መጋቢት 16 ፣ 2014

ተበዳይን ያልካሰ ብሄራዊ እርቀ ሰላም ፍትሕን አያሰፍንም

City: Addis Ababaአስተያየት

ሁሉን አቀፍ ሰለማዊ ድርድር ሲካሄድ፣ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት የሚወክሉት ቡድን ፈጽሞታል ተብሎ የሚታመኑትን ጥፋቶችን አምኖ በመቀበል ህዝባዊ ይቅርታ መጠየቅና ካሳ መክፈል ይገባቸዋል።

Avatar: Borga Delassa
ቦርጋ ደላሳ

Borga Delassa is a 4th-year law student at Addis Ababa University

ተበዳይን ያልካሰ ብሄራዊ እርቀ ሰላም ፍትሕን አያሰፍንም
Camera Icon

Photo: Getty Image

ኢትዮጵያ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ ጥፋቶች ተመዝግበዋል። ጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከነበራቸው ተፋላሚዎች ባለፈ ዳፋው ለንፁሀን ተርፎ በርካቶችን ለከፋ ጉዳት ዳርጓል እየዳረገም ይገኛል። ከዛም ቀደም ባለው ጊዜ  በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች በተከሰቱ የብሄር መልክ ባላቸው ግጭቶች ሳቢያ የዜጎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል ያስከተለ የሰላም እጦት በስፋት ተስተውለዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ብዙ አሰቃቂ ጥቃቶችና ወንጀሎች ሲፈጸሙ ነበር። ለእነዚህ ወንጀሎች በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የፌደራልና የክልል መንግስታት፣ የታጠቁ ቡድኖች፣ የህብረተሰብ አካላት ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች እርስ በእርስ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሲካሰሱም ይታያል። ይህም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ስፋት ባለው መልኩ የአጥቂና የተጠቂ የማህበረሰባዊ አተያይ ጥሯል። 

የዚህ አይነት የአመለካከት ባህሪያት መገለጫ ደግሞ፣ በማህረበሰብ ውስጥ የደረሱ በደሎች በሌላ በማህበረሰብ አካል ላይ የማሳበብ ሁኔታ ይስተዋላል። ከዚህም የተነሳ አጥቂ ተብሎ ከተፈረጀው ማህበረሰብ የመጣ ማንም ግለሰብ የአጥቂው ማህበረሰብ ባህሪያት ተብሎ የታመነውን አንፀባራቂ ተደርጎ ይቆጠራል። እራሱን በመጠቃት የሚያየው ቡድንም ይህን አጥቂ ማህበረሰብ ሆነ ሌላ ቡድንን ሲያጠቃ ደግሞ እራስን የመከላከያ መንገድ እንደሆነ በማሰብ ይከውናል። ተጠቂው ማህበረሰብ ደግሞ በዛኑ ያህል  የቁጭት ስሜት ይፈጠርበታል ይህም የቂም በቀል ስሜትን ይፈጥራል። ይህ ክስተት በዓለም ላይ አጋጥመዉ ባለፉ ጦርነቶች ማግስት የተስተዋለና በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋረጠ የግጭቶች ውጤት ነው። በ2ኛው የዓለም ጦርነት የአይሁዶች አሰቃቂ መገደል ካበቃ ሰባታ አስርት ዓመታት ቢያስቆጥርም እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ባህሪያት በተለያዩ እስራኤላውያን ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲስተዋሉ ይታያሉ። ምን አልባትም ይህ አተያየት   የዘለቀው የደረሰባቸውን ግፍ ለማስታወስ የተቀሟቸው የተለያዩ መዘክሮች በህዝቡ ዘንድ እነዚህ ስሜቶች እንዲቆዩ ምክንያት ይሆናል።

በቅርቡ በኢትዮጲያ ሊካሄድ የታሰበዉን ሀገራዊ እርቅና ዉይይት የሚመሩ ኮሚሽነሮች ለህዝብ ይፋ ሆነዉ በይፋ እንቀስቃሴ ጀምረዋል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተዉ ጦርነትም ቆሞ በመንግስትና በትግራይ ሀይሎች መካከል (ይፋ የተደረገ ነገር ባይኖርም) ድርድር ለማካሄድ ሙከራዎች መጀመራቸዉ እየተሰማ ይገኛል። ወደ እነዚህና ሌሎች ሰላማዊ ድርድሮች ለመሸጋገር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መዘንጋት የሌለባቸው ነጥቦች አሉ። የኢትዮጵያ ግጭቶችም በከፍተኛ ሁኔታ ማህበረሰቡን ያሳተፉ እንደመሆናቸው ጭምር የአጥቂና ተጠቂ ግንኙነቶችና አስተያየቶች በመፈጠራቸው ምክንያት ዘላቂ ሰላም ለሚያደረጉ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ እንቅፋቶች ይሆናሉ ተብሎ ይሰጋል። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚወሰዱ እርምጃዎች ፀሀፊው ከታች የተዘረዘሩትን ሃሳቦች መካተት አለባቸው ብሎ ያምናል። በመጀመሪያም ሁሉን አቀፍ ሰለማዊ ድርድር ሲካሄድ፣ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት የሚወክሉት ቡድን ፈጽሞታል  ተብሎ የሚታመኑትን ጥፋቶችን አምኖ በመቀበል ህዝባዊ ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል። ከላይ በተጠቀሱት ጥናቶች ውስጥ የሚስተዋለው፣ ተጠቂው ቡድን በራሱ ላይ በደሎች እንደደረሱ ዕውቅና ይፈልጋል በተለይም አጥቂ ተብሎ በሚታመነው ቡድን ጥፋቱን እንዲያምንና ይቅርታ እንዲጠይቀው ይፈልጋል። የዚህ ዕውቅናና ይቅርታ መኖር ለሰላማዊ ህይወትና አመለካከት መመለስ ጉልህ ድርሻ አለው ተብሎ ይታመናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱት ወንጀሎች ተጠያቂ ተብለው የተለዩ አካላት ሁሉ ተጎጂ ማህበረሰቦች ያማከለ የካሳ ክፍያ መፈጸም አለባቸው ብሎ ፀሃፊው ያምናል። ይህ ካሳ የወደሙ መሰረተ ልማቶች ከማደስ የታሰበ ሳይሆን በተለያዩ ችግሮች ቀጥተኛ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች በቀጥታ የሚሰጥ መሆን አለበት።

ይህ ሲብራራ የፌደራል መንግስት በትግራይ ጦርነት ለደረሰው ጉዳቶች፣ በወለጋና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በህግ ማስከበር ሂደት ወቅት ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ መክፈል ይገባዋል። በተጨማሪም የፌደራል መንግስት የሀገሪቱን ዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለበት 
በተለያዩ አከባቢዎች ለደረሱ መፈናቀሎች ለተጎጂዎች ወይም ተጎጂ ነን ብለው ለሚያስቡ ዜጎች ክፍያ መፈፀም ይገባል። ከእነዚህም መካከል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ ነዋሪዎች ላይ በሕግ ማስከበር ስም ለደረሱ ጉዳቶች፣ የክልሉ ነዋሪ በሆኑ የአማራ፣ ጉራጌና ሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ላይ ለደረሰ መፈናቀል፣ ሞት፣ ንበረት መውደም፤ በተለይም በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ተወላጆችና ሌሎች ብሄሮች ላይ ለደረሰ ሞት፣ መፈናቀል፣ ንብረት መጥፋት ኃላፊነቱን በመውሰድ የካሳ ክፍያው አንድ አካል ሊሆን ይገባል።

የትግራይ ክልል መንግስትም ወደ አማራና አፋር ክልሎች በጦርነት ለፈፀማቸው የተለያዩ ጥቃቶች፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በአማራ፣ በኦሮሞና ሌሎች ብሄሮች ለደረሱ መፈናቀልና ጉዳቶች፣ የአማራ ክልል መንግሥት በተለያዩ በሕግ ማሰከበር ድርጊቶች በተለያዩ ሰዎች ላይ ለደረሱ ጉዳቶች ካሳ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባቸዋል። ከታጠቁና ከተደራጁ አካላት አንፃር ደግሞ፣ ኦነግ ሸኔ በተለያዩ ጊዜያት በአማራ ተወላጆች ላደረሰው ግድያና ማፈናቀል፣ ህወሓት በስሙ እና በአመራሮቹ ለተፈፀሙ ጉዳቶች ካሳ መክፈል ይኖርበታል።

ገዥዉ ፓርቲ ብልፅግናም ሀገሪቱን እንደሚያስተዳድር ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ የተተከሰቱ የእርስበርስ ግጭቶች ባለመከላከሉና ለዜጎች ጠበቃ ባለማድረጉ ለተፈጠሩ ጉዳቶች ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ለጉዳት ካሳ ሊከፍል ይጠበቃል። ከነዚህ ከተዘረዘሩትና ሌሎች የተደራጁ አካላት በተጨማሪ ከየማህበረሰቡ የተዋጣ ካሳም አስፈላጊ ነው። በአንድ አካባቢ የሚገኘው ሰፊ ብሔር በዉስጡ ለሚገኙ አናሳ ብሄሮች ለደረሱት ጥቃቶች ቀጥተኛ ተጠያቂ ባይሆንም እንደብዝሀነቱ በተፈላጊው ሁኔታ ጉዳቱን ባለመከላከሉ ማህበረሰቦችን ይበልጥ ከማቀራረብ አንፃር የተጎዱት ብሔሮች ይቅታ በመጠየቅ ተጎጂዎችን ሊክስ ይገባዋል። በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉትም የተለያዩ ግጭቶችም የብሄር መልክ የያዙ እንደመሆናቸውም መጠን ለሌሎች ነገሮችን እንዳልነበሩ አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ የተለያዩ ብሔሮች እርስ በእርስ ካሳ መከፋፈላቸው ለዘላቂ ሰላም መፍትሄ ይሆናል። 

በኢትዮጵያ ካሳ መክፈል ስነ ስርዓት ባህላዊ የዕርቅ ምልክት እንደመሆኑ መጠን የዚህ መተግበር ሀገሪቷን ወደሰላም ለመመለስ በሚደረጉ እርምጃዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የመንግስት የፍትህ አካላት ባልተጠናከሩበት ቦታዎች፣ ግጭቶች ወይም ሌሎች ወንጀሎች ሲፈፀሙ መፍተሄያቸውን የሚያገኙት በባህላዊ መንገዶች ነው። እነዚህ የባህላዊ መፍትሄዎች ትኩረታቸው አጥፊዎቹን መቅጣት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ ማህበረሰቡን ወደቀደመ ሰላም መመለስ ላይ ነው። ለዚህም እንደመፍትሄ አማራጭ የሚወሰደው ተጣልተው የነበሩትን አካላት ማቀራረብና ማስታረቅ ነው። አጥፊ ተብሎ የተፈረጀው አካል ለእርቁ የሚከፍለው ካሳ ይኖራል። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችም የካሳ አይነቱ ቢለያይም፣ ይህ የባህላዊ የእርቅ መንገድ በሰፊው ሲተገበሩ ይታያል። ካሳ የአካባቢው ማህበረሰብ በተሰበሰበበት ቦታ ከተከፈለ በኃላ የተጎዳው አካል ከእንግዲህ ወዲህ ቁርሾ ይዞ እንደማያጠቃ ቃል ገብቶ፣ ሁለቱ አካላት እንደ ታረቁ ለህበረተሰቡ ተነግሮ ስነ ስርዓቱ ይፈፀማል። ታዲያ በኢትዮጵያ ሊደረጉ የታሰቡ ሰላማዊ ድርድሮች በህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የተፈጠሩ መቃረኖች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአጠቃላዩን ህበረተሰብ አመኔታ ያገኘ መሆን ይገባዋል። ለእነዚህም ሰላማዊ ድርድሮች ባህላዊ የሆነውን የካሳ አከፋፈል ስነስርዓት ማካተት ይኖርባቸዋል።

ይሁን እንጂ ከላይ የተዘረዙት የመፍትሔ ሃሳቦች ብቻቸውን በቂ ይሆናሉ ማለት አይደለም። መንግስት አጥፊ ብሎ ያመናቸውን ወንጀለኞች ህግና ስርዓት በጠበቀ መልኩ ወደህግ ማቅረብም ይኖርበታል። በተለያዩ ግጭቶች የወደሙ መሰረተ-ልማቶችና መልሶ መገንባት፤ በተለያየ ሁኔታ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀያአቸው መመለስ፤ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ በርካታ የታጠቁ ቡድኖችንም ትጥቅ ማስፈታት አሊያም ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር የማዋሃድ ስራ የሰላምና የእርቅ ሂደቶቹን ዉጤታማ ለማድረግ ትልቅ ሚና አላቸዉ። እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች ግን ለብቻቸው በቂ ናቸው ብሎ ፀሀፊው አያምንም። በዚህ አንቀፅ የተዘረዘሩትም ድርጊቶችም የተለያዩ ዓላማ ያላቸው ናቸው። ፀሀፊውም ከላይ ያነሳው ሃሳቦች ዓላማቸው በህብረተሰብ መካከል ሊፈጠር የሚችልን ቀጣይነት ያለው የጠላትነት ስሜቶች እንዳይፈጠር ከመከላከል አንፃር የታሰቡ ናቸው። በዚህ አኳያም በማህበረሰብ አመለካከትና አስተያየት ላይ የደረሱ ጉዳቶች ትኩረት ለመስጠት ያህል፣ በኢትዮጵያ ለደረሱ ለተለያዩ ጉዳቶች ዕውቅና መስጠት፣ ይቅርታ መጠየቅና ካሳ መክፈል መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች ናቸው።

በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ መንግስት ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ የሚያደርገው ሂደት በራሱ ሰለምና መረጋጋት ለመፍጠር በቂ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህን እርምጃ ለብቻው መውሰድ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ይበልጥ ሊያወሳስበዉ ይችላል። ለዚህ ምክንያት የሚሆነው በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱት የተለያዩ ችግሮች አንድ ቡድን በሙሉው ሃላፊነት የሚወስድ አይደለም። በአንድም ቢሆነ በሌላ መልኩ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላት፣ የመንግስት አካላት፣ የተደራጁ ቡድኖች በችግሮቹ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ አካላት አንዱን ብቻ ነጥሎ ለፍርድ ማቅረብ ችግሩን ከመፍታት አኳያ ብዙ እርምጃ የሚያስኬድ አይደለም። የፍትህ አካላት ተዓማኒነታቸውን በከፍተኛ መልኩ የሚጎዳ እርምጃም ነው። የፍርድ እርምጃዎች አጥፊን ለይቶ ከመቅጣት በዘለለ ሌላ ሚና አይኖራቸውም። በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ደግሞ መጠነ ሰፊ የእርቅ እርመጃዎች ሊወሰዱ ይገባል። ይህም ደግሞ ከፍርድ ሂደት ውጪ ሌላ መፍትሔ ያሻል።

በተጨማሪም በተከሰቱት የተለያዩ ችግሮች የነበረው የተሳታፊነት አይነት በተናጠልና በጋራ የተፈፀሙ መሆናቸው ነው። የተለያዩ የፍርድ አካላት ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚችሉት ግለሰቦችን ብቻ ነው። በጋራ የተፈፀሙት ጥፋቶች መፍትሄ የማያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል። በእነዚህ ምክንያቶች ወንጀለኞችን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ ተጎጂዎችን ያማከለ የካሳ መክፈል ስነስርዓቶች፣ የባህል እሴቶች እንደመሆናቸውም ጭምር ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

ካሳ የመክፈል ስነስርዓቶች በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላል። ለምሳሌ የካሳዉ መጠን ስንት ይሁን፣ በምን አይነት መንገድ ይከፈል፣ ተከፋይ ወገኖች እንዴት ይለዩ፣ የመንግስትና የህበረተሰቡ አቅም ያገናዘበ ነው ወይ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላል። የካሳ ተከፋዮችም ተጎጂዎችም እንደግለሰቦች በመቁጠር ብቻ መሆን አለባቸው ብሎ ፀሃፊውም አያምንም። ተጎጂዎች እንደጋራም መካስ ይኖርባቸዋል። ይህም በራሱ ሌሎች ጥያቄዎች ያስነሳል። የፀሀፊውም ዓላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሙሉ መልስ መሰስጠት አይደለም። በራሳቸው ሰፊ ምርምር የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። በሌሎች ሀገራት የካሳ ክፍያዎች በግጭት ለተጎዱ ሰዎች የሚከፈሉበት አግባብ አለ። ከእነዚህ ሀገራት ልምድ የሚጠይቅ ጉዳይም ይሆናል። የነዚህ እርምጃዎች ስኬት የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ፈቃደኝነት የሚጠይቁም ናቸው፣ ምክንያቱም እነዚህ ካሳዎች ህጋዊ ሳይሆኑ ፖለቲካዊ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ውስንነቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ካሳዎችን ለእርቅ መጠቀም ዘላቂ መፍትሔ ነው ተብሎ ፀሀፊው ያምናል።

አስተያየት