ታህሣሥ 17 ፣ 2015

የሰዋሰው ሙዚቃ መተግበሪያ መጀመርን ተከትሎ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው ዓለም አቀፉ ስፖቲፋይ

ኪነ-ጥበብ

የሰዋሰው የሙዚቃ መተግበሪያ ኃላፊዎች የስፖቲፋይ እቅዶችን እንደሚያውቁ እና ኢትዮጵያ በስፖቲፋይ የዓመት የገበያ እቅድ ውስጥ እንኳን እንዳልነበረች ይናገራሉ

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የሰዋሰው ሙዚቃ መተግበሪያ መጀመርን ተከትሎ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው ዓለም አቀፉ ስፖቲፋይ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሜድያ

ሰዋሰው የተሰኘ ሀገር በቀል የሙዚቃ መተግበሪያ ስራውን ከጀመረ በጥቂት ወራት ውስጥ ግዙፉ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያ የሆነው ስፖቲፋይ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ታውቋል። 

የሰዋስው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቱ ነጋሽ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ስፖቲፋይ በኢትዮጵያ አገልግሎት የጀመረው ሰዋሰው በተጠናከረ እና በተቀናጀ መልኩ ስራ መጀመሩ ገፋፍቶት ነው” ብሏል። 

“የስፖቲፋይን እቅድ እናውቀዋለን፤ ኢትዮጵያ አይደለም በሳምንት በዓመት እቅዳቸው ውስጥም አልነበረችም” ያለው ኃላፊው “በ38 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አገልግሎቱን ለማስጀመር በያዙት የረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥም ኢትዮጵያ እንዳልተካተተች” ገልፀዋል።

በስፖቲፋይ መተግበሪያ የሚተላለፉ የሙዚቃ ስራዎች እና ሌሎች የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት በኢትዮጵያ የሚገኙ ተጠቃሚዎች ቪፒኤን (VPN) የመጠቀም ግዴታ የነበረባቸው ቢሆንም አሁን በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖቲፋይ ተጠቃሚዎች የራሳቸው መለያ በነፃ መክፈት እንዲችሉ አድርጓል። 

ዓለም አቀፉ የሙዚቃ መተግበሪያ በሀገሪቱ ስራዉን ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ስብስቦች እንዳሉት በሚነገርለት ስፖቲፋይ ላይ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች እና ድምፃውያንም አልበምና ሌሎች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በተለይም በውጭ ለሚገኙ አድማጮቻቸው ተደራሽ ለማድረግ ይጠቀሙበት ነበር። 

በዚህ ዓመት ስራውን የጀመረው ሰዋሰው የሙዚቃ መተግበሪያ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)ን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች በአገልግሎቱ ማስመዝገብ እና ስራዎቻቸውም በመተግበሪያው እንዲጫኑ እያደረገ ይገኛል። 

በቅርቡ ከተለቀቀው የተወዳጁ የሄኖክ አበበ 'ይቅርታ' የተሰኘ አልበምን ጨምሮ በርካታ የሙዚቃ አልበሞችም በሰዋሰው የሙዚቃ መተግበሪያ አማካኝነት ለአድማጮች መድረስ ችለዋል። በተጨማሪም መተግበሪያው ካሙዙ ካሳ፣ አቤል ጳውሎስ፣ ታደለ ገመቹ፣ ራሄል ጌጡ እና ብሌን ዮሴፍን የመሳሰሉ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞችን እና ድምፃዊያንን አስፈርሟል። 

ቴዲ አፍሮ በ2009 ዓ.ም. በተለቀቀው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው የመጨረሻ አልበሙ የቢልቦርድ ቁጥር አንድ ሽያጭ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ የሚታውስ ሲሆን ሰዋሰው ቴዲ አፍሮን ማስፈረሙ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል።

“ስፖቲፋይ በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት መጀመሩ የኢትዮጵያ አድማጮች የሙዚቃ የጣዕም ልኬታቸውን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ቢሆንም በየቀኑ ወደ 81 ሺህ የሚጠጉ የሙዚቃ ስራዎች በመተግበሪያው ስለሚጫኑ የኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ስራዎች ማግኘት ያለባቸውን እያታ ላያገኙ ይችላሉ” ሲል የሰዋስው መልቲሚዲያ የሙዚቃ ዘርፍ ኃላፊው አቶ ሀብቱ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል። 

በኢትዮጵያ የሚገኙ ተጠቃሚዎች አሁን የራሳቸው ነፃ መለያ በስፖቲፋይ መተግበሪያ መክፈትና አገልግሎቱን በክፍያ እና ያለክፍያ በሆኑ አማራጮች መጠቀም ይችላሉ። ይሁን እንጂ በነጻ መለያ የሚጠቀሙ ተመዝጋቢዎች ሙዚቃ እና ሌሎች የድምፅ አገልግሎቶችን በኢንተርኔት (ኦንላይን) ብቻ ማዳመጥ የሚችሉ ሲሆን በአንድ ሰዓት ውስጥም ስድስት ጊዜ ብቻ ማሳለፍ ወይም ማዘለል እንዲችሉ ይፈቅዳል።

በተጨማሪም የስፖቲፋይ የፕሪምየም ወይም የክፍያ አገልግሎት በ535 ብር ገደማ ወይም በ9.99 ዶላር ማግኘት የሚቻል ሲሆን በፔይፓል አልያም ደግሞ በማስተር ካርድ በመክፈል ተጠቃሚዎች የሚወዷቸውን ዘፈኖች ማዳመጥ፣ አዳዲስ ሙዚቃዎችን እና ፖድካስቶችን ባልተገደበ መልኩ መጠቀም እንዲሁም ያለገደብ ማሳለፍ እና ከመተግበሪያው በማውረድ ከኢንተርኔት ውጭ (ኦፍላይን) እንዲያዳምጡ ያስችላል። 

የሙዚቃ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን በስፖቲፋይ በሚለቁበት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን እይታ በአማካኝ ከ3 ሺህ 300 እስከ 3 ሺህ 500 ዶላር እንደሚያገኙ ይገመታል። 

ሰዋሰው በበኩሉ ተጠቃሚዎች የራሳቸው መለያ በመፍጠር የተለያዩ ሙዚቃዎች እና የድምፅ ይዘት ያላቸው ሌሎች ስራዎችን እንዲያገኙ እያደርገ የሚገኝ የሙዚቃ መተግበሪያ ሲሆን ተጠቃሚዎች ያለገደብ እንዲጠቀሙ እና የሚፈልጉትን ሙዚቃ አውርደው እንዲያዳምጡ የመመዝገቢያ ጥቅል መግዛት ይጠበቅባቸዋል። 

የአንድ ሳምንት የመመዝገቢያ ጥቅል ዋጋ 25 ብር ሲሆን በአንድ ወር 90 ብር እንዲሁም ደግሞ በአመት 918 ብር በመክፈል የጥቅል አገልግሎቶቹን መጠቀም ይቻላል። 

ከነበረው የገበያ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ሰዋሰው ለሙዚቀኞች የተሻለ ጥቅማጥቅሞች እና ክፍያዎችን ይዞ እንደመጣ የሚናገሩት አቶ ሀብቱ “አዳዲስ ሙዚቀኞች ከሰዋሰው ጋር ውል ሲፈራረሙ ከ1 ሚሊዮን ብር ጀምሮ የሮያሊቲ ክፍያ እንደሚከፈላቸው” ገልፀዋል። በተጨማሪም ኃላፊው “ተጨማሪ ክፍያዎች የባለሙያዎቹ ሙዚቃዎች ባገኙት እያታ ብዛት እንደሚፈፀሙም” አስረድተዋል። 

የስፖቲፋይ መተግበሪያ በዓለም ዙሪያ 195 ሚሊዮን የተመዘገቡ ደንበኞችን ጨምሮ 456 ሚሊዮን ጠቅላላ ተጠቃሚዎች አሉት። በአፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ በአልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቱኒዚያ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ስፖቲፋይ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ እና ሴኔጋልን ጨምሮ አገልግሎቱን ወደ 38 የአፍሪካ ሀገራት ያስፋፋ ቢሆንም ኢትዮጵያ በዝርዝሩ አልተካተተችም ነበር።

በ2011 ዓ.ም. አውታር የተሰኘ የዲጅታል ሙዚቃ ማስተላለፍያ መተግበሪያ በታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ እና ሀይሌ ሩትስ ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ መተግበሪያም ሆነ ተቋም አልነበረም። 

አውታር የበርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች ስራዎች እና አልበሞች ለተመልካቾች ያደረሰ ቢሆንም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተጠበቀው ደረጃ ውጤታማ አንዳልሆነ ይገልፃሉ። ስሙ አንዳይጠቀስ የፈለገ የሙዚቃ አቀናባሪ የአውታር መተግበሪያን በተመለከተ ለአዲስ ዘይቤ በሰጠው ሐሳብ “አውታር ያልተሳካበት ምክንያት ከአስፈረማቸው ሙዚቀኞች ጋር በጥቅማ ጥቅም እና በሌሎች ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ባለመስማማታቸው ነው” ይላል። 

የሙዚቃ ባለሙያው ሲጨምርም “የበርካታ ዝነኛ የሙዚቃ ባለሙያዎች ስራዎች በአውታር መተግበሪያ በኩል ለአድማጭ ደርሰዋል። ቢሆንም ሙዚቀኞቹ ስለሚያገኟቸው ጥቅማጥቅሞች እና ክፍያዎች ቅሬታ ስላላቸው መድረኩ በሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ ካሉ ተዋናዮች ሊኖረው የሚገባውን እምነት ማስቀጠል አልቻለም” ሲል ተናግሯል።

አስተያየት