ጳጉሜ 2 ፣ 2015

በመቀሌ የተቃውሞ ሰልፍ ከ120 በላይ ሰዎች ሲታሰሩ በርካቶች በፖሊሶች ተደበደቡ

City: Addis Ababa

ትላንት(ጳጉሜ 1፣ 2015) የታሰሩት የሶስቱ ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት ካደሩብት ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በመቀሌ የተቃውሞ ሰልፍ ከ120 በላይ ሰዎች ሲታሰሩ በርካቶች በፖሊሶች ተደበደቡ

ውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት)፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት)  እና ባይቶና ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲዎች 'ኪዳን ለስር ነቀል ለውጥ' ለውጥ በሚል ተጣምረው በዛሬው ዕለት ጳጉሜ 2፣ 2015 መቀሌ ከተማ ሮማናት አደባባይ በጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ከ120 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የሰልፉ አስተባባሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህ እንደሚጨምር ተገምቷል።

በትግራይ ክልል የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠራው ሰልፍ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ያላቸውን ጥያቄ ለማቅረብ ሲሆን በትላንትናው እለት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ እንዲሁም ከቀናት በፊት የመቀሌ ከተማ አስተዳደር እንዳስታወቁት የክልሉ “የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም” እንዲሁም “ከበዓላት ጋር ተያይዞ ሰልፉን ለመጠበቅ የሚያስችል የፀጥታ ሀይል አቅም የለም” የሚሉ ማሳሰቢያዎች ሲሰጡ ነበር።

ከማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት መታሰር የጀመሩ ሲሆን በትላንትናው እለት የሳልሳይ ወያነ ሊቀ መንበር ሃያሉ ጎደፋይ፣ የውድብ ናፅነት ትግራይ ሊቀ መንበር ደጀን በርሀ እንዲሁም የባይቶና ዓባይ ትግራይ አመራር አቶ ክብሮም በርሀ የታሰሩ ሲሆን በዛሬው እለት “የት እንደተወሰዱ አልታወቀም” ተብሏል።

ከሶስቱ ፓርቲዎች ማለትም ውናት፣ ሳወት እና ባይቶና ከእያንዳንዳቸው ሶስት አመራሮች ተመርጠው የተዋቀረው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትም ከሁለት አስተባባሪዎች በስተቀር ሁሉም ታስረዋል። አዲስ ዘይቤ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት እና የውድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት) ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑትን አለምሰገድ አረጋይ ያነጋገረች ሲሆን በዛሬው እለት ከ120 በላይ ሰዎች ከሰልፉ “ታፍሰዋል” ብለዋል።


ዛሬ በሰላማዊ ሰልፉ እለት ብቻ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ከ20 በላይ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እንደታሰሩ የሰልፉ አስተባባሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ሲደርስባቸው 13 የሚሆኑ ሌሎች ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደህክምና ተቋማት ተወስደዋል።

ዛሬ ጷግሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም ንጋት ላይ ሰላማዊ ሰልፉን ለመምራት “ሁለት የድምፅ ማጉያ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በፖሊሶች ከተወሰደ በኋላ ሌላ ሶስተኛ የድምፅ ማጉያ ሲጨመር እሱም ተወስዷል” ሲሉ አለምሰገድ አረጋይ ተናግረዋል።

ከጠዋቱ 5 ሰዓት ድረስ ብቻ የዓረና ሊቀ መንበር ዓምዶም ገብረስላሴን ጨምሮ 13 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ ስድስት የቀድሞ የትግራይ ሠራዊትና ሰልፉ ላይ የነበሩ ሰዎች እንዲሁም አራት ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ንፁሃን ሰዎች በአጠቃላይ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች ለእስር ተዳርገው ነበር።

ሰላማዊ ሰልፉ የተጠራበት ሮማናት አደባባይ አካባቢ “ከሰልፈኞች ቁጥር ያልተናነሰ የፀጥታ ኃይል” እንደነበር የሚገልፁት የውድብ ናፅነት ትግራይ ምክትል ሊቀ መንበር፤ በሰልፈኞች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግብግብ ነበረ ብለዋል።

“የከተማው ዙሪያ በትግራይ ኃይል  ታጣቂዎች ኃይለኛ ጥበቃ ነበረበት፣ የቀረው የከተማ ፖሊስ እና ሚሊሻ በሙሉ አደባባዩ ጋር ነው የነበረው። አደባባዩ ጋር ኦልሞስት በሚያሳዝን መልኩ ከሚሰለፈው ሰው ቁጥር እኩል የሚሆን ኃይል ነው ያለው ወደ አደባባዩ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ተዘግተዋል፤ ወደዛ የሚያልፍ ካለ ሙሉ የያዘው ንብረት እየተወሰደ ነው። ለሰላማዊ ሰልፉ የተዘጋጁ ወደ 38 ባነሮች ተወስደዋል” ሲሉም አስተባባሪው የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በብዙ ጥረት ወደ አደባባዩ ያለፉ ሰልፈኞች “በተቻለ ሁኔታ” ፍትህ ይንገስ፣ ሰላም ይስፈን፣ ዳቦ ለህዝባችን የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎችና መፈክሮችን አሰምተዋል።

ሊቀ መናብርቱ ትላንት የታሰሩበት ቀዳማይ ወያነ እስር ቤት የሉም። ማረሚያ ቤቱ አገልግሎት የሌለበት አዳራሽ ውስጥ ተከተዋል። ከሊቀመናብርቱ በፊት እዛ የታሰሩት ሰዎች አሉ፣ ዛሬም የግቡት አሉ መሪዎቹ ግን የሉም፡፡”ሲሉ አስተባብሪው አስረድተዋል።
 

አስተያየት