ኅዳር 11 ፣ 2014

ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ የተቋቋመዉ የፈጠራ ማበልጸጊያ ተቋም

City: Addis Ababaየፈጠራ ዐውድማህበራዊ ጉዳዮችንግድ

የስራ ፈጠራ ባለቤቶች እና በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶችም በአለም አቀፍ የዲዛይኒንግ ክህሎትን እንዲያገኙ የሚያግዘ ተቋም

Avatar: Henok Terecha
ሄኖክ ተሬቻ

Henok is a reporter at Addis Zeybe. He is passionate about storytelling and content creation.

ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ የተቋቋመዉ የፈጠራ ማበልጸጊያ ተቋም
Camera Icon

Photo: ethiopia.un.org

ሜሮን ተስፋዬ በሀያዎቹ መጨረሻ የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ወጣት የስራ ፈጠራ ባለሙያ ናት። 'መሆን ክራፍት' የተሰኘ ጀማሪ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ መስራች እና ባለቤት የሆነችው ሜሮን 'ክርኤቲቭ ሀብ ኢትዮጵያ' የተሰኘው የፈጠራ ማበልጸጊያ ባዘጋጀው ዲጂታል ስቱዲዮ ውስጥ በቅርቡ ለገበያ ሊውል በዝግጅት ላይ ያለውን የእጅ ቦርሳ ንድፍ ለመጨረስ ስትጣደፍ ትታያለች።

ከዛሬ አምስት ወራት በፊት ተቋሙ ያወጣውን የአባልነትና የስልጠና እድል በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀ ማስታውቂያ አይታ እንደተመዘገበች የምትናገረው ሜሮን ከዚህ ቀደም የፈጠራ ሀሳቦቿን ወደ ተግባር ለማውረድ በርካታ መሰናከሎች ወደ ኋላ ይጎትቷት እንደነበር ታስታውሳለች። 

“ስለብራንዲንግ ምንም አይት እውቅት አልነበርኝም የቆዳ ምርቶች ላይ እንዴት ብራንድ ማተም እንዳለብኝ አላውቀም ነበር። ሌላው የቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትም ላይ ሰፊ ክፍተት ነበረብኝ” በማለት ትገልጻለች።

ወደ ማዕከሉ ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስልጠናዎችን አግኝቼበታለሁ ከዚህም ባሻገር ላቦራቶሪውን በመጠቀም ከስራዬ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የተለየዩ ዲዛይኖችን እያወጣሁ ያልነበረውን ተጨማሪ ነገር እንዳካትትበትም አግዞኛል የምትለው ሜሮን የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እና ከፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከአመት በፊት በተከፈተው ክርኤቲቭ ሀብ የተሰኘ የፈጠራ ማበልጸጊያ ተቋም ውሰጥ የስልጠና እድል ካገኙ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ውስጥ አንዷ ናት።

የፈጠራ ማበልጸጊያ ማዕከሉ የጋራ የመስሪያ ቦታን ያመቻቸልን ሲሆን በጋራ በመሆን የምናመርተውን እዚሁ ለሚመጡት ደንበኞቻችን ለእይታ በማቅረብ በተለያዩ መንገዶች ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎቻችንንም ጭምር በመጠቀም ለገበያም እናቀርባለን ስትል ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች። “ከአለም ዙሪያ እና ሀገር ውስጥ ከሚታወቁ ስራ ፈጣሪዎች እና ዲዛይነሮች ጋር የልምድ ልውውጥ እንድናደርግ ሁኔታዎችን ያመቻችልናል። የገበያ ትስስርም እንድንፈጥር ያግዘናል” ትላለች።

በመሆኑም ክራፍት የተለያዩ ዲዛይን ያላቸውን የሌዘር ምርቶችን ከእንጨት እና ከፕላስቲክ ጋር በማድረግ የእጅ ቦርሳዎችን፣ የእጅ ጌጣጌጦችን እና ለቤትና ለቢሮ የሚውሉ መገልገያዎችን እንዲሁም ማስታወሻ ደብተሮችንም በማምረት በማህበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ ባዛሮች ላይ ምርቶቿን ለገበያ እያቀረበች እንደምትገኝ የምትገልጸው ሜሮን በቅርቡ ከማዕከሉ ተመርቃ ስትወጣ ተጨማሪ ሰራተኞችን ቀጥራ ምርቶቿን በስፋት የማምረት እቅድ እንዳላት ነግራናለች።

ራሄል እደግልኝ እንደሜሮን ካሉ በማዕከሉ የስልጠና ዕድል ከተመቻቸላቸው ወጣት የስራ ፈጣሪዎች አንዷ ስትሆን የተለያዩ የልብስ ውጤቶችን በተለያዩ አይነት ዲዛይኖች ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ በፈጠራ ተቋሙ በአዳዲስ ዲዛይኖች የተሰሩ አልባሳት ውጤቶችን በማሰናዳት ትገኛለች።

“ማዕከሉ የተለያዩ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማመቻቸት ስልጠናዎችን በማዘጋጀት፤ ከሀገር ወስጥ እና አለም አቀፍ ልምድ እና እውቅና ካላቸው ዲዛይነሮች ጋር ተገናኝተን ልምዶችን እንድንቀስም ያግዘናል” የምትለው ራሄል ባለፈው ሳምንት ከጣሊያን ሀገር የመጣ ታዋቂ ዲዛይነር ለስራቸው የሚያግዝ ስልጠናዎችን እንደሰጣችው ትናገራለች።

የፈጠራ ተቋሙ/ሀቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተመስገን ፍሰሀ ማዕከሉ የተመሰረተበትን ዋና አላማ ሲያብራሩ ውስጥ ያሉትን የስራ ፈጠራ ባለቤቶች እና በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶችም በአለም አቀፍ የዲዛይኒንግ ክህሎትን እንዲያገኙ በማገዝ በአይነቱ ለየት ያለና የተሻለ የዲዛይን ሀሳብ በመጠቀም የተለያዩ ምርቶች ይዘው እንዲመጡ ማስቻል ሲሆን ለዚህም የሚረዱዋቸውን የተለያዩ ግብአቶችን አካቶ የሚገኘው ይህ የፈጠራ ተቋም የአብሮ መስሪያ ቦታ፣ ፈጣን ዋይፋይ፣ ፋብሪኬሽን ላብራቶሪ፣ ዲጂታል ላቦራቶሪ እና ኦዲትሪም እና ሌሎችንም ያካተተ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የፈጠራ ተቋሙ የገበያ ትስስርንም እንዲያገኙ፣ ምርቶቻቸውንም በማህበራዊ መገናኛዎች እና በባዛሮችም ጭምር የሚያስተዋውቁበትን መድረክ እንዲሁ በማዘጋጀት እንዲታዩላቸውም እንሰራለን፣ ከዚህም በተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችንም እናመቻችላቸዋለን ያሉት ሀላፊው ማዕከሉ እስካሁን የብድር አቅርቦት እየሰጠ እንዳልሆነ በመግለጽ በቀጣይ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የብድር አማራጮችንም የሚያገኙበትን ሁኔታዎችን እናመቻቻለን፤ በዚህ የፈጠራ ተቋም ውስጥ አምስት አይነት ሴክተሮች በስራችን አሉ እነሱም ፋሽን ዲዛይን፣ ሌዘር ዲዛይን ፣ ቴክስታይል፣ ፕሮዳክት ዴቨሎፕመንት እና ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሲሆኑ የኛ የፈጠራ ተቋም በነዚህ ዘርፎች ላይ ነው ስልጠናዎችን፣ የመስሪያ ቦታዎችን፣ ቤተመጽሐፍትን፣ ፋብሪኬሽን ላቦራቶሪ እና የዲዛይኒንግ ስልጠናዎችን የምንሰጥበት ነው በማለት አብራርተውልናል።

“የስራ ቦታውን ያመቻቸልን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተቋም ሲሆን የጣልያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎልናል። ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር የአይ ሲ ቲ እና ዲዛይኒንግ ስልጠናዎችን ከአይስ አዲስ እና አፍሪካን ሞዛይክ ጋር በመተባበርም ነው ስልጠናዎች የምንሰጠው”።

በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል የመስሪያ ቦታ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የክህሎት ክፍተቶች ወ.ዘ.ተ እንቅፋት ሲገጥማቸው ይስተዋላል፤ የወጣቶቹን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለማዘጋጀትና ድጋፍ ለማድረግ በሚል በመንግስት ተቋማት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በግለሰብ ደረጃ የተቋሙ የስራ ፈጠራ ክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማት በርካታ ወጣቶችን ሲደግፉ ቢስተዋልም ለብዙሃኑ ተደራሽ አይደለም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል። 

አብዱላሂ አደም የኦሮሚያ ኢንተርፕረነርሺፕ ዴቨሎፕመንት ሴንተር ኮርዲኔተር ናቸው። እንዲህ አይነት ማዕከል ለሀገሪቱም ብሎም ለወጣቱ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ይላሉ።  “ወጣቱ የፈጠራ ሀሳቡን ይዞ በየሰፈሩ ከሚቀር እንደዚህ አይነት ቦታዎች በየከተሞች ቢስፋፉ ትልቅ ተጽእኖ ያመጣሉ፤ ስራ ፈጣሪ ትውልድም አንዲፈጠር የራሱን ድርሻም ይወጣል” በማለት ይገልጻሉ። ነገርግን ይላሉ ባለሙያው “ ነገር ግን የስራ ፈጠራ የጥምረት ስራን የሚፈልግ ዘርፍ ስለሆነ የተለያዩ አካላትን ማለትም የመንግስትን፣ የግሉ እና የተለያዩ ድርጅቶች የጋራ ጥረት ቢታከልበት የበለጠ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፤ ምክንያቱም ከትላልቅ ፋብሪካዎች ይበልጥ እንደዚህ ባሉ የፈጠራ ቦታዎች ላይ አዳዲስና በአይነታቸው ለየት ያሉ የፈጠራ ውጤቶችን ለማግኘት ትልቅ አቅም ይኖረዋል” ይላሉ።

አስተያየት