የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም ከጤና ጋር በተያያዘ ላለፈው አንድ ዓመት የተቸገሩ መሆኑን ለባልደረቦቻቸው በላኩት መልዕክት ገልፀዋል። ያለፉትን አምስት ወራትም በሀገረ አሜሪካ በህክምና ላይ ሆነው ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመገናኘት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዉ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በጤናቸው ላይ ሙሉ ትኩረት ማድረግ ስለፈለጉ በቦታው መገኘትንና ትኩረት የሚጠይቀውን የአየር መንገዱን የአመራር ሂደት ማስቀጠል እንደማይችሉ ለአየር መንገዱ የአመራር ቦርድ አሳውቀዉ ከሀላፊነታቸዉ ለቀዋል።
በዚህም ምክንያት ያቀረቡት የቅድመ ጡረታ ጥያቄ በእዛው እለት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ማኔጅመንት ተቀባይነት አግኝቶ መስፍን ጣሰዉ እሳቸዉን ተክተዉ እንዲሰሩ በቦርዱ ተሹመዋል።
ተወልደ በአየር መንገዱ በነበራቸዉ የስራ ቆይታ በርካታ ፈታኝ ወቅቶችን በስኬት ያለፉ፤ አየር መንገዱ በአፍሪካና በአለም ደረጃ ያለዉን ተቀባይነት እንዲጨምር በግልጽ የሚታይ ጠንካራ አመራር የሰጡ መሪ ነበሩ። ተወልደን በቅርብ የሚያቋቸዉ ታታሪነታቸዉንና ለስራ ዲሲፕሊን ያላቸዉን ትጋት ያደንቃሉ።
በአየር መንገዱ ያገለገሉ አንዳንዶች ደግሞ ተወልደ የሽያጭ ዘርፍ ላይ እንደቆየ ባለሙያ በተቋሙ የሽያጭ ስራ ላይ አበርክቶ ቢኖረውም፤ ሙያና ክህሎትን መሰረት ያላደረጉ ውሳኔዎች የማሳለፍ አልፎ አልፎም ፈላጭ ቆራጭነት ይታይበት ነበር ሲሉ ይወቅሱታል። ከዚህ አለፍ ሲልም ሰራተኞች እድገት ወይም ወደሌላ ዘርፍ ምደባ የሚያገኙት ለተወልደ ባላቸው ቅርበትና ከስራዉ ጋር በማይገናኙ መመዘኛዎች የሆኑበት ጊዜ መኖሩን ይናገራሉ።
ተወልደ ገብረማርያም በትግራይ ክልል ከዛላምበሳ 5 ኪሎ ሜትር ያህል ራቅ ብላ በምትገኘው አጋመ አውራጃ መወለዳቸውን ታሪካቸው ያሳያል። ተወልደን ጨምሮ ዘጠኝ ልጆች ካሉበት የወላጆቹ ቤት ብቻቸውን የሚኖሩት አያቱ አንድ ልጅ ከእርሳቸው ጋር እንዲሆን በመፈለጋቸው ተወልደ ዛላምበሳ ወደሚገኘው የአያቱ ቤት ሄዶ ኑሮውን ከእሳቸው ጋር አደረገ።
የቀለም ትምህርቱንም ስምንተኛ ክፍል እስከሚደርስ አያቱ ቤት ሆኖ በዛላምበሳ አውራጃ ተከታትሏል። ወቅቱ የደርግ እና ሕወሓት ጦርነት የነበረበት በመሆኑ አስቸጋሪ ነበር። ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልን ለመማር 35 ኪሎ ሜትሮችን በእግር ጉዞ አቋርጦ በየሳምንቱ ወደ አዲግራት መጓዝ የግድ ቢሆንበትም ጉዞውን ከመቀጠል አላገደውም።
የጦርነቱ ሁኔታ እየተባበሰ ሲሄድ ተወልደም የትምህርት ደረጃው ከፍ እያለ በመሄዱ የ11ኛና 12ኛ ከፍል ትምህርቱን ለመከታተል በነበረው ፍላጎት ለ10 ቀናት እያቆራረጠ ተጉዞ አዲስ አበባ ከሚኖረው አጎቱ በመከተም በቀድሞ አጠራሩ ተፈሪ መኮንን አሁን እንጦጦ ተብሎ በሚጠራው ተማሪ ቤት ገባ።
ማህበራዊ ሳይንስ የተማሩት ተወልደ፤ የዩኒቨርሲቲ ምደባ ሲገለፅላቸው የህክምና ሳይንስ ተመድበው ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ቢሆንም ፍላጎቴ ማህበራዊ ሳይንስ ማጥናት ነው በማለት ወደ ስድስት ኪሎ አስቀይረው በአካውንቲንግ ስልጠና ዲፕሎማ ለማግኘት ተቃረቡ።
በእዚህ ወቅት ግን ብሔራዊ ውትድርና የሚባል ፈተና ቀደማቸውና ወጣቶች ለውትድርና እንዲመዘገቡ የሚጠይቅ ጥሪ ቤታቸው ገባ። በአንድ በኩል መመረቂያቸው እየደረሰ መሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መቅረት የማይቻልበት ውትድርና ተወልደንና ቤተሰቦቹን አጨናነቀ።
ለብሔራዊ ውትድርና ተመዝግበው መስፈርቶችን አልፈው የምልምል ወታደር መታወቂያ ሲሰጣቸው ተስፋ በመቁረጥ ስሜት መምህራኖቹን ለመሰናበት ወደ ተፈሪ መኮንን የሙያ ኮሌጅ ሄደ። ርዕሰ መምህሩ ጋር ሲገባ ግን የብስራት ዜና ተነገረው። ርዕሰ መምህሩ “የመጨረሻ ዓመት የሙያ ተመራቂ ተማሪዎች የብሔራዊ ውትድርና ጥሪ እንደማይመለክታቸው በአዋጅ ተቀምጧል” ብለው ለተወልደ ቢነግሩትም ለጉዞ 2 ቀናት መቅረቱ ሌላ ሀሳብ ሆነበት።
ተወልደን በትምህርቱ የላቀ ደረጃ ላይ መመልከት የሚፈልጉት ርዕሰ መምህሩ ለቀበሌ ደብዳቤ ፅፈውለት ከብሔራዊ ውትድርና እንዲቀር ሆነ። ነገር ግን ከምርቃቱ በኋላ ሁለተኛ ዙር የብሔራዊ ውትድርና ጥሪ በድጋሜ እነ ተወልደ ቤት ገባ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመዝግቦ የነበረው ተወልደም ለብሔራዊ ውትድርናው ካልመጣ በሚል ቤተሰቦቹ ሲታሰሩ ከዩኒቨርሲቲው ወጥቶ የውትድርና ምልመላውን ሂደት ጀመረ። አሁንም ሌላ እድል፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማርኬቲንግ ዘርፍ አሰልጥኖ መቅጠር ይፈልጋል” የሚል የስራ ማስታወቂያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተመለከተ፤ ለመመዝገብ ሁለቴ ማሰብ አላስፈልገውም።
በመቀጠል የአየር መንገዱን ስልጠና እየወሰደ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመረ። የአየር መንገዱን የአንድ ዓመት ስልጠና ከወሰደ በኋላ ወደ ጭነት (ካርጎ) ክፍል ለስራ ተመደቦ በቀን ለ14 ሰዓታት በስራ በማሳለፍ ለሰባት ዓመታት ቆየ። ከስራው ጎን የሚማረው የኢኮኖሚክስ ትምህርታቸውን በመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀቁ። ተወልደ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽንም ተቀብለዋል።
ለሰባት ዓመታት ከቆየበት የጭነት አገልግሎት ክፍል ወደ መንገደኛ አገልግሎት ስራ ተመደበ። ተወልደ እና ባልደረቦቹ እንደአሁኑ ዘመናዊ አሰራር ሳይኖር አውሮፕላን በር ላይ ቆመው የመንገደኞችን ክፍያ እየሰበሰቡ ወስደው ባንክ ማስረከብም ሰርተዋል።
ህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ሲንጋፖር፣ ስሪላንካ እና ታይላንድን የሚያካትት የስራ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በስራ ቆይተዋል። በመቀጠል ሳኡዲ አረቢያ ለሁለት ዓመታት ሲቆዩ የባህል ልዩነት መኖሩ አስቸጋሪ ቢሆንም በቆይታቸውም ደስተኛ እንደሆኑ ይገልፃሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪኩ ረጅሙን በረራ የጀመረበት አሜሪካ ሀገርን ተደራሽ ለማድረግ ሲታሰብ ፕሮጀክቱን ለመከታተል አራት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ሲመረጡ ተወልድ ገብረማርያም አንዱ ሆነው ወደ ኒው ዮርክ አቀኑ።
በኒው ዮርክ ከተማ መንታዎቹ ህንፃዎች ላይ የ9/11 (ናይን ኢለቨን) ጥቃት በደረሰበት ወቅት ክስተቱን ከቢሯቸው ሆነው ተከታትለዋል። ከጥቃቱ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ የሚያደርገው በረራ ወደ ዋሽንግተን እንዲሆን በማድረግ አገልግሎታቸውን ቀጥለው አቶ ተወልድ በጥቅሉ ለሰባት ዓመታት በአሜሪካ ቆዩ።
በነሐሴ ወር 1996 ዓ.ም. አየር መንገዱ አዲስ የአመራር ቦርድ በሚያዋቅርበት ጊዜ የተወልደ የመጀመሪያ የበላይ አለቃው የነበሩት አቶ ግርማ ዋቄ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆኑ፤ አቶ ተወልደም ከአሜሪካ ተጠርተው የአየር መንገዱ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። በማኔጅመንት ስብሰባቸው የአየር መንገዱን እድገት ማሻሻል ችለዋል።
አየር መንገዱ ለስራ በሚጠቀመው የአውሮፓውያን የዘመን ቀመር እስከ 2010 ዓ.ም. የተቋሙን ዓመታዊ ገቢ 1 ቢልየን ዶላር ማድረስ ሲሆን በእቅዱ ማብቂያ የአየር መንገዱ ገቢ 1.3 ቢልየን ዶላር ማድረስ ችለዋል። በቀጣዩ ዓመት በአቶ ግርማ ዋቄ ለቦርዱ አቅራቢነት አቶ ተወልደ ገብረማርያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው በቀጣዩ ዓመት ተመረጡ።
አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ስራ አስፈፃሚነት ባስተዳደሩበት 11 አመታት ለአየር መንገዱ እና ለአመራር ብቃታቸው በርካታ እውቅና አግኝተዋል፤ እውቅናም ብቻ ሳይሆን በዓይን የሚታይ ለውጥ ማምጣት ችለዋል። ወደ ዋና ስራ አስፈፃሚነት ኃላፊነት በመጡበት ወቅት የአየር መንገዱ ዓመታዊ ገቢ አንድ ቢልየን ዶላር የነበረ ሲሆን ባለፉት 11 ዓመታት ወደ 4.5 ቢልየን ዶላር አመታዊ ገቢ ማደግ ችሏል።
33 አውሮፕላኖች የነበሩት አየር መንገዱ አሁን በ130 አውሮፕላኖች እየሰራ ይገኛል፣ ከኮቪድ19 ወረርሺኝ መከሰት በፊት 3 ሚልየን መንገደኛ በዓመት ከማጓጓዝ ወደ 12 ሚልየን መንገደኛ ከፍ ማለት ከስኬቶቹ መካከል ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚገልፀው በሌሎች የመለክያ ዘርፎች ታይቶ የተወልደ የስራ አስፈፃሚነት ዘመን አራት እጥፍ አስደናቂ እድገት ለማስመዝገብ ተችሏል።
በተጨማሪም አየር መንገዱ የአፍሪካ ትልቁን ሆቴል፣ የእቃ ጭነት ተርሚናል፣ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የአቪዬሽን ትምህርት ማዕከልን እና ሙሉ ምስለ በረራን ጨምሮ ከ700 ሚልየን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው መሰረተ-ልማት ባለቤት በሆነበት ሂደት የአቶ ተወልደ ሚና ከፍተኛ ነበር።
ተወልደ ከ37 ዓመታት የአየር መንገድ ቆይታ በኋላ ስራውን ለቋል። አሁንም 38 ዓመታት በአየር መንገዱ የተላያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት መስፍን ጣሰው ተወልደን ተክተዋል። ታዲያ የአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ተጠናክረው ይቀጥሉ ይሆን የሚለው ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ይሆናል።