መስከረም 21 ፣ 2014

የፖለቲካ ተቃውሞ ኢሬቻ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል?

ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ዘንድሮ የኢሬቻ በአል መስከረም 22 እና 23 ይከበራል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የፖለቲካ ተቃውሞ ኢሬቻ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል?

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የገዳ ስርአት አንዱ ነው፡፡ ኢሬቻ በገዳ ሥርአት ውስጥ ከሚታቀፉ ስርአቶች መካከል ይመደባል፡፡ ከምዝገባው ዕለት አንስቶ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ሆኗል፡፡ በያዝነው ዓመትም የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ መስከረም 22 እና 23 በተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች ይከበራል፡፡ የበዓሉን አክባሪዎች ጨምሮ ሌሎችም ህዝቦች በተለያየ ስሜት እየጠበቁት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን ዝግጅት በማጠናቀቅ በጉጉት የሚጠብቁት እንዳሉ ሁሉ በሰላም ላይጠናቀቅ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ የገቡም አጋጥመዋል፡፡ የኦሮምያ አባገዳዎች ሕብረትና የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ በበኩላቸው አዲስ አበባ ላይ የሚከበረውን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችላቸውን ዝግጅት ስለማጠናቀቃቸው አሳውቀዋል፡፡

“በአምናው የኢሬቻ ክብረ-በዓል ላይ ግርግር እንደነበረ አስታውሳለሁ” የምትለው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ሜክሲኮ አካባቢ ያገኘናት አስተያየት ሰጪ እድሜዋ በ30ዎቹ መጨረሻ ይገመታል፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኝ ካፌ ውስጥ የአስተዳደር ሰራተኛ ናት፡፡ ያለፈው ዓመት ገጠመኗን በማስታወስ በያዝነው ዓመትም ተመሳሳይ ገጠመኝ እንዳትመለከት ትሰጋለች፡፡ “ከስታድየም ጀምሮ ግርግር ነበር፣ ብጥብጥ ፈጣሪዎቹ ከፖሊስ እና ወታደሮች ለመሸሽ ካፌዎች ውስጥ ገብተው ሲደበቁ ትዝ ይለኛል” ብላናለች፡፡ በሥራ ገበታዋ ላይ በነበረችበት በዚያ ወቅት የተመለከተችው አደጋ ባይኖርም ድንጋጤውን በመፍራት በበዓሉ እለት ካፌውን ለመዝጋት መወሰናቸውን አጫውታናለች፡፡ “የሚፈጠረው ስለማይታወቅ አቅራቢያዬ ማውቃቸው አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቅ እንደማይከፍቱ ነው የነገሩኝ” በማለት ሐሳቧን ደምድማለች፡፡

ወጣት በቀለ ኡርጌሳ ኢሬቻ የፖለቲካ መድረክ እየሆነ በመምጣቱ እንደልቡ የማክበር ፍላጎቱ እየተገታ መሄዱን በቅሬታ ይናገራል። “በዓሉ የእርቅ እና የፍቅር ነው ነገር ግን ወጥተን በሰላም እንዳናከብር ደግሞ ያለው የፖለቲካ ጡዘት መወጫ ይሆናል የሚል ስጋት እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙ ወዳጆቼን ሁሉ ወጥተን እንዳናከብር ያደርገናል” ይላል።

ሌላኛው አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው ወጣት ሚኪያስ ቁምላቸው በዩቲዩብ እና ተያያዥ የሚዲያ ስራዎች እንደሚተዳደር ነግሮናል። “አምና የኢሬቻን ድባብ ለመቅረጽ እና ለማስተላለፍ ከባልደረቦቼ ጋር በቦታው ተገኝተን ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ስሜታዊ ወጣቶች ድምጻችንን እናሰማ ብለው በፈጠሩት ግርግር መደናገጥ ውስጥ ገብተን በሩጫ ከአካባቢው ለመራቅ ተገደናል” ሲል ባሳለፍነው ዓመት አዲስ አበባ ላይ የተከበረውን ክብረ በዓል በዩትዩብ ቻናሉ ለማስተላለፍ ባደረገው ጥረት ያጋጠመውን አጫውቶናል፡፡ በወቅቱ እሱን ጨምሮ ሌሎች ባልደረቦቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መለቀቃቸውን አስታውሷል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢሬቻ ፖለቲካዊ አንድምታ ጨምሯል፡፡ ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ያላቸው ተቃውሟቸውን የሚያሰሙበት መድረክ ሆኖም ታይቷል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በ2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ የነበረው የአከባበር ሁኔታ፤ በ2011 ዓ.ም. በለውጡ ሰሞን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሲከበር የሽመልስ አብዲሳ ንግግርና በፖለቲካው ላይ ‘ፕሮሚነንት ፊገር’ የነበረው ጃዋር መሀመድ መገኘትና ጡዘቱ ለዚህ ማሳያ ነው የሚሉት የዚህ ሀሳብ አራማጆች የ2013 ኢሬቻ ከድምጻዊ ሐጫሉ መገደል በኋላ መሆኑ እና የኮቪድ 19 ክልከላ ውጥረቱን ስለማጋጋላቸው ያነሳሉ፡፡

ደራሲና የኢትኖግራፊ ተመራማሪ አፈንዲ ሙተቂ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከአዲስ ዘይቤ የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ “በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ መንግስት የራሱን በቂና አስተማማኝ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም፤ ሕብረተሰቡም በዓሉ በአንዳንድ የህዝብን ሰላም በማይሹ ኃይሎች ድብቅ የተላላኪነት አጀንዳ እንዳይውል መከላከል አለበት” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

ኢሬቻ ሀገራችን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ መሰረትና ሁነኛ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ረጅም ታሪክ ያለው የኦሮሞ ህዝብ የሥልጣን መሸጋገሪያ ስርዓት መላው ህዝብ በሰላም እንዲያከብር፣ የትኛውም ኃይል የህዝቦችን ወግና ባህል ተፃርሮ እንዳይቆም ተደርጎ ሊከበር ይገባል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ “ኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅት ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ፣ ከአዲስ አበባ ከተማም በዓሉን ለማክበር ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በጉዟቸው ወቅትም ሆነ በክብረ-በዓሉ ጊዜ ምንም ዐይነት የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲያከብሩ ከሁሉም የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቂ ዝግጅት ስለተደረገ ሰዎች ሊሰጉ አይገባም” ብለዋል፡፡

አስተያየት