ግንቦት 10 ፣ 2014

የዓሳ አስጋሪዎች ህይወት በሐዋሳ!

City: Hawassaየአኗኗር ዘይቤኢኮኖሚ

በሃይቁ በቀን ብቻ ሳይሆን በለሊትም በዓሳ ማስገር ስራ የተሰማሩ ሰዎች ሲኖሩ የቀናቸው ከ200-300 ዓሳ፤ ያልቀናቸው ባዶ እጃቸውን የሚመለሱም አሉ

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የዓሳ አስጋሪዎች ህይወት በሐዋሳ!
Camera Icon

ፎቶ፡ Exploring Africa

ንጋት ላይ ብርሀን ወገግ ሲል በሀዋሳ ሃይቅ ዳር የሚስተዋለው ትዕይንት ሁለት አይነት ነው፤ ከሃይቁ ወደዳርቻው ለሊቱን ሲሰሩ ባደሩ ዓሳ አስጋሪዎች የሚገፉ ዓሳ የያዙ ጀልባዎችና በጠዋት ደግሞ ወደሃይቁ ለስራ ጀልባዎቻቸውን፣ መረቦቻቸውንና መንጠቆዎቻቸውን ይዘው የሚሰማሩ አስጋሪዎች ግርግር። ይህ ትዕይንት አካባቢውን ያደምቀዋል። 

ጸሃይ የዘወትር ግብሯን ልትጀምር አድማሱ ላይ ገና ጮራዋን ስትፈነጥቅ ዓሳ አስጋሪዎች የዕለት ጉርሻቸውን ፍለጋ በተንጣለለው የሀዋሳ ሀይቅ ላይ ስራቸውን ይጀምራሉ። የንጋቱን ቅዝቃዜና ነፋስ ተቋቁመው በዓሳ ማስገር ስራቸው ሲተጉ ያረፍዳሉ። 

ምንአሉ አሰግድ እና ዉብሸት ሙሉቀን ወደ አሞራ ገደል ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸዉ ለመምጣት ሰላሳ ደቂቃ ይፈጅባቸዋል። የዓሳ ማስገር ስራቸዉን ለመጀመር ንጋት ላይ በእግር ወደ ሃይቁ ይመጣሉ። “እኔ እና ጓደኛዬ የምንኖረዉ ቤት በጋራ ተከራይተን ሲሆን የተገናኘነዉም በዚሁ ስራ ላይ ነዉ። አብዛኛው የዓሳ ምርት የሚገኘዉ በሌሊት በመሆኑ እኛም የምንመርጠዉ እሱን ነዉ፤ ልክ ከሌሊቱ 11:00 ሰዓት ጀምሮ የሚያስፈልጉንን የማጥመጃ መሳሪያዎች በመያዝ ወደ ስፍራዉ እናቀናለን” ይላል ውብሸት። 

ገና ሳይነጋ ሐዋሳ ሃይቅ የሚደርሱት ምንአሉና ውብሸት ወደ ሃይቁ መረባቸውን ከመወርወራቸው በፊት በርካታ የዓሳ ምርት ሊያገኙ ስለመቻላቸው ቅኝት ያደርጋሉ። “ከሁለት አንዳችን ለስራችን አጋዥ የሆነችዉን ጀልባ በመያዝ ወደ መሃል እንቀዝፋታለን፤ በማስከተል ቀደም ብሎ ከሃይቁ ዳር የተስተካከለዉን መረብ በመወጠር ካለንበት በትይዩ እንወረዉረዋለን፤ በዚህ ጊዜ ወዲያዉ ዓሳዉን ማግኘት ስለሚቸግር በአንድ ቦታ አምስት ደቂቃ ያህል ከታገስን በኋላ ዉስጥ ለዉስጥ ይዘነዉ ወደ ተነሳንበት ስፍራ እንመለሳለን” ይላል ምንአሉ ስራው ግዜና ትዕግስት እንደሚፈልግ በመግለጽ። 

የዓሳ አስጋሪዎቹ የዕለት ዉሎ በዚህ አያበቃም። ወደ ተነሱበት ስፍራ ከደረሱ በኋላ እድል ከእነሱ ጋር መሆን አለመሆኗን የሚያዉቁት መረባቸዉን እስከመጨረሻው ፈትሸዉ ካረጋገጡ በኃላ ነው። እነ ውብሸት ዛሬ በአንድ ዙር ከአምሳ በላይ ዓሳ ይዘዋል። “በፊት ከዚህ በላይ የምንይዝበት አጋጣሚ አለ፣ ሳንይዝም የምንመለስባቸው ቀናትም እንደዛዉ ይኖራሉ” ይላል ምንአሉ። የያዙትን ዓሳ  የሚያስረክቡት በቁርጥ (ፊሌቶ) አልያም በመጥበስ ለበላተኛ ለሚያቀርቡ ነጋዴዎች ነው። የዓሳዎቹ መጠን ትልቅ ከሆነ እስከ 60 ብር፣ አነስተኛ ከሆኑ ደግሞ እስከ 50 ብር ለነጋዴዎች ያስረክባሉ።  

የጠዋቷ ፀሐይ እስከምትጠነክር ድረስ የዓሳ አስጋሪዎቹ ስራ ይቀጥላል። በሁለተኛ ዙር ዓሳ ለመያዝ መረባቸዉን እየወጠሩ የሚገኙት ወጣቶቹ ምንአሉ እና ዉብሸት ስራዉ አድካሚ እና አንዳንድ ግዜም ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ያወሳሉ። “ጀልባዉን መቅዘፍ፣ መረብ መወጠር፣ ወደ ሃይቁ የተወረወረዉን መሰብሰብ፣ እንደገና ዓሳዉን ለመሸጥ ከነጋዴ እና ከበላተኛ ጋር መከራከር አንድ ላይ ተደማምሮ ምነዉ በቀረብኝ የሚያስብልበት ግዜ አለ” ይላል ውብሸት። 

ወጣቶቹ በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው የበለጠ ዓሳ ለመያዝ የቦታ ለዉጥ አድርገዋል። ከአንድ ሰዓት በኋላ በድጋሚ መረባቸውን ወደ ሃይቁ የወረወሩት ምንአሉና ውብሸት ያሰቡት ሳይሆን ቀርቷል። መረባቸው ባዶ ነው። ድካማቸውና ብስጭታቸው ከፊታቸው ላይ እየታየ የእለት ስራቸውን ከአንድ ዙር ባገኙት የዓሳ ምርት ሽያጭ አገባደዋል። 

“የእኛን እጅ የሚጠብቁ ከከተማው ወጣ ብለዉ የሚኖሩ ቤተሰቦች አሉን፤ ራሳችንንም ሆነ እነሱን የምንረዳዉ በዚህ ስራ ነው” በማለት ዓሳ አስጋሪዎቹ ያስረዳሉ። 

የሐዋሳ ሃይቅ በኢትዮጵያ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ የሚገኝ ሲሆን 150 ካሬ ኪ.ሜ. ስፋት እንዲሁም አማካይ ጥልቀቱ ደግሞ 11 ሜትር ነው። 90% የሚሆነውን የሀዋሳ ሃይቅ የዓሳ ምርት ቴላፒያ (ቆሮሶ) የተባለው ዝርያ ነው። በውሃ ግብርና ምርምርና ልማት ጆርናል ላይ በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በሐዋሳ ሃይቅ ላይ የአሳ ምርት ገበያ አቅርቦትን የሚወስኑ ሁኔታዎችን በተመለከተ ባለፈው አመት የቀረበው የምርምር ፅሁፍ እንደሚያመለክተው ሃይቁ በአመት 600 ቶን አሳ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በአብዛኛው ሊገኝ የሚችለው ምርት ወደ 512 ቶን እንደሆነና በተለያዩ ምክንያቶች ሃይቁ ከአቅሙ በታች በማምረት ላይ ይገኛል።  

በምርምሩ እንደተገለፀው ለምርት መቀነሱ እንደ ምክንያት ከተጠቀሰው በሃይቁ አካባቢ ካሉ ተቋማት ወደ ሃይቁ የሚገባው በካይ ፍሳሽ በተጨማሪ በቂ የገበያ መረጃ አለመኖሩ፣ የብድር አገልግሎቶች አለመመቻቸት፣ የዓሳ ማስገር ስልጠናና ልምድ አለመኖር፣ እንዲሁም አብዛኞቹ አስጋሪዎች የግል ጀልባና ማቀዝቀዣ የሌላቸው መሆኑ የዓሳ ምርት አቅርቦትና ገበያው ላይ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች ዋነኞቹ ናቸው።

የሀዋሳ ሃይቅ ከአንድ የጥቁር ውሀ የተፈጥሮ ፍሳሽ ገባር ወንዝ ጋር ብቻ ይዋሃዳል። በስተሰሜን ኦሮምያ እና በስተደቡብ የሲዳማ ክልል ይዋሰኑታል። ዓሳ በማስገር ሃይቁን የገቢ ምንጫቸው ያደረጉት ዓሳ አስጋሪዎች ከእነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ናቸው።  

ጀልባቸውን ይዘው ወደመሃል ሃይቁ ከሚሄዱት አስጋሪዎች በተጨማሪ በሃይቁ ዳር መረባቸውን ጥለው ዓሳ የሚያጠምዱም አሉ። የአስር አመት እድሜ ካላቸው ልጆች ጀምሮ በርካታ ሰዎች የዕለት ጉርሳቸዉን ለማግኘት በመረብ እንዲሁም በቀጭን ዱላ በተሰራ መንጠቆ ዓሳ ይይዛሉ። 

በቀን ብቻ ሳይሆን በለሊትም በዓሳ ማስገር ስራ የሚሰማሩ ሰዎች አሉ። ለሊቱን ዓሳ ሲያሰግሩ ያደሩት የሰበሰቡትን ዓሳ ከሶስት እስከ አራት ሰው በመሆን እንዳይበታተን መረቡን ዳር እና ዳር በመያዝ ወደመሀል የመሰብሰብ ስራ ይሰራሉ። የቀናቸው እስከ ሁለትና ሦስት መቶ ድረስ ዓሳ ይይዛሉ፤ ያልቀናቸው ባዶ እጃቸውን የሚመለሱም አሉ። 

አቶ ዳኢሞ ሉቃስ ሌላው በሀዋሳ ሃይቅ ዳር ያገኘናቸው ዓሳ አስጋሪ ናቸው። አቶ ዳኢሞ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ መተዳደሪያቸዉ ዓሳ በማስገር በሚገኘው የዕለት ገቢ ነዉ ፤ “በዚህ ስራ ልጆችን አስተምሮ የቤት አስቤዛ ገዝቶ ቤተሰብን መምራት ይከብዳል” በማለት አጫውተውናል። “ይህ ስራ ሎተሪ ነዉ ማለት እችላለሁ። ምክንያቱ ደግሞ በሳምንት ዉስጥ ሶስት እና አራት ቀናት ዓሳ ሳንይዝ ወደ ቤታችን የምንመለስበት አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ ነዉ” የሚሉት አቶ ዳኢሞ ዓሳን በማስገር ከአምስት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩና ለእሳቸዉ ይህ ስራ ህይወታቸው እንደሆነ ነግረዉናል።

ዓሳ አስጋሪዎቹ መረቦቻቸውን በዓሳ ከሞሉ በኋላ ስራቸው ያበቃል። ዓሳውን በልተው፣ በፊሌቶ (ጥሬ) መልክም ይሁን በጥብስና ቅቅል ለተጠቃሚው የሚያቀርቡት ከአስጋሪዎቹ  አሳውን የሚረከቡት ነጋዴዎች ናቸው። 

እነዚህ ነጋዴዎች በብዛት አሳዎቹን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡት ሐዋሳ ሃይቅ አጠገብ በሚገኘው በተለምዶ አሞራ ገደል ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነዉ። በቦታው ተገኝቶ የደራዉን ገበያ ለተመለከተ ሰዉ በአንድ የበአል አልያም የገበያ ቀን ብቻ የሚገኝ የዓሳ ምርትና ግብይት ሊመስለው ይችላል፤ ነገር ግን ይህ የአሞራ ገደል የየዕለት ትዕይንት ነው።    

“ገበያዉ አንዳንዴ ይለዋወጣል፤ በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ዓሳ ተወዷል ማለት ይቻላል” ይላል ሌላው የአካባቢው አሳ አስጋሪ ሌጣ ያሬድ። ሌጣ እንደሚለዉ በገበያው የሚታየው የምርት ውድነት ተለዋዋጭ ነው። “ነጋዴዎች ከእኛ የሚረከቡበት ዋጋ አንዳንድ ግዜ ስምንትና አስር ብር፣ እንደ ዓሳው ግዝፈት እና የገበያ ሁኔታ ደግሞ እስከ 30 ብር ይደርሳል” በማለት ሌጣ ያስረዳል።

በአሞራ ገደል የተለመደውና ተወዳጅ የሆነው ጥሬ የዓሣ ቁርጥ (ፊሌቶ) የተባለው ምግብ ነው። ነጋዴዎች የተረከቡትን አሳ አጽድተውና በልተው ለተመጋቢው ከማባያ ዳቦ (ቂጣ) ጋር የሚያቀርቡ ሲሆን እንደ ማባያ ደግሞ ከአጠገቡ አዋዜና ዳጣ አይጠፋም ። 

በገበያው ዓሳ ሲገዛ ያገኘነው አቶ ቢኒያም ታደሰ አዘውትሮ ፊሌቶ (ዓሳ ቁርጥ) እንደሚመገብ አጫውቶናል። “የዓሣ ቁርጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተወዷል አንዱን ሰሃን ሰማኒያ ብር ነበር የምገዛዉ፤ አሁን ግን በመወደዱ ምክንያት ሁለት መቶ ብር ነዉ የገዛሁት” ሲል እየናረ ስለመጣው የዓሳ ዋጋ ያስረዳል።

የሐዋሳ ሃይቅ የተፈጥሮ ሀብት ከዓሳ አስጋሪዎች ህይወት ባሻገር የከተማዋን የተለያዩ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጭምር ሲደጉም ይስተዋላል፤ በተለይ የፍቅር ሃይቅን ተንተርሰዉ የተሰሩ ሆቴሎች እና መዝናኛ ስፍራዎች ዉስጥ ተቀጥረዉ የሚሰሩትን ወጣቶች ለምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በሐዋሳ ሃይቅ ላይ በህጋዊነት ተደራጅተዉ አሳ በማስገር ስራ የተሰማሩ ሰዎች በአጠቃላይ ከ 500 በላይ እንደሆነ ይገመታል። በዚያዉ ልክ ደግሞ በህገወጥ መንገድ አሳ የሚያሰግሩ እና የሚያጠምዱ ሰዎች ቁጥር በየጊዜዉ እየጨመረ መምጣቱ ምርቱ እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል የሐዋሳ ሃይቅ አሳ አስጋሪዎች ማህበር አባል የሆነዉ አቶ ቁምላቸዉ ባይከዳ ይናገራል። “በሃይቁ ላይ ህገወጥ የአሳ አስጋሪዎች ባልተገባ መልኩ አሳዎች እንቁላል ሳይጥሉ ማስገራቸዉ የሃይቁ የአሳ ሀብት እንዲቀንስ እያደረገ ይገኛል። ይህ ደግሞ ጉዳቱ ገና በማደግ ላይ ባሉ ትንንሽ አሳዎችን ከሃይቁ በማስወገድ ተተኪ እንዳይኖር ያደርጋል” ይላል።

በሐዋሳ ሃይቅ ላይ የሚስተዋለውን የምርትና የገበያ ተግዳሮትን በተመለከተ በውሃ ግብርና ምርምርና ልማት ጆርናል የቀረበው ጥናት በማጠቃለያው እንዳስቀመጠው፣ “የዓሳ ማስገርና ምርትን ለተጠቃሚ የማቅረብ ስራዎች በአብዛኛው በወንዶች የተያዘ ሲሆን ሴቶች ወደዚህ ስራ እንዲገቡ ማበረታታት ይመከራል። በህገ ወጥ አስጋሪዎች የሚከናወነው ገና ያልደረሱ ትናንሽ ዓሳዎችን የማጥመድ ተግባር የምርት ትራጄዲ እያስከተለ ነው። ይህም በመሆኑ የዓሳ ምርት የመሰብሰብ ስራንና ገበያውን ለማረጋጋት ጠንካራ የዓሳ አስጋሪዎች የህብረት ስራ ማህበር ማቋቋም ግድ ይላል።”

አስተያየት