ሐምሌ 23 ፣ 2014

ጎርፍና ኩሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ...

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮችአስተያየት

በአንዳንድ የአዲስ አበባ ሰፈሮች እስከ ጉልበት የሚደርስ የጎዳና ላይ ጎርፍ ይከሰታል። ታዲያ ይህን የጎዳና ላይ 'ወንዝ' ለመሻገር እግረኞች ገንዘብ ከፍለው በሰው ጀርባ ላይ ታዝለው ሲሻገሩ ማየት አሳዛኝ ትዕይነት ነው።

Avatar: Assegid Gebeyehu
አሰግድ ገበየሁ

አሰግድ ገበየሁ በአዲስ ዘይቤ የአማርኛ ፅሑፎች አርታዒ ሲሆን በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ምሩቅ ነው።

ጎርፍና ኩሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ...
Camera Icon

ፎቶ፣ አሰግድ ገበየው (ከአዲስ ዘይቤ)

የክረምቱን መግባትና ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለአይን የበዙ ትእይንቶች ሞልተዋል። በየፌርማታው የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ከሚደረገው እልህ አስጨራሽ ሰልፍና ግፊያ እስከ ጎዳና ላይ ንግድ ድረስ በአስገራሚና በአሳዛኝ ሁነት የተሞላ ነው።

በአራቱም የከተማዋ ጫፍ መሃሉን ጨምሮ እየተገነባች ባለችው አዲስ አበባ፤ በርዝመታቸው የሚፎካከሩ ከሚመስሉት ህንጻዎች እና ሁሌ አዲስ በሆነ የመንገድ ግንባታ ከተማዋ መልከ ብዙ ሆናለች። በክረምት ወራት በተለይም ከስራ መውጫ ሰዓት እስከ ምሽት ባለው ጊዜ ላፍታ ቆም ብለን ብንታዘብ የአፍሪካ መዲናዋ ሸገር ሌላ ገጽታ ይዛ ትልቅ የገበያ ስፍራ ትመስላለች።  

በክረምት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዳር ዳሩን በእሸት በቆሎ እና በዣንጥላ ሽያጭ ይደምቃሉ። ታድያ የመንገዱ የመሐለኛ ክፍል ደግሞ 'ክረምት ሰራሽ' በሆነ ጎርፍና ኩሬ ይሞላል። አዲስ አበባ እንደ አቅሟ ውብና ፅዱ የሆኑ መንገዶች ቢኖሯትም በግንባታና በአጠቃቀም ጉድለት ለተደጋጋሚ ብልሽት ይዳረጉባታል። በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች የከተማዋ ዋና መንገዶች፣ የእግረኛ መተላለፊያዎች፣ አደባባዮች፣ ድልድዮች እና የፍሳሽ መውረጃ ቦዮች እድሜያቸው አጭር እየሆነ ነው።

በተለይ በቆሻሻ የተሞሉት የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቦዮች የክረምቱን ጎርፍ ማስተናገድ ተስኗቸው የያዙትን ፍሳሽ ከነግሳንግሱ በዋናው መንገድ ላይ ይለቁታል። ይህ እንደደራሽ ወንዝ መንገዱን የሚያጥለቀልቀው ጎርፍ የእግረኛውንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ከማስተጓጎሉም በላይ በሚሰነፍጥ መጥፎ ሽታው አካባቢውን ያዳርሳል። 

በአንዳንድ የአዲስ አበባ ሰፈሮች እስከ ጉልበት የሚደርስ የጎዳና ላይ ጎርፍ ይከሰታል። ታዲያ ይህን የጎዳና ላይ 'ወንዝ' ለመሻገር እግረኞች ገንዘብ ከፍለው በሰው ጀርባ ላይ በሸክም ሲሻገሩ ማየት አሳዛኝ ትዕይነት ነው። የዚህ አይነቱ አጋጣሚ ዝናብን ተከትሎ በጉርድ ሾላ፣ በካዛንቺስ፣ በበቅሎ ቤት ግሎባል ሆቴል አካባቢና በሳሪስ አቦ አካባቢዎች ይታያል። 

እዚህ ላይ ለመውረጃ ቦዮች መበላሽት ምክንያቱ ከግንባታ ጥራት ጉድለት በተጨማሪ ተጠቅመን እንደዘበት የጣልናቸው የውኃ መያዣ የፕላስቲካ ጠርሙሶችና መሰል ቆሻሻዎች መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በተጨማሪም በአግባቡ ባለመሰራታቸው ምክንያት ጠበው፣ ሳር በቅሎባቸው አንዳንዶቹም ተደፍነው ውኃ የማያስገቡ የፍሳሽ ቦዮች በየቦታው አሉ።

ፎቶ፣ አሰግድ ገበየው (ከአዲስ ዘይቤ)

በሌላ በኩል በመንገድ ግንባታ መጓተት ምክንያት ነዋሪዎችን ለረጅም ጊዜ በጎርፍና ጭቃ ካማረሩ እንዲሁም 'የጎዳና ላይ ኩሬ' ከሚታይባቸው ቦታዎች መካከል የቃሊቲ እና የኮተቤ የመንገድ ስራዎች ዋናዎቹ ናቸው። በተለይም ከሰባት አመታት በፊት ተጀምሮ እስካሁን ያልተጠናቀቀው የኮተቤው መንገድ ግንባታ፤ ከጭቃና ከጎርፍ ችግር አልፎ ብዙ የመኪና አደጋ አስከትሏል። በዚህም ከአካል ጉዳት እስከ ሞት ድረስ አሳዛኝ የመኪና አደጋ መድረሱ የነዋሪዎች አሳዛኝ ትውስታ ነው።

ከላምበረት፣ ኮተቤ ካራ ደረስ የሚዘልቀው ይህ የመንገድ ግንባታ አሁን ላይ የመንገዱ ስራ እየተጠናቀቀ ነው። ይሁንና አሁንም በኮተቤ ኮሌጅ፣ በወንድይራድ ት/ቤት እና ካራ አርሴማ ቤተ ክርስትያን አካባቢ ተቆርሰው የቀሩት መንገዶች እንኳንስ ለእግረኛ ለመኪኖችም ፈታኝ ናቸው።

በቅርቡ የተጀመሩት የቦሌ ሚካኤል እና የገርጂ ኢምፔሪያል የመንገድ ስራዎች እግረኛውን ለእንግልት ዳርገው መኪኖችን እየናጡ ይገኛሉ። ሌላው ተቆፍረው እንዲሁ ከቀሩት መንገዶች መካከል ደግሞ የካዛንቺስ ታክሲ ተራ፤ አፍንጮ በር እና ሳሪስ ብሔረ ፅጌ መንገዶች ይጠቀሳሉ።

ለመንገድ ጥገና፣ እድሳትና ማስፋፊያ ስራዎች በተጨማሪ ለመስመር ዝርጋታ ተብሎ የሚቆፈሩ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የፍሳሽ መውረጃ ቦዮች ነዋሪዎችን ሳያማርሩ ተሰርተው አይጠናቀቁም። አንዳንዴም ከረዥም ጊዜ መጓተት በኋላ ተሰርተው የተጠናቀቁ እና ተመርቀው ክፍት በሆኑ በወራት ጊዜ ውስጥ ተመልሰው የሚቆፈሩትን መንገዶች የመንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይቁጠራቸው። በዚህም ለሚባክነው ከፍተኛ የሀገር ሀብትና ጉልበት ተጠያቂ አለመኖሩ ደግሞ ነገሩን በእጅጉ አሳዛኝ ያደርገዋል።

ፎቶ፣ አሰግድ ገበየው (ከአዲስ ዘይቤ)

ቁጥሩ በፍጥነት እያሻቀበ ላለው የአዲስ አበባ ህዝብ በቂ የእግረኛ መንገድ ባለመኖሩ እግረኛው ህዝብ ከዋናው መንገድ መሃል ከመኪኖች ሲጓዝ ማየት ሆኗል። ሁኔታውን የሚያደርገው ደበከተማዋ በየእለቱ ሰዎች በትራፊክ አደጋ የመሞታቸው ዜና ሲነገር ነው። በመገናኛ፣ በሜክሲኮ፣ በፒያሳ፣ በቃሊቲ፣ በጦር ሀይሎች ተዟዙሮ ለተመለከተ ሰው፤ እንኳን የእግረኛ ዋናውም መንገድ በሰው ተሞልቶ አሽከርከሪዎች ለማለፍ ሲቸገሩ በማየት ግራ ሊጋባ ይችላል።

በቅርብ ወራት ውስጥ ተሰርቶ የተጠናቀቀው ከማዘጋጃ ቤት፣ በቸርችል ጎዳና፣ በብሔራዊ ትያትር አድርጎ ለገሐር የሚደርሰው የእግረኛ መንገድ ውብና ምቹ ሆኖ ተዘርግቷል። ከመንገዱ ስፋትና ጥራት በተጨማሪ በአበቦች እና በማረፊያ ወንበሮች የተሟላ ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በተቃራኒው ከላምበረት እስከ ካራ ድረስ ያለው የእግረኛ መንገድ ከአራት ወራት በፊት ተቆፋፍሮ እንዲሁ ቀርቷል። ከሶስት ኪ.ሜ በላይ የሚረዝመው ይህ ከላምበረት በወሰን ሰፈር ካራ የሚወስደው የእግረኛ መንገድ በቀኝም በግራም ረድፍ ለረዥም ጊዜ ሊያገለግል የሚችል የሸክላ ንጣፍ ነበረው። የሸክላውን ንጣፍ በማንሳት፣ መንገዱን በመቆፈርና አፈሩ በመቆለል ለጎርፍና ለጭቃ ተመቻችቶ ተቀምጧል። 

'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' እንደሚባለው ከተማዋን የህዝብ ቁጥር ሳያገናዝብ የተሰራውን ጠባብ የእግረኞች መተላለፊያ መንገድ በህንፃ ግንባታ ሰበብ ይዘጋል። በብዙ ቦታዎች ላይ ሀላፊነት የማይሰማቸው የህንፃ ገንቢዎች አሸዋ፣ ኮረት፣ ብረትና እንጨት በእግረኛ መንገድ ላይ በመከመር ህዝቡ ወደ መኪና መንገድ መሃል ገብቶ ለአደጋ እንዲጋለጥ ሲያደርጉ ይታያል።

ለአዲስ አበባ ጎዳናዎች ብልሽት የመንገዱ አሰራር ሌላኛው ምክንያት ሲሆን ይታያል። በዚህም መንገዱ የታሰበለትን ጊዜ ያህል ሳያገለግል ከጥቅም ውጪ ሲሆን ይስተዋላል። በአሰራር (በዲዛይን) ዕክል ምክንያት መንገዶች የዝናብ ውኃን ለረዥም ጊዜ በመያዝ ለብልሽት ሲጋለጡ ይያያል። የዝናብ ውኃ ቋጥረው ኩሬ ከሚሰሩ ቦታዎች መካከል የእስታዲየም አውቶቡስ ፌርማታ፣ ከጦር ሃይሎች ወደ ቶታል የሚወስደው መንገድ፤ ቦሌ አትላስ፣ ፒያሳ 3ተኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ ታክሲ መያዣ እና ሳሪስ ዮሴፍ ድልድይ አካባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል።

የእስታዲየሙ አውቶቡስ ፌርማታ ለእግረኞች መተላለፊያ እና ለአውቶቡስ መጠበቂያነት የሚያገለግል ስፍራ ነው። ይሁንና በግንባታው አሰራር ጉድለት የፍሳሽ መውረጃ ስለሌለው ቦታው ዝናብ ከጣለ በኋላ ውኃ በማቆር 'የጎዳና ላይ ኩሬ' ይሰራል። ውኃው መፋሰሻ አጥቶ ለቀናት ስለሚቆይ እና ቆሻሻ ስለሚይዝ በስፍራው ቆሞ አውቶቡስ ለሚጠብቀው እንዲሁም ለሚተላለፈው ህዝብ ለዐይንና ለአፍንጫ እያስቸገረ ነው።  

ሌላው ደግሞ በመሬት ወጣ ገባ አቀማመጥ ጋር ያልተስማሙ የመንገድ ስራዎችም በብዙ የከተማዋ ክፍሎች የክረምቱን ውአቁረው ይገኛሉ። በተጨማሪም ከውስጥ ለውስጥ መንገዶች በክረምቱ ጎርፍ ተገፍቶ በደለል በመሞላቱ ምዋናው መንገድ ለብልሽት ይዳረጋል። በዚህም የተነሳ በምሽት ለሚፈጠር የመኪና አደጋ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል።

ከላይ ለመግለጽ እና ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው ቦታዎች እና ሁነቶች እኔን ጨምሮ የአዲስ ዘይቤ ሚዲያ የስራ ባልደረቦቼ በሚዘዋወሩበት አካባቢ በክረምት ያለውን የመንገድ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ተሞክሯል። ከከተማዋ ስፋት እና ከችግሩ ዓይነት አንፃር ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ መሞከር ማለት 'አባይን በጭልፋ' እንደ መቅዳት ይቆጠራል። እናም የህዝብን ሀሳብ በመጨመር ይህን ጉዳይ በተሟላ መልኩ ለሚመለከትው አካል ለማቅረብ ይቻል ዘንድ የመዲናችን ነዋሪ፣ አካባቢ ያለውን የመንገድ ዕክል ከፎቶ ጋር አያይዘው ቢልኩልን በአክብሮት እናስተናግዳለን።

አስተያየት