የአሜሪካ መንግስት በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ በኢትዮጵያ የጣለችው ማዕቀብ አሁንም አሳሳቢ የደህንነት ሁኔታዎች በመኖራቸው ለቀጣይ አንድ ዓመት እንዲራዘም ፕሬዝዳንት ባይደን ወሰኑ።
እ.ኤ.አ. መስከረም 2021 ከሁለት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኤግዚኪዩቲቭ ኦርደር 14046 መሰረት በብሄራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ላይ የተደቀነ ስጋትን ለመቋቋም በሚል ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የጣለውን ማዕቀብ ለአንድ ዓመት አራዘመ።
የኋይት ሃውስ መግለጫ እንዳመላከተው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዲሁም ችግሩን የተከተሉ ወቅታዊ የሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ መሆን ኢትዮጵያን እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ላይ ያላቸው ስጋትን ገልፆ “ከወትሮው በተለየ መልኩ በብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያልተለመደ ስጋት መፍጠሩን ቀጥሏል” ብሏል።
በዚህ ምክንያት በመስከረም 2021 ኢትዮጵያን በሚመለከት የታወጀው ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ ማእቅብ ከፈረንጆች መስከረም 17 2023 ጀምሮ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንዲቀጥል መወሰናቸውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ባለስልጣናት ማዕቀቡን በተደጋጋሚ “በውስጥ ጉዳይ ተገብቶ የተጣለ ማዕቀብ” በማለት የሚጠሩት ሲሆን በ2013 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ የተደረገውን ጨምሮ የአሜሪካ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ሊያሳድር በሚችለው ጫና ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ሲደረጉ ተስተውሏል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣላቸው ማዕቀቦች የኢትዮጵያ እንዲሁም የኤርትራ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊ ሰራተኞች እና ሌሎች ግለሰቦች የቪዛ እገዳ፣ በትግራይ ክልል እና በኢትዮጵያ ለተስፋፋው ብጥብጥ፣ ግፍ እና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ የሆኑ አካላት እና ግለሰቦች ላይም ልዩ ማዕቀቦችን ያካተተ ነው።
በተጨማሪም የመከላከያ አገልግሎቶችም ሆኑ መሳሪያዎች ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የታጠቁ ኃይሎች፣ ለፖሊስ፣ ለስለላ ወይም ለሌሎች የውስጥ ደኅንነት ኃይሎች እንዳይላኩ እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 100 ሚልየን ዶላር ገቢ ታገኝበት የነበረው የአፍሪካ የዕድገትና ዕድል ሕግ (አጎአ) ከቀረጥ ነፃ የአሜሪካን ገበያ ተጠቃሚነትን ማሳጣት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ከሚቀጥሉ ማዕቀቦች ዋነኞቹ ናቸው።
አሜሪካ የመጀመሪያውን ማዕቀብ በመስከረም 2021 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ስትጥል በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት አባሎች፣ በአማራ ክልል ኃይሎች እንዲሁም በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን ይፋ አድርጋ ነበር።
የመጀመሪያው ማዕቀብ አንድ ዓመት ሲሞላው ባለፈው ዓመት መስከረም 2022 ላይ የአሜሪካ መንግስት ማዕቀቡን ለማራዘም ሲወስን የቻይና መንግስት ተቃውሞ አሰምቶ ነበር። ማዕቀቦቹ አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ተራዝሟል።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ለሁለት ዓመታት የተደረገው የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ጦርነት በአሜሪካ ከፍተኛ “ሚና” አልያም “ጫና” ተፋላሚ ኃይሎቹ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተገናኝተው የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።
ከአራት ወራት በፊት የፌደራል መንግስት “የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት” መወሰኑን ተከትሎ የተለያዩ ታጣቂዎችን መንግስት “መልሶ ማደራጀት” ብሎ በሚጠራዊ ተፋላሚዎች ደግሞ “ትጥቅ ማስፈታት” ብለው በሰየሙት ሂደት በአማራ ክልል መከላከያ ሠራዊት ከፋኖ ኃይሎች ጋር ውጊያ ገጥሟል።
ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን ረቂቅ አፅድቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የፌደራል መንግስቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በጅምላ እስር እና አስገድዶ መሰወር እየየተቸ እና ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጣ የሚጠይቁ ተበራክተዋል።
የአማራ ክልል አዲስ አስተዳደር ከሰሞኑ እንዳሳትወቀው አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ያለ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች የሽምቅ ውጊያዎች አልፎ አልፎ እየተከሰቱ መሆናቸውን ግን መገናኛ ብዙኀን እየዘገቡ ነው።