መጋቢት 16 ፣ 2014

ነባር ተጫዋቾችን ባለማሳተፍ ቅሬታ የቀረበበት የአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ

City: Adamaስፖርት

ባሳለፍነው ዓመት በደጋፊዎች እና በቡድኑ ማኔጅመንት መካከል አለመግባባት ካስነሱ ጉዳዮች መሃከል የውጤት ቀውስ ዋነኛው ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ነባር ተጫዋቾችን ባለማሳተፍ ቅሬታ የቀረበበት የአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

ሦስት አስርት ዓመታት የደፈነው የአዳማ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ የዚህ ዓመት የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ተካፋይ ነው። ቡድኑ የትግራይ ክልል ቡድኖች በጦርነቱ ምክንያት በጨዋታው መሳተፍ አለመቻላቸው የተሳትፎ አጋጣሚውን ፈጥሮለታል። በስሩ አራት ቡድኖችን የያዘው የአዳማ እግር ኳስ ክለብ፡ ዋና ቡድን፣ ከሀያ ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች እና በሴቶች ቡድን ይጫወታል። ዓመታዊ በጀቱ 120 ሚሊዮን ብር የሆነው ቡድኑ ገቢውን ከ70 በመቶ በላይ ገቢውን የከተማ አስተዳደሩ ይሸፍናል።

ባሳለፍነው ዓመት በደጋፊዎች እና በቡድኑ ማኔጅመንት መካከል አለመግባባት ካስነሱ ጉዳዮች መሃከል የውጤት ቀውስ ዋነኛው ነው። የእግርኳስ ክለቡ ማኔጅመንት በዘንድሮው ውድድር የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ወደ መካከለኛ ደረጃ አድጓል ቢልም ደጋፊዎች ዛሬም ደስተኛ አይደሉም። 

ማሚላ በሚል ስያሜ የተዋወቀን ወጣት የአዳማ ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ነው። "ከውጤትም በላይ ቡድኑን እዚህ ያደረሱት ተጫዋቾች በየመንደሩ ስታያቸው ያናድዳል" ይላል። የቀድሞ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ በአሰልጣኝነትም ሆነ በአስተዳደር ውስጥ በብዛት አለመኖራቸው ይቆጨዋል። “አዳማ ከነማ ጠንካራ ታዳጊ ቡድኖች አለት" የሚለው ማሚላ “በዋናው ቡድን ውስጥ ቢገቡም የመጫወት እድል አለማግኘታቸው ያሳዝናል” ብሎናል።

ቶማስ ተስፋዬ የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋች ነው። ከ1987 እስከ 1995 መጨረሻ በአዳማ ከነማ ከታዳጊ ቡድን ተጫውቷል። የነበረበት ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መድረስ ችሎ እንደነበር ያስታውሳል።

“የክለቡ አመራር ለቀድሞ ተጫዋቾች ምንም ቦታ የለውም። በቃል ደረጃ የእምቢታ መልስ ባይሰጡም ተግባር ላይ አያውሉትም” ብሎናል። ክለቡን ለማገዝ ያቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ የእሺታ መልስ ቢያገኝም በቀጠሮ አግኝቶ በዝርዝር የሚያወራው አመራር በማጣቱ እንዳልተሳካ ይናገራል። በቁጭት “ክለቡ ተጎድቷል። የባለቤትነት ስሜት አጥቷል” ይላል።

የአሁኑ አልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምክትል አሰልጣኝ ይታገስ እንዳለ የቀድሞ የአዳማ ከነማ ተጫዋች መሆኑን የሚያነሳው ቶማስ “ጥሩ ጅምር ነው” ብሎታል። በዘንድሮው ዓመት 5 ታዳጊዎች ዋና ቡድኑን ተቀላቅለው ማየቱም ደስታ ከፈጠሩበት የክለቡ እንቅስቃሴዎች መካከል ጠቅሷቸዋል።

"ክለቡ ባለፈው ዓመት በ4 የተለያየ ትጥቅ ነበር የተጫወተው። ዘንድሮም እንዲሁ በ3 ትጥቁ የተለያየ ነው" የሚለው ማሙሽ ክለቡ እስካሁን ስፖንሰር አለማግኘቱ የደጋፉ ማኅበሩንም ሆነ የማኔጅመንቱን ድክመት ለማሳያነት አቅርቦታል።

"ክለቡ ከደጋፊዎቹ ያገኘው ምንም ዓይነት ጥቅም የለም" የሚሉት አቶ አንበሴ መገርሳ አሁን ማኅበሩ በአዲስ መልክ እየተደራጀ እንደሆነ፣ ከዩናትድ ቢቨሬጅ ጋር የ5 ዓመት ውል በመፈራረማቸው የትጥቅ ተመሳሳይነት ችግር እንደተቀረፈ አንስተዋል። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ 15 ሺህ ማልያ ርክክብ እንደሚኖር በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።

"ቡድናችን የምፈልገውን ውጤት ባያመጣም አሁንም ከቡድኑ ጋር ነን። ለቡድናችን ከፍተኛ ፍቅር አለኝ" ያለን አዳማ ከተማ ተወልዶ ያደገው ቲቶ ሰሎሞን ነው። የፋይናንስ ችግሩ ለመውረድ እንዳበቃውና ከዚህ በኋላ የሚመልሰው እንደማይኖር ተስፋ አድርጓል።

የደሞዝ ክፍያ አለመከናወን እና መዘግየት ለብዙ ተጫዋቾች እንዲለቁም ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ብዙዎችም የወራት ደሞዝ ሳይከፈላቸው መልቀቃቸውን ይናገራል።

ከማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ አዳማ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም በሚገኘው የማኅበሩ ጽ/ቤት የአባላት ምዝገባ ተጀምሯል። ከዚህ ቀደም የነበረ ደጋፊ ማኅበር አልነበረም ያልናቸው ደጋፊዎች እንደሚከተለው ብለውናል።

የመጀመሪያ የደጋፊ ማኅበር ምስረታ የተከናወነው በ2002 ዓ.ም. እንደሆነ የሚናገሩት ደጋፊዎች ይኼ ማኅበር ተቀዛቅዞ በ2011 ዓ.ም. እንደ አዲስ መቋቋሙን ይናገራሉ።

በአሁን ወቅት ያለው የደጋፊ ማኅበር በህዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደተመረጠ የማኅበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ሰለሞን ይናገራል። "በከተማዋ በተደጋጋሚ በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፣ በሀገር ደረጃ የነበሩ ሁኔታዎች እና የኮቪድ ወረርሽኝ ጉዳይ እስካለፈው የውድድር ዓመት ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. በተገቢው ሁኔታ እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው ይናገራል።

ስራውን ሲጀምሩ ቀድሞ ከነበረው የማኅበሩ አመራር ጋር የሥራ እና የማህተም ርክክብ አለማከናወናቸው ሌላኛው ፈተና እንደነበረ እና የነበረው አለመግባባት በውይይት እንደተፈታ አብራርቷል።

አንደ ምስክር ገለጻ "የክለቡ ደጋፊ ተቋሟዊ አሰራርን ለምዶ፣ ቡድኑ ህዝባዊ መሠረት ኖሮት እንዲቀጥል እየሰራን ነው" ማኅበሩ ከናታኒም ኢንተርቴይንመንት ጋር የሁለት ዓመት ውል ተፈራርሞ መላው ኦሮሚያ 200 ሺህ ደጋፊ ለማፍራት መታቀዱን ይናገራል።

ከናታኒም ኢንተርቴይመንት ጋር በገቡት ውል መሠረት እስከ 200 ለሚደርሱ ደጋፊዎች የስራ እድል ለመፍጠር እንደታሰበ የነገረን ምስክር ሰለሞን በአሁን ወቅት የቢሮ እድሳቱን እና የ10 ሰራተኞች ቅጥር መፈጸሙን ነግሮናል።

ደጋፊ ማኅበሩ ሰራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት ውል ተቀባዩ ናታኒም ኢንተርቴይንመንት እንደተከናወነ ነግሮናል። በዚህም በአሁን ወቅት 10 ሰራተኞች ከሰኞ ጀምሮ ከ2 ሺህ 5 መቶ  እስከ 3 ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ስራ መጀመራቸውን ነግሮናል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የደሞዝ ክፍያ ባለመፈጸሙ በከፍተኛ ደረጃ ስሙ ሲነሳ የነበረው አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ወደታችኛው ዲቪዚዮን ከመውረድ የተረፈው በትግራይ ክለቦች መቅረት ምክንያት ነበር።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ እንደሚሉት ከሆነ ከዚህ ቀደም የነበረው የከተማ አስተዳደር ክለቡን ለመደገፍ የነበረው ተነሳሽነት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ማሻሻያ እያደረጉ እንደሆነ ይናገራሉ።

በተጨማሪም የክለቡን አቅም አጠናክሮ ወጪዎችን ለመቀነስ በታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየሰራን ነው" የሚሉት አቶ አንበሴ መገርሳ ታዳጊዎች እድል አልተሰጣቸውም በሚለው አይስማሙም። ይልቅም በአሁን ወቅት በዋናው ቡድን ውስጥ ከታዳጊ የመጡ 10 ተጫዋቾች መኖራቸውን ይናገራሉ።

"ለአራቱም ቡድኖች ዓመታዊ በጀታችን 120 ሚሊዮን ብር ነው። 70 በመቶ ወጪውን የሚሸፍነው ከተማ አስተዳደሩ ነው" የሚሉት አቶ አንበሴ መገርሳ ከስፖንሰርሺፕ፣ ከፕሪሚየር ሊጉ የሚገኝ ገቢ ደግሞ ቀሪዎቹ እንደሚሸፈኑ ይናገራሉ።

"በ2012 ዓ.ም. እንደ አዲስ የተቋቋመው ደጋፊ ማኅበር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ነገር ግን ሚጠበቅበትን ያክል ክለቡን እየደገፈ አይደለም" የሚሉት አቶ አንበሴ ለወደፊት ማኅበሩን በማጠናከር ቡድኑ የሚጠቀምበትን መንገድ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ይናገራሉ።

አስተያየት