ሰኔ 29 ፣ 2010

ክልሎች እና የበጀት ቀመር

ፖለቲካምጣኔ ሀብት

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ጋምቤላ ክልል ተቀራራቢ ነዋሪ ያላቸው ቢሆንም (ወደ 450ሺህ ገደማ) የፌደራል መንግስት ለሁለቱ የሚመድበው በጀት ግን የተራራቀ…

ክልሎች እና የበጀት ቀመር
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ጋምቤላ ክልል ተቀራራቢ ነዋሪ ያላቸው ቢሆንም (ወደ 450ሺህ ገደማ) የፌደራል መንግስት ለሁለቱ የሚመድበው በጀት ግን የተራራቀ ነው፡፡  ባለፈው አመት ለጋምቤላ የተመደበው በጀት ለድሬዳዋ ከተመደበው በእጥፍ ገደማ ይበልጥ ነበር፡፡ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ ሲነሳ የሚቀርበው ማብራሪያ በልማት ወደኋላ ስለቀሩ የሚል ነው፡፡ በልማት ወደኋላ ቀርተዋል፣ የተማረ የሰው ኃይል የላቸውም፣ የማስፈፀም አቅማቸው አናሳ ነው፤ ግን ከሌሎች በላይ ገንዘብ ይመደብላቸዋል፡፡ይህ ምን ውጤት አስገኘ?ጋምቤላ የከተማ ኑሮን የማያውቁና ተበታትነው የሚኖሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መኖሪያ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ኖሯል፤ በደርግ ጊዜ አካባቢውና የአካባቢው ነዋሪ ከከተሜነት ጋር ተዋወቀ፤ ደገኞች ከአደገኛ አየር ንብረትና የቆላ በሽታዎች ጋር እየታገሉ በወታደራዊው መንግስት አስተባባሪነት ከተማ ተቆረቆረ፡፡ይህ ከበርካታ ክፍለዘመናት በኋላ የታዬ አንድ ለውጥ ነው፡፡ባለፉት 27 አመታት ጋምቤላ በቁጥር ከእሱ ከሚበልጡ የደቡብ የብሔረሰብ ዞኖች በእጥፍ የበለጠ በጀት እየተመደበለት ኖሯል፡፡ ለዚህ መነሻው በልማት ወደኋላ የቀረ የሚል ነው፡፡ በውጤቱ ግን በሚመደብለት በጀት ልክ ከሌሎች በላይ ትራንስፎርም ከማድረግ ይልቅ አሁንም ውራ የሆነ አፈፃፀም እንደፈፀመ አለ፡፡ጋምቤላ ክልል የሚመደብለትን በጀት ለደሞዝ በመጠቀም አንደኛ ነው፡፡ ልማት የለም፣ ፈቅ ያለ የክልሉ ነዋሪዎች ህይወት የለም፣ ደሞዝተኛ ግን በሽበሽ ነው፡፡ 30/40 በመቶ የበረሃ አበል የሚከፈለው፣ በአውሮፕላን ሽር ፍስስ ሲል የሚውል ከየትኛውም የሐገሪቱ ክልል በላይ ፎርጅድ የትምህርት ማስረጃን የሚጠቀም የመንግስት ሰራተኛ፡፡እንደሚታወቀው የመግስታዊ አገልግሎቶች ከገጠር ይልቅ ከተሞች ላይ ይበዛሉ፡፡ ገጠር የሚፈለጉ መንግስታዊ አገልግሎቶች ትምህርት ጤናና ግብርና ናቸው በዋናነት፡፡ ከተሞች ግን በርካታ አገልግሎቶችን ይፈልጋሉ፤ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ ፈቃድ፣ ሊዝ፣ ኮንስትራክሽን፣ ፖሊስ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣. . . ወዘተ፡፡ በዚህም ከተሞች አካባቢ የመንግስት ሰራተኞች ቁጥር ገጠር ከሚበዛባቸው ክልሎች ይልቅ በርከት ያለ ነው፡፡ ለዚህም ሐረሪና አዲስአበባን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል፡፡ በሁለቱ ከተሜ የሚበዛባቸው አካባቢዎች አንድ የመንግስት ሰራተኛ ከጠቅላላው ህዝብ አንጻር አገልግሎት የሚሰጠው ለ34 እና 35 ሰዎች (በቅደም ተከተል) ነው፡፡ የገጠር ነዋሪ በሚበዛባቸው አማራ ትግራይና ኦሮሚያን በመሳሰሉ ክልሎች ግን ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው፡፡ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በአማካይ አገልግሎት የሚሰጠው ህዝብ (ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ለመንግስት ሰራተኛው ሲካፈል) አማራ ላይ 60፣ ትግራይ ላይ 61፣ ደቡብ 74 እንዲሁም ኦሮሚያ 75 ነው፡፡ ከገጠር ነዋሪም አርብቶ አደሩ ቋሚ የመንግስት ሰራተኛ የመፈለግ እድሉ አነስተኛ ስለሆነ አርብቶ አደር ባለባቸው አካባቢዎች ቁጥሩ ከፍ ይላል፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ቁጥሩ ለማሻቀቡ መንስዔው ይሄው ነው፡፡ጋምቤላ ክልል ስንመጣ ግን ሌላ ታሪክ ነው ያለው፡፡ በጋምቤላ አንድ የመንግስት ሰራተኛ አገልግሎት የሚሰጠው ለ20 ሰዎች ነው፡፡ ድሬዳዋና ጋምቤላ ተቀራራቢ ቁጥር ያለው ህዝብ ቢኖራቸውም በመንግስት ሰራተኞች ብዛት ግን ጋምቤላ በሶስት እጥፍ ትበልጣለች፡፡ በዚህ መልኩ የመጣ የተሻለ ቀርቶ እኩል የሆነ አገልግሎትና የህዝብ ተጠቃሚነትም የለም፡፡ ግን “በዜግነት” የሚከፈላቸው ብዙ ዜጎች እንዲፈጠሩ መንስዔ ሆኗል፡፡ተቀራራቢ የህዝብ ቁጥር ያላት ድሬዳዋ በሚፈቀድላት በጀት መሰረታዊ የሚባሉ ልማቶችን በራሷ መገንባት አስቸጋሪ እየሆነባት ከሌሎች ከተሞች አንፃር ዝቅተኛ ልማት የሚታይባት ከተማ ሆናለች፡፡ ባለፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አምስት አመት ለምሳሌ የተሰራው የአስፋልት መንገድ ሁለት ኪሎሜትር እንኳ አይሞላም፡፡ እንደነመቀሌ፣ ሃዋሳና አዳማ 30ና 40 ኪሎሜትር አስፋልት መንገድ ልስራ ብትል ሌሎች ፕሮጄክቶች ብቻ ሳይሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝም ሊታጠፍ ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የፌደራል መንግስት ከድሬዳዋ እስከ መልካ ኢንዱስትሪ መንደር ያለውን አስፋልት እገነባለሁ ብሎ መንገዱ ግን ባለአንድ አካፋይ ብቻ አደርገዋለሁ በማለቱ እና መስመሩ እንኳን የኢንዱስትሪ መንደርና ባቡር ጣቢያ ተጨምሮበት እንዲሁም ፋታየለሽ ስለሆነ አስተዳደሩ ግማሹን ዋጋ እኔ ልሸፍንና ባለሁለት አካፋይ መንገድ ሆኖ ይሰራልን በማለቱ በዚሁ አግባብ እየተሰራ ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ሲባል አምና ከድሬዳዋ የታጠፉ የካፒታል ፕሮጄክቶች በርካታ ነበሩ (በነገራችን ላይ የፌደራል መንግስት ግን በበርካታ መካከለኛና ትናንሽ ከተሞች ሳይቀር ባለሁለት አካፋይ መንገዶችን እንደሚሰራ እያስታወቀ ነው ድሬዳዋ ላይ ይቺን 7 ኪሜ ገደማ መንገድ በባለሁለት አካፋይ ለመስራት ፈቃደኛ ያልሆነው)፡፡መቀሌና ባህር ዳርን የመሰሉ ሌሎች የክልል ከተሞች በክልሎቻቸው በጀት ስለሚመደብላቸው የመሰረተልማት ግንባታ ችግር ሆኖባቸው አያውቅም፤ ድሬዳዋ ግን የፌደራል መንግስቱ የተለዬ ነገር ስለማያደርግላት፣ በነፍስ ወከፍ ከሌሎች ክልሎች ያነሰ በጀት ስለሚመድብላት፣ በልማትም በሚገባው ደረጃ ስለማይደግፋት ለመልማት ያላት አማራጭ በርካታ ፕሮጄክቶችን በማጠፍ አንድ ፕሮጄክት መፈፀም ሆኗል፡፡ከላይ ለንፅፅር ያነሳሁት የመንግስት ሰራተኞች ቁጥር ለጠቅላላ ነዋሪ ያለው ምጣኔም ከከተሜ ክልሎቹ ሃረሪና አዲስ አበባ (34 እና 35) ጋር የሚቀራረብ ሳይሆን የገጠር ነዋሪ ከሚበዛባቸው የአማራና ትግራይ ክክሎች (60 እና 61) ጋር የሚቀራረብ 1 የመንግስት ሰራተኛ ለ52 ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል፤ እነሱም አብዛኞቹ ከሌሎች አቻ ክልሎች ያነሰ ተከፋይ የሆኑ ናቸው፡፡ አሁን ድሬዳዋ በአዲአበባና ሀረር ደረጃ የመንግስት ሰራተኞች ቁጥር ይኑረኝ ብላ ሁለት ሺ ወይ ሶስት ሺ መንግስት ሰራተኞችን ብትቀጥር የካፒታል ፕሮጄክት በጀት ኦና መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡በውጤቱም ብዙ የተባለላት ድሬዳዋ ከተማ፣ ለብዙዎች ህልም የነበረቺው ድሬዳዋ ከተማ፣ በሀገሪቱ ሁለተኛ የነበረቺው ድሬዳዋ ከተማ አሁን ወደ ስድስተኛነት ወርዳለች፡፡በድሬዳዋ መውደቅም ሆነ መነሳት ግን ተጠቃሚውም ሆነ ተጎጂው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ ብቻ አይደለም፤ አጎራባች ክልሎችም ጭምር እንጂ፡፡አሁን በድሬዳዋ የመንግስት ሆስፒታሎች ከ60 በመቶ በላይ አልጋ ይዘው የሚታከሙ ታማሚዎች የአጎራባች ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የሚፈጠሩ የስራ እድል ተጠቃሚዎችን በትውልድ አካባቢ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት የለም እንጂ አብዛኛው የስራ እድል ተጠቃሚም አጎራባች ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሜዳ ሀኖላቸው ምርታቸውን ድሬዳዋ የሚሸጡ፣ እንዲሁም እየተመላለሱ ድሬዳዋ የሚነግዱ የአጎራባች ክልል ነዋሪዎችም የትየለሌ ናቸው፡፡ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችንም ታበረክታለች ድሬዳዋ ለጎረቤቶቿ፡፡ሆኖም ለጎረቤቶቹ ቀርቶ ለራሱ መሆን ላልቻለው ጋምቤላ ክልል ከሚመደበው በግማሽ ያነሰ በጀት ነው የሚመደብላት፡፡የፌደራል መንግስት የህዝቦችን ተጠቃሚነት እና በትስስር ማደግን ከወደደ ከተሞች ላይ ያተኮረ ልማት ይተግብር፡፡ ድሬዳዋ ብታድግ ዙሪዋን ያለ በሚሊዮን የሚቆጠር የአጎራባች ክልል ነዋሪም ጭምር ነው ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡ የአዲስአበባ የኢኮኖሚ ማዕከልነት ጠቀሜታው ለአዲስአበባ ብቻ ሳይሆን ለመላ ሃገሪቱ መሆኑን ማንም አያጣውም፤ ጎጃምና ድሬዳዋ ጤፍ የሚገበያዩት አዲስአበባ ነው፡፡ መቀሌና አርባምንጭ ሙዝ የሚገበያዩትም አዲስአበባ ነው፡፡ አዲስአበባ ለአዲስአበባ ብቻ አይደለችም፡፡ ኢኮኖሚክስና ሶሲዮሎጂን ሳይሆን ደረቅ ፖለቲካን ብቻ እያኘኩ የበጀት ቀመር ማዘጋጀት በቃ ሊባል ይገባል፡፡ ይሄ ነገር በዋናነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስራ መሆንም የለበትም፡፡

አስተያየት