ዘመኑ 1952 እና 1953 ዓ.ም. ነበር። ወታደሮቹ የሰረፈሩበት አካባቢ አሁንም ድረስ የመጡበትን አካባቢ ስያሜ እንደያዘ ይገኛል። ኮረም ሰፈር፣ አዲስ አበባ ሰፈር፣ ሐረር ሰፈር፣ ውቅሮ ሰፈር አሁንም የመኖርያ መንደሮቹ መጠሪያ ነው። 

ዋርካው የአካባቢው የመጀመርያ ሰፋሪ ወታደሮች የመጀመርያ ውይይታቸውን ያካሄዱበት እንደሆነ ይታመናል።  በ1970 ዓ.ም. በዋርካ ሆቴል ባልደረባነት የተቀላቀሉት አቶ ጌታቸው አራጋው “ዋርካ ያባቴን ስም ተክቶ መጠርያዬ እስከመሆን ደርሷል” ይላሉ። በተጠቀሰው ዓመት በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ሐዋሳ የተጓዙት ወታደሮች መጽሐፍ ለማንበብ፣ ረጋ ብሎ ለመወያየት፣ የተጣላን ለማስታረቅ የሚጠቀሙበት ዋርካ እንደነበር ስለመስማታቸው ነግረውናል።

የከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤቶች አዋጅ በታወጀበት ወቅት መንግሥት የወረሰው “ዓለማየሁ ሆቴል” ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ተረክቦ ሲያስተዳድረው ቆይቷል። በ1978 ዓ.ም. ስያሜውን ወደ "ዋርካ ሆቴል" ሲቀየር በከተማዋ ከነበሩ ሁለት  ቀደምት ሆቴሎች የተለየ ሆኖ ወጥቷል ። አነዚህ ሆቴሎች አማረ እና ሸበሌ ሆቴል ናቸው።

አቶ ጌታቸው አራጋው ዋርካውን ተንተርሶ የተሰራው ሆቴል አነስተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ። በጊዜ ሂደት እየሰፋ ዋርካውን እንደ ምሰሶ ተጠቅሞ በተሰራው ጎጆ ቤት ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጠ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በአሁን ሰዓት “ዋርካ” የሆቴሉ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው መጠሪያ ለመሆን በቅቷል።

ከ20 ዓመታት በላይ የሆቴሉ ደንበኛ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ግርማ አድማሱ ዋርካ ሆቴል የቀደመ ይዘቱን ጠብቆ እንደሚገኝ አጫውተውናል። “ሆቴሉ የከተማዋ ቅርስ እንደመሆኑ በቱሪዝም ዘርፍ ተገቢው ሥራ አልተሰራበትም” የሚል ሐሳብ የሰነዘሩ ሲሆን “መጠነኛ እድሳት ቢደረግለት የከተማዋ የቱሪስት መስህብ ከሆኑ መዳረሻዎች መካከል ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

ከ50 ዓመታት በፊት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የአምልኮ ስርአትን ጨምሮ የሸንጎ፣ የእርቅና የምክክር ሥርአት ያከናውኑበት እንደነበር መስማታቸውን የሚያስታውሱት አቶ ጌታቸው ሆቴሉ በአሁን ሰዓት ከ50 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉት ነግረውናል።

ዋርካ ሆቴልን በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚመጡበት ጊዜ የሚያቁት 5 ጓደኛሞች ሆቴሉ የዛሬ እና የትላንት ትዝታቸው ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ። “ከ25 ዓመት በፊት ቤተሰቦቻችንን ተከትለን፣ ካልወሰዳችሁን ብለን እያስቸገርን እንመጣ ነበር። አሁን ደግሞ ልጆቻችንን ይዘን እየተዝናናንበት ነው” ብለውናል።

በሆቴሉ ከአርባ ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቶ ጌታቸው “ቦታው የጎብኚዎችን ትኩረት እንዲስብ እንክብካቤ ሊደረግበት ይገባል። የማስተዋወቅ ስራውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

አስተያየት