ግንቦት 19 ፣ 2013

የትግራይ ክልል እጣ ፈንታ ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኋላ

ምርጫ 2013ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ፣ የሰብአዊ ቀውሱ አገግሞ ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ እስኪቻል ድረስ ክልሉ በፌደራል መንግሥት ምስረታ ላይ ምን ዐይነት ሚና ይኖረዋል? በማንስ ይተዳደራል?

 የትግራይ ክልል እጣ ፈንታ ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኋላ

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ ከትግራይ ክልል በስተቀር አዲሱን ክልል ሲዳማን ጨምሮ 9ኙ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ምርጫ ለማካሄድ የመጨረሻዎቹን ዝግጅቶች ላይ  እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት “የጨረባ ምርጫ” ሲል የሰየመውና ተቀባይነት የሌለው ብሎ ያጣጣለውን ክልላዊ ምርጫ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ያካሄደችው ትግራይ ምርጫውን በዚህ ጊዜ ታካሂዳለች የሚል ቀን አልተቆረጠላትም፡፡

የመራጮችን አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መንግሥት በሚመሰርትበት፣ በሚወዳደርበት ምርጫ ጣቢያ ብዙኃን የመረጡት ግለሰብ የምክርቤት ወንበር በሚያገኝበት፣ 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚካፈሉበት በ6ኛው ሐገራዊ መርጫ ትግራይ ክልል ውክልና የላትም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ፣ የሰብአዊ ቀውሱ አገግሞ ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ እስኪቻል ድረስ ክልሉ በፌደራል መንግሥት ምስረታ ላይ ምን ዐይነት ሚና ይኖረዋል? በማንስ ይተዳደራል? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ምላሽ እና የሕግ ባለሙያ ሐሳብ ይዘናል፡፡

“ምርጫ ማድረጉ በራሱ ሕገ-መንግሥታዊ ዐይደለም” የሚሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሕግ ባለሙያ ይህም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 38 ላይ የተጠቀሰውን “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እድሜው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሰረት የመምረጥ፣ የመመረጥ መብት አለው’’የሚለውን ድንጋጌ ለትግራይ ክልል የሚጥስ በመሆኑ ነው ይላሉ።  

አክለውም አንቀጽ 61 ላይ “የፌዴረሽን ምክር ቤት አባላት፤ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ህዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል። በተጨማሪም የብሔሩ ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል” ተብሎ የተቀመጠውን እንዳማያከብር ይናገራሉ። ነገር ግን የሕግ ባለሙያዋ እንደሚሉት “ትግራይ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንደመሆኗ አዋጁ እስከሚነሳ የምርጫ መብት ሊነፈግ ይችላል። ስለሆነም ከትግራይ ውጭ ባሉ የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች ድምጽ የመንግሥት ምስረታው ይካሄዳል” ያሉ ሲሆን “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደተነሳ በአፋጣኝ ምርጫ መካሄድ አለበት’’ብለዋል። 

በክልሉ ምርጫ እስከሚካሄድ የጊዜያዊ አስተዳደር ስራውን ቢቀጥል እና የፌዴሬሽን እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ጊዜያዊ አስተዳደር ቢወከል የተሻለ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዋ መሰረታዊ የሚባሉ ውሳኔዎች ላይ የህዝብ መብት እንዳይጓደል ትግራይ ተሳታፊ መሆን እንዳለባት በመግለጽ ነው።

“በምርጫው ውጤት የመንግሥት ምስረታ በሚደረግበት ወቅት አንድ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ አሸንፎ የፌዴሬሽን እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ቢይዝ በቀደመው ምርጫ አሸናፊ ተብሎ በትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድርነት ቦታ ላይ ያለው (ኢህአዴግ/ብልጽግና) ፓርቲ ቀጥሎ ተወካይ መሆን ይችላል?’’ ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ “ይሄ ነው ተብሎ የተጻፈ ሕግ የለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ “ሥልጣኑን በሚይዘው ፓርቲ አቋም ሊወሰን ይችል ይሆናል አሊያም ትግራይ ብቻ ምርጫ እስከምታደርግ አሁን ባለው ፓርቲ (ብልጽግና) ልትቆይ ትችላለች። ይሄ ይሆናል ተብሎ ከሕግ አንጻር ለመናገር ይከብዳል” በማለት የሕግ ባለሙያዋ መልሰዋል። 

ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር እንደሚሉት በትግራይ ክልል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እየተመራ በክልሉ ምርጫ እስከሚደርግ ድረስ ይቆያል። ነገር ግን የክልሉ ቀጣይ የጊዜያዊ አስተዳደር ዕጣፈንታ ምርጫውን በሚያሸንፈው ፓርቲ ሊወሰን እንደሚችል ይናገራሉ። አክለውም “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተፎካክሪ ፓርቲ አመራር ሊተካ ይችላል’’ ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር አብረሀም በላይ (ዶ/ር) ርዕሰ ጉዳዩን አስመልክተው የሰጡን አጭር ምላሽ ''በትግራይ ክልል ምርጫ አይደረግም፤ ምርጫ ካልተደረገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ አይኖርም እንዲሁም ምርጫ እስከሚካሄድ በጊዜያዊ መስተዳድር መተዳደሯን ትቀጥላለች’’ የሚል ነው።

በ2012 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ሃገራዊ ምርጫ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ተከትሎ ጷግሜ 4 ላይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያልተሳተፈበት በትግራይ ክልል ምርጫ መደረጉ፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሙሉ በሙሉ አሸንፌአለሁ ማለቱ፣ በፌደራል መንግስት ቅቡልነት ያላገኘው ምርጫ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የፈጠሩት ውጥረት ከ6 ወር በፊት የፌደራል መግሥት “ሕግ ማስከበር”፣ የሕወሓት ባለስልጣናት “ዘር ማጥፋት” ብለው የሰየሙት ዘመቻ መካሄዱ፣ በዘመቻው የሕወሓት ኃይል የአስተዳደር ወንበሩን ለቆ ጫካ መመሸጉ፣ ትግራይም በጊዜያዊ አስተዳደር በመመራት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡

አስተያየት