ግንቦት 3 ፣ 2015

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ የተሰጠው ኤም-ፔሳ ማን ነው?

City: Addis Ababaቴክኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 150 ሚልየን ዶላር የከፈለበትን የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት 10 ሚልየን ደንበኛ ለመድረስ አቅዷል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ የተሰጠው ኤም-ፔሳ ማን ነው?

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ሆኖ የገባው ሳፋሪኮም ቴሌኮምኒኬሽን ኩባንያ በሞባይል ገንዘብ የማዘዋወሪያ አገልግሎቱም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የውጭ ድርጅት ሆኗል።

ኤም ፔሳ ወይም የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደስራ እንዲገባ ከዛሬ ግንቦት 3፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ ተሰጥቶታል። ሳፋሪኮም ይህንን የአገልግሎት ፈቃድ ከኢትዮጵያ መንግስት ለማግኘት 150 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር የከፈሉ ሲሆን የኩባንያው ዋአ ስራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ በቅርብ ሳምንታት አልያም ወር ውስጥ ኤም ፔሳ በኢትዮጵያ ስራውን እንደሚጀምር በዛሬው እለት ዓመታዊ ሪፖርት ሲያቀርቡ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ግዙፍ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) ተቋም የሆነው ኤም ፔሳ ከ5 ሚልየን በላይ ተጠቃሚዎችን ከ10 በሚበልጡ ሀገራት ማፍራት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ ወደሆነችው ኢትዮጵያ ደርሷል። በሳፋሪኮም ኤም ፔሳ የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወሪያ በዓመት ከ314 ሚልየን ዶላር በላይ ይንቀሳቀሳል።

ኤም-ፔሳ ምንድን ነው?

ኤም የሚለው ሞባይል የሚለውን ለመግለፅ ሲሆን ፔሳ ማለት በስዋሂሊ ቋንቋ ገንዘብ ወይም ክፍያ ማለት ነው። ኤም-ፔሳ በኬንያ ሳፋሪኮም እና በደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም የሚተዳደር የፋይናንስ አገልግሎት መስጫ ሲሆን በታንዛኒያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ፣ ጋና እና ግብፅን ጨምሮ በ12 የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ በ3 ሀገራት ውስጥ ይሰራል። 

ኤም-ፔሳ የሞባይል ገንዘብ ክፍያዎች እና የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 በቮዳፎን (የደቡብ አፍሪካ) እና ሳፋሪኮም (የኬንያ) ኩባንያዎች የተጀመረ ሲሆን ቀጠናዊ ትስስርን የሚያበረታታ ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያቀርብ አገልግሎት ነው።

ገንዘብ ተቀባዮች በሃገራቸው ምንዛሬ ገንዘብ እንዲቀበሉ የሚያስችላቸው የገንዘብ መላክ እና መቀበል አገልግሎቶችን በእነዚህ ሀገራት ያቀርባል። አንድ በኢትዮጵያ ወይም ኬንያ የሚገኝ የኤም ፔሳ ደንበኛ በሩዋንዳ ላሉ የንግድ አጋሮች ገንዘብ መላክ፣ ኮሌጅ ላሉ ልጆቻቸው ወደ ኡጋንዳ የኪስ ገንዘብ መላክ፣ ታንዛኒያ ውስጥ ላሉ ቤተሰብ ገንዘብ መላክ ወይም በኬንያ ላሉ አገልግሎት አቅራቢዎች ስልክን በመጠቀም ገንዘብ መላክ ያስችላል።

ኤም ፔሳ በሲም ካርድ የግብይት አገልግሎቶችን የሚሰጥ ዘመናዊ የባንክ ሥርዓት ሲሆን አንድ ጊዜ ሲም ካርድ በተንቀሳቃሽ ስልክ ውስጥ ከገባ በኋላ ተጠቃሚዎች ክፍያ መፈፀም እና በአጭር የፅሁፍ መልእክት ለደንበኞች እና ለቤተሰብ ገንዘብ ማስተላለፍ ይችላሉ።

የባንክ አካውንት የሌላቸው ተጠቃሚዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ኤም ፔሳ ገንዘብ ወጪ፣ ገቢ እና ተቀማጭ ማድረግ የሚቻል ሲሆን በወኪሎች አማካኝነት አገልግሎቶቹን ያቀርባል። 

በአሁኑ ሰዓት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 2 ሚልየን የድምፅ ደንበኞች ያሉት ሲሆን 1.4 ሚልየን የሚሆኑት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በኢትዮጵያ አሁን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው 22 ከተማዎች በአጠቃላይ 13.1 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝቷል። 

ኤም-ፔሳ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲጀምር መፈቀዱን ያበሰሩት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ፣ በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 10 ሚልየን ደንበኞች ጋር እንደሚደርስ እቅድ ተይዟል ብለዋል።ኤም-ፔሳ በኢቲዮቴሌኮም አማካኝነት በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማራውና ከሀያ ሚሊዮን በላይ ተመዝጋቢዎች ካሉት ቴሌብር እና ሌሎች ሀገር በቀል አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ብርቱ የገበያ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 


 

አስተያየት