ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል የጀበና ቡና አንዱ ነው። የጀበና ቡና ቤት ከማሞቅ የመንደርተኛን ማኅበራዊ ትስስር ከማጠናከር አልፎ አደባባይ ከወጣ ጥቂት ሰንበትበት ብሏል። በርካታ ሰዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች፣ ዋና ዋና አውራጎዳናዎች፣ በገበያ ስፍራዎች፣ በመዝናኛ ማእከላት፣ በትልልቅ ሞሎች እና ገበያ ማዕከላት በርካታ የጀበና ቡና አቅራቢዎች እና ተጠቃሚዎች አሉ።
በጎንደር ከተማም እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ በግለሰቦች የሚዘጋጁ የጀበና ቡና አቅርቦቶች በብዛት ይገኛሉ። በርከት ያሉ የጀበና ቡና አቅራቢዎች ከሚገኙባቸው የከተማዋ አካባቢዎች መካከል አራዳ፣ ማራኪ፣ እና አዘዞ ከፍለ ከተሞች ይጠቀሳሉ።
ነባሩን ባህላዊ የቡና አፈላል ሂደት ተከትሎ እየተሰናዳ የሚቀርበው፣ በአብዛኛው ተጠቃሚ የሚወደደው የጀበና ቡና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሌላ እየተተካ ይመስላል።
ጃንተከል ዋርካ ስር የጀበና ቡና ሲጠጣ ያገኘውነው አቶ ሳምሶን ቢንያም ነዋሪነቱ ካናዳ ነው። ለ5 ዓመታት ካናዳ የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ለ3ኛ ጊዜ ነው። ለእረፍት በተገኘባት ጎንደር የጀበና ቡና ማግኘት እንደ ከዚህ በፊቱ ቀላል እንዳልሆነለት ይናገራል። በቀደመው ጉብኝቱ ከቤተ-መንግሥታቱ በተጨማሪ በየአካባቢው የሚገኙት የጀበና ቡና መሸጫዎች ያዝናኑት እንደነበረ አንስቶ አሁን በቁጥር ቢጨምሩም አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ሲሊንደር “ሞካ ፖት” መጠቀማቸው ቅር እንዳሰኘው ነግሮናል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ አምሳሉ ቢያድግልኝም በሐሳቡ ይስማማል። “በባህላዊው የሸክላ ጀበና የሚፈላው ቡና ጣእሙ ብቻ ሳይሆን ስነ-ስርአቱም ልንተወው የማይገባ የባህላችን አካል ነው” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል።
“አሁን እንደ ድሮ በየአካባቢው የጀበና ቡና የለም። በብዛት የማየው በአነስተኛ ሲሊንደር የሚያፈሉትን ነው” ብሏል። በሲሊንደር የሚፈላው ቡና የጀበናውን ያህል ጣእም እና እርካታ ስለማይሰጠው በባህላዊ መንገድ የሚያፈሉትን ይመርጣል። “እንኳን ጣዕሙ ሽታው ይለያል። በሌሎች ነገሮች ባይተካ ጥሩ ነው። እንደ ጎንደር ያሉ በርካታ ቅርሶች ያሉባቸውና ጎብኚዎች የሚመርጧቸው ከተሞች ሲሆኑ ደግሞ ባህልንም ማስተዋወቅ ነው” ሲል ሐሳቡን ይደመድማል።
አልማዝ ጌታቸው በጎንደር ከተማ ከማራኪ ወደ ፒያሳ በሚወስደው ዋና አስፓልት መንገድ ዳር ቡና ከሚሸጡ ሴቶች መካከል አንዷ ነች። በሥራው ላይ ከሦስት ዓመታት በላይ ቆይታለች። ከ6 ወራት በፊት ጀምሮ በጀበና ማፍላቷን ትታ አነስተኛዋን ተንቀሳቃሽ ሲሊንደር መጠቀም መጀመሯን ነግራናለች።
አነስተኛዋን ሲሊንደር የመረጠችበት ምክንያት ስትናገር “ጊዜ ይቆጥባል። ደንበኞቻችን ቡናው እስከሚፈላ የሚጠብቁትን ሰዓት ያሳጥርላቸዋል። በዚህም ደስተኞች ናቸው” ያለች ሲሆን ጥቂት የማይባሉ ተጠቃሚዎች የቡናው ጣእም የጀበናውን ያህል አይሆንልንም የሚል ቅሬታ ቢያሰሙም ሥራዋን ስላቀላጠፈላት ምርጫዋ ሆኗል። አልማዝ በተጨማሪም “አሁን ጀበናውን የምንጠቀምበት ለማቅረብ ብቻ ነው” ብላናለች።
በተመሳሳይ የሥራ መስክ የተሰማራችው ሌላዋ አስተያየት ሰጪአችን ገነት አስማረ ትባላለች። የሥራ ቦታዋ አዘዞ ክፍለ ከተማ ነው። የአነስተኛዋ ሲሊንደር ቡና ከባህላዊው ቡና የበለጠ ጣዕም እንዳለው ታምናለች። እንደ ገነት ገለጻ፣ “የቡናውን አተላ ጨምቆ ስለሚለየው የበለጠ እርካታ ይሰጣል።”
በ1933 በየመን ሞቻ ከተማ የተሰየመው “ሞካ ፖት” ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጋሎት ላይ የዋለችው በጣሊያናዊው ኢንጅነር አልፎንሶ ቢያሌቲ ነው። በኤሌትሪክ ወይም ያለኤሌትሪክ አለግልሎት ትሰጣለች። የ”ሞካ ፖት” ተወዳጅነት ከጣልያን ሐገር አልፎ በአውሮፓ እና በላቲን አሜሪካም ተዳርሷል።
በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በመላው ደቡብ አውሮፓ የንድፉ ተቀባይነት ጨምሯል። ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ አውስትራልያን የረገጡ ጣልያናውያን ስደተኞች ወደ አውስትራልያ እንዳስገቡት ይገመታል። ከ2000 (እ.ኤ.አ) በኋላ በበርካታ አውስትራልያውያን ዘንድ ታዋቂ ሆነ።
አምራቾች አዳዲስ ንድፎችን በነባሩ የኢንጅነር አልፎሳ ዲዛይን ውስጥ እያካተቱ መስራት ጀመሩ። ይህ አላሄድ አሁን እስካለንበት ጊዜ ቀጥሏል።
በአንድ ጊዜ እስከ 18 ሲኒ ቡና ማፍላት የሚያስችለው “ሞካ ፖት” በበርካታ ሙዚየሞች ውስጥ ይገኛል። የለንደን ሳይንስ ሙዚየምን ጨምሮ በዘመናዊ የኢንዱስትሪ ዲዛይን ሙዚየሞች፣ በንድፍ ዲዛይን ሙዚየሞች እና በሌሎችም የቴክኖሎጂ እና የዲዛይን ታሪክ እና አመጣጥን በሚያሳዩ አውደ ርዕዮች በዓለም ዙርያ በመጎብኘት ላይ ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜ ከማይዝግ ብረት እና ከአሉሚንየም የተሰሩ ሲሆኑ እጀታቸው ፕላስቲክ ወይም እንጨት ይሆናል።
የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት መሪ አቶ ልዕልና አበበ “ሁሉም ቡና በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎች ሥራቸውን በሸክላው ጀበና እንዲያፈሉ ለማድረግ እየሰራን ነው” ብለዋል። ቢሯቸው የሸክላ ጀበናዎች እንዳይጠፉ የእደ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማደራጀት በሰፊው ገበያውን እንዲቀላቀሉ ማድረጉን አንስተዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ገበያውን የተቀላቀለችው አነስተኛዋን ሲሊንደር በተመለከተ ባህላዊ የቡና አፈላሉን ሊጎዳው እንደሚችል በማሳወቅ ምክረ-ሐሳብ ከመስጠት ያለፈ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ሕጋዊ ማእቀፍ እንደሌለ ሰምተናል።