ጥቅምት 5 ፣ 2015

በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ዉሳኔ ላይ "ዎላይታ ክልላዊ መንግስት" የሚል አማራጭ እንዲቀመጥ ተጠየቀ

City: Hawassaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት በሚደረገው ህዝበ ዉሳኔ "የዎላይታ ክልል" የሚል አማራጭ የሌለበትን ምርጫ ፓርቲዉ እንደሚያወግዝ ገልጿል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ዉሳኔ ላይ "ዎላይታ ክልላዊ መንግስት" የሚል አማራጭ እንዲቀመጥ ተጠየቀ

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎህዴግ) አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት በጥር ወር መጨረሻ ይደረጋል በተባለው ህዝበ ዉሳኔ ላይ "የወላይታ ብሔራዊ ክልል" የሚል አማራጭ መካተት አለበት ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

ዎህዴግ ዛሬ ጥር 05 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣዉ መግለጫ “የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደር ያቀረበውን ህገመንግስታዊ መብት ወደ ጎን በመተዉ የገዢው ፓርቲን ክላስተር የተባለውን ኃሳብ ለማስፈጸም የሚደረገው አካሄድ ኢ-መንግስታዊ በማለት” ተቋውሞውን አሰምቷል።

በደቡብ ክልል ስር ካሉት 6 ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሚያደርጉት ህዝበ ዉሳኔ ላይ "የዎላይታ ክልል" የሚል ምርጫ የሌለበትን ምርጫ ፓርቲዉ እንደሚያወግዝ በመግለጫዉ ገልጿል።

በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተብለው እንደሚካተቱ የተቀመጡትና ህዝበ ዉሳኔ ለማድረግ እየተጠባበቁ ከሚገኙት ዉስጥ ዎላይታን ጨምሮ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ደራሼ፣ አሌ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ኬሌ፣ ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ይገኙበታል።

መቀመጫውን ዎላይታ ሶዶ ያደረገዉ ፓርቲው ሪፈረንደም የመራጩ ህዝብ ሃሳብና ተጨማሪ አከራካሪ ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ድምፅ የሚሰጥበት ስርዓት መሆኑ ገልፆ "ነገር ግን አሁን ላይ ምንም አይነት ምርጫ ለህዝብ አልተቀመጠም" ብሏል። 

"ዎላይታ ብሔራዊ መንግስት መሆን፣ በክላስተር መደራጀት እና በደቡብ ክልል ስር መቀጠል የሚሉ አማራጮች ለህዝብ እስካልቀረቡ ድረስ ህዝበ ዉሳኔዉ ትርጉም የለዉም" በማለት ፓርቲው አቋሙን አስታውቋል።

በደቡብ ክልል በተደጋጋሚ እየተነሱ በሚገኙ በክልል እንደራጅ ጥያቄዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት የሲዳማ ክልል እንዲሁም አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳዎች በጋራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚል ክልል ሆነዋል። 

መንግስት በክልል ለመደራጀት ጥያቄ የሚያቀርቡ ዞኖች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ "ክላስተር" የሚል ሀሳብ የመፍትሔ አማራጭ ማምጣቱ ይታወሳል። ይህን አዲስ የመንግስት አደረጃጀትተቀብለው በምክር ቤታቸው ያፀደቁት ዞኖችም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔያቸውን ልከዋል። 

የእላስተር አወቃቀር ተቀራራቢ መልክዓ ምድር፣ በአኗኗር፣ ባህል እና በቋንቋ ተቀራራቢ የሆኑ ጎረቤት ዞኖች እንዲሁም ልዩ ወረዳዎች ባማከለ ሁኔታ እንደተቀረፀ መንግስት አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የሚገኙ 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች በክላስተር የመደራጀት ጥያቄያቸውን በመቀበል በጋራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሆን እንደሚችሉ እና ህዝበ ዉሳኔ እንዲካሄድ ተወያይቶ ከዉሳኔ ሲደርስ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ ዞን እና የም ልዩ ወረዳ በአንድ ላይ ክልል ለመሆን ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በነባሩ ደቡብ ክልል ስር እንዲቀጥሉ መንግስት ወስኗል።

አስተያየት