ዓለማችን በርካታ መጠሪያ ስሞችን አድምጣለች። ያደረጉት አስተዋፅኦ ማህበረሰብን፣ ግዛቶችን እና ሃገራትን የለወጡ ስሞችን። በጣም ጥቂቶች ደግሞ ሃገራቸው አልፈው በርካታ ሃገራትን የያዙ ክልሎችን በመለወጥ ብሎም ለመላው የሰው ዘር አስተዋጽኦ በማርከት ስማቸውን በወርቃማ ብእር ከትበዋል። ዛሬ እ.ኤ.አ ሜይ 10፣ 2023 አዲስ አበባ የሚገኘው የአዛርባጃን ኤምባሲ 100ኛ የልደት በዓሉን ማስታዎሻ በስድስት ኪሎው የኢንተርናሽናል ሊደርሸፕ ኢንስቲትዩት ጊቢ ውስጥ እያከበረለት የሚገኘው የአዛርባጃን የቀድሞ ፕሬዝዳንትና ብሄራዊ ጀግና ሃይደር አልየቭ ከነዚህኞቹ መካከል ይመደባል።
ሜይ 10 1923 ናክቺቫን በተባለው የአዛርባጃን ግዛት የተወለዱት ሃይደር አሊርዛ ኦጉል አሊየቭ ሃገሪቱን ከ1993ቱ የውድቀት አፋፍ መልሰው ራሷን የቻለችና የበለጸገች ሃገር እንድትሆን ያስቻሉ ትልቅ ፖለቲከኛና ሃገር ወዳድ መሪ ነበሩ። አዛርባጃናውያን ሃይደር አሊየቭን እኤአ ከ1969 እስከ 1982 ዓም የቀድሞዋን አዛርባጃን ሪፐብሊክ ሲያስተዳድሩና ሃገሪቱን ከኋላቀር የግብርና ወደ ገዙፍ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት ሲቀይሯት ጀምሮ ጠንቅቀው ያውቋቸው ነበር። ሃይደር አሊየቭ አዛርባጃንኛ ከራሽያኛ ጋር በህገ መንግስት እንዲካተት አድርጓዋል።
ከ1982 እስከ 1987 በሞስኮ ውስጥ የዩኤስኤስ አር የፖሊት ቢሮ አባል እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ምክትል ሊቀመንበር በነበረበት ወቅት የአዘርባይጃን ህዝብ ከፍተኛ ድምጽ አገልግለዋል፡፡ በበ1987 የዩኤስኤስአር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ምክትል ሊቀመንበር እና የኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ቢሮ አባል በመሆን ቁልፍ ቦታቸውን ለቀው ነበር። በጥር 1990 በአዘርባጃን ዘመናዊ ታሪክ ጥቁር ጃንዋሪ ተብሎ ከተጻፈው ጥር 20 ቀን ደም አፋሳሽ አደጋ ጋር በተያያዘ በአዘርባጃን ህዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ፍትህን፣ በአዘጋጆች እና አጥፊዎች ላይ ቅጣት እንዲቀጣ እስከመጠየቅም ደርሰው ነበር።
ህዝቡ ከጁን 1993 ሀገሪቱ ውድቀት ላይ በነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ሃይደር አሊዬቭ የሀገሪቱን የመሪነት ቦታ እንዲወስዱ ያለማቋረጥ ጠየቁ። ኦክቶበር 3, 1993 በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ድምጸ ውሳኔ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ። አዘርባጃን በብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ፈተናዎች ፣ የአርሜኒያ ወታደራዊ ጥቃት በህገ-ወጥ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎች፣ በአገር ውስጥ ህገ-ወጥ የታጠቁ እና የወንጀል ቡድኖች፣ እንዲሁም በደካማ አስተዳደር ምክንያት እየተፈተነች በነበረችበት ሰዓት ነበር ፕረዝዳንቱ ስልጣን የተረከቡት። አዘርባጃን ወደ ብልጽግና፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሳይንሳዊ እና ባህላዊ እድገቶች እንድትመራ የአስቻሉት ሃይዳር አሊዬቭ በእውቀት፣ ልምድ፣ አርቆ የማየት እይታ እና የአመራር ችሎቸውን በትክክልና በአግባቡ በመጠቀማቸው ነበር ይላሉ የአዛርባጃን የኤምባሲ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ሚር ሩስላን ናሲቦቭ።
"ብሄራዊ መሪያችን ብዙ አስደናቂ እቅዶችን እና ፖሊሲዎችን በመንደፍና በመተግበር፣ የአዘርባጃን ህዝብ በማስተባበር፣ አለምአቀፍ አጋሮችን በማሳተፍ እና የሀገሪቱን እምቅ ሀብቶች በመጠቀምና ለሰብአዊ ካፒታል ልማት ትኩረት በመስጠት ሃገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርገዋል’’ ብለዋል ሚስተር ሩስላን።
ሚስተር ሩስላን እንዳሉት ሃይዳር አሊዬቭ ቀሪው ዓለም አዘርባጃንን እንደ ታማኝ አጋር መመልከት እንዲጀምርም አስተዋጿቸው ላቅ ያለ ነው። በሴፕቴምበር 1994 የክፍለ ዘመኑን ውል በመፈራረም ለሃገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ደቡብ ካውካሰስ ክልል ታላቅነትም መሠረት ጥሏል። ሃይደር አሊዬቭ በታህሳስ 12 ቀን 2003 ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም በሳል ፖሊሲያቸው በአሁኑ የሃገሪቱ ፕረዝዳንት ኢልሃም አሊየቭ ቀጥሎ አዛርባጃን በብልጽግና ጎዳና ላይ ትገኛለች ብለዋል ሚር ሩስላን። የኩሩ ዜጎች መኖሪያ፣ የመድብለ ባህልና ስምምነት አርማ፣ የአለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል፣ የሆነችው አዛርባጃን የግዛት አንድነቷን እና ሉዓላዊነቷን ለሚያከብሩ መንግስታት ጥሩ ጎረቤት፣ ለቀጠናው ብልጽግና ደሞ አስተማማኝ መሰረት ሆና እንደምትቀጥል በሙሉ ልብ የሚናገሩት ሚር ሩስላን፣ ታማኝ እና ኃላፊነት የሚሰማው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባል ከዓለም ሀገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር ታደርጋለች ብለዋል።
“ውዷ ሀገራችንን ከአመድ ላይ በማንሳት ወደ ከፍታ የመሯትን፣ ከክልሉ ጠንካራ ግዛቶች ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጓትን፣ የግዛት አንድነት በማስጠበቅ ወደ ብልፅግና እና ሰላም ህይወት እንድናመራ መሰረት የጣሉላትን የታላቁን መሪያችንን 100ኛ ዓመት የልደት በዓል ስናከብር ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።