ጥቅምት 6 ፣ 2015

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተውኛል ያላቸውን ባለሀብቶች ሊከስ ነው

City: Adamaዜና

ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንቨስትመንት አዋጅ መሰረት እገዳው የተጣለባቸው ባለሀብቶች በቀጣይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደሚታይ ታውቋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተውኛል ያላቸውን ባለሀብቶች ሊከስ ነው
Camera Icon

ፎቶ፡ አዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን

በአዳማ ከተማ ከ1987ዓ.ም ጀምሮ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደስራ ባልገቡ እንዲሁም ከተሰጣቸው ፍቃድ ውጪ ሲሰሩ የቆዩ ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዳማ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቱራ ግዛው በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

እነዚህ እርምጃ የተወሰደባቸው ፕሮጀክቶች በአማካኝ በ15 ዓመት በተሰላ ስሌት ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበትን 700 ሚሊዮን ብር በማስቀረት መንግስትን ማክሰራቸውን የገለጹት ኃላፊው በተጨማሪም እንፈጥራለን ብለው ቃል የገቡትን 1599 የስራ እድል ባለመፍጠራቸው በዚህም በደሞዝ መልክ ይከፍሉት የነበረውን 800 ሚሊዮን ብር ባለመክፈላቸው በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 208/2012 ዓ/ም መሠረት አንድ ፕሮጀክት በ6 ወራት ውስጥ ወደ ግንባታ መግባት እንዲሁም በ3 ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ መሠማራት እንዳለበት ይገልጻል ያሉት አቶ ቱራ እገዳው የተጣለባቸው ባለሀብቶች በቀጣይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንደሚታይ ገልጸዋል።

በተጠቀሰው ጊዜ በአጠቃላይ ለ1198 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ፍቃድ መሰጠቱንና ከእነዚህ ውስጥ 820ዎቹ በስራ ላይ ሲገኙ 200 ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል። 

የኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ጽ/ቤት ኃላፊው ማብራሪያ መሰረት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው መሬት አጥረው ያስቀመጡ 54 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ፍቃዳቸው ተነጥቆ  80 ሔክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ ሲደረግ ከተመላሽ መሬቶች ውስጥም በቀጣይነት ለሚያለሙ ባለሀብቶች በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን መሬት መጋዘን ሰርተውበወር እስከ 3 ሚሊዮን ብር ያከራዩ የነበሩ 48 ፕሮጀክቶችን በመለየት 24ቱ ማሻሻያ እንዲያደርጉ እንዲሁም 24ቱ ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።

አስተያየት