መጋቢት 30 ፣ 2014

የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ መጓተት 11 ቢልዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጠየቀ

City: Dessieዜና

የመጀመሪያውን ዙር ኘሮጀክት በጨረታ ያሸነፈው ኮንትራክተር በ2007 ዓ.ም. ግንባታውን ጀምሮ በግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መናር ምክንያት በታቀደው ጊዜ አጠናቆ ማስረከብ አልቻለም

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ መጓተት 11 ቢልዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጠየቀ
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ

የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል በ3 ቢልዮን ብር ካፒታል የተጀመረ ፕሮጀክት ነው። ግንባታው በ2007 ዓ.ም. ሲጀመር የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ጨምሮ 5.5 ቢልዮን ብር እንደተመደበለት የወቅቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያሳያል። ሆስፒታሉን ጨምሮ ሌሎችም የማስተማሪያ ህንጻዎች ግንባታ በ3 ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ቢጠበቅም 7ኛ ዓመቱን ይዟል። በልዩ ልዩ ምክንያቶች 4 ዓመት የዘገየው የግንባታው ሂደት 11 ቢልዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንደጠየቀ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ደረጀ ተስፋዬ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አስማማው አባተ የሆስፒታሉ ግንባታ ተጓቷል የሚለውን ቅሬታ ይቀበላሉ። “ሕዝቡ በትኩረት የሚከታተለው ፕሮጀክት ነው” የሚሉት አቶ አስማማው የደቡብ ወሎ ነዋሪ ፕሮጀክቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደለም በሚል ኮሚቴ አዋቅሮ ጠቅላይ ሚነስትር ጽ/ቤት ድረስ በመጓዝ ጥያቄውን ያሰማበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

“በተጨማሪም የግንባታውን ሂደት በበላይነት ማን ያስተዳድረው?” የሚለው ጥያቄ ብዙ ሲያከራክር ቆይቶ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ስር እንዲተዳደር መወሰኑን፣ የፌደራል መንግሥት በጀት መድቦለት የግንባታ ሂደቱ እንደቀጠለ ነግረውናል።

የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ደረጀ ተስፋዬ የሆስፒታሉን አጠቃላይ የግንባታ ሁኔታ ሲገልጹ ኘሮጀክቱ በሁለት ምእራፍ እንደሚከናወን ነግረውናል። ተቆጣጣሪው በማብራሪያቸው፡-  

የመጀመርያው ምዕራፍ 4 ፕሮጀክቶች እና 28 ሕንጻዎች ሲኖሩት የማስተማሪያ ሕንጻዎችን፣ ቤተ-መጻሕፍትን፣ የቅድመ እና የድህረ ምረቃ የተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻ ግንባታን የሚያካትት ነው። ከእነዚህ መካከል ለቅድመ ምረቃ የታሰቡት 6 ህንጻዎች ተጠናቀው አራቱ በመገንባት ላይ መሆናቸውን ሰምተናል። የስፖርት ማዘውተሪያን እና የሰራተኞች መኖርያን ጨምሮ በድምሩ 9 ህንጻዎች በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው።

“ሁለተኛው ምዕራፍ የዋናው ሆስፒታል ግንባታ ነው” ያሉት ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ በአሁን ሰዓት በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል።

ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ ከ16 በላይ የ‘ሰብ ስፔሻሊቲ’ ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል። በ3.2 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው ሆስፒታሉ በዓመት 15 ሚሊዮን ታካሚዎችን ያስተናግዳል ተብሏል።

አቶ ደረጄ “የመጀመሪያውን ዙር ኘሮጀክት በጨረታ ያሸነፈው ‘ኮንትራክተር’ በ2007 ዓ.ም. ግንባታውን ጀምሮ በግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መናር ምክንያት በታቀደው ጊዜ አጠናቆ ማስረከብ አልቻለም። በአሁን ሰዓት ችግሩን ለማቃለል በተደረገ ርብርብ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

የህዝብ ጥያቄ የሚበዛበትን የዋናውን የሆስፒታል ግንባታ ጉዳይ አስመልክቶ አቶ አስማማው ሲናገሩ “አሁን ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው በሁለት ተቋራጮች ነው። በአንደኛው ተቋራጭ እየተገነቡ የሚገኙት ሕንጻዎች በአብዛኛው በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። የተዘረፉት እና የተበላሹት የሕንጻው ክፍሎች እንዲሟሉ እየተደረገ ነው” ያሉ ሲሆን ሕንጻዎቹ በያዝነው ዓመት ተጠናቀው በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የጤና ሳይንስ ተማሪዎች እንዲማሩበት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነግረውናል።

በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የሆስፒታሉ ግንባታ ጨረታም በቅርቡ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አስተያየት