ሐምሌ 26 ፣ 2014

የነገዴ ማህበረሰብ ሀገረሰባዊ የእጅ ስራ ውጤቶች እና የአኗኗር ዘይቤ

City: Bahir Darባህል የአኗኗር ዘይቤ

የነገዴ ማህበረሰቦች በጎጃምና በጎንደር አካባቢ በስፋት አንድ ላይ ሰፍረው የሚገኙ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲሆኑ በብዛት በባህላዊ እጅ ስራ ውጤቶቻቸው ይተዳደራሉ

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የነገዴ ማህበረሰብ ሀገረሰባዊ የእጅ ስራ ውጤቶች እና የአኗኗር ዘይቤ
Camera Icon

ፎቶ፡ አብነት ቢሆነኝ

በኢትዮጵያ በርካታ አይነት ሳቢና ማራኪ ሀገረሰባዊ የእጅ ስራ ውጤቶች (folk crafts) ይገኛሉ፡፡ ባህር ዳር እና አካባቢዋ የሚኖሩት የነገዴ ማህበረሰብ አባላትም የተለያዩ ሀገረሰባዊ እጅ ስራ ውጤቶችን ለበርካታ ዓመታት በመስራት ዕውቅናን አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በኢኮኖሚያዊያዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታቸው የጎሉት የስፌት ስራዎቻቸው እና የድንጋይ ወፍጮዎቻቸው ይገኛሉ፡፡ 

የማህበረሰቡ አባላት በአካባቢው ኗሪዎች ዘንድ “ወይጦ” በመባል እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ መጠሪያዎች ይጠራሉ፡፡ በዚህ ዳሰሳ ግን አባላቱ የሚስማሙበትን፣ በደርግ ስርዓት አገኘነው የሚሉትን “ነገዴ” የሚለውን መጠሪያቸውን ይዘናል። 

የነገዴ ማህበረሰብ ባህላዊ የእጅ ስራ ውጤቶች

በስፋት የሚታወቁትንና ለዘመናት የቆዩትን ባህላዊ የእጅ ስራ ወጤቶችን ለመስራት ነገዴዎች የሚጠቀሙባቸው የቁሳቁስ አይነቶች፣ መገኛ ቦታቸው፣ እንዲሁም የአሰራር ሂደታቸው ምን እንደሚመስል ለመቃኘት እንሞክራለን። 

በነገዴ ማህበረሰብ በስፋት የሚከወኑ የስፌት ውጤቶች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡ መሶብ፣ አገልግል፣ ቁና (ወራንታ)፣ ወንፊት፣ ሰባጥራ፣ ሰፌድ፣ ሙዳይ፣ ማቶት (የጀበና ማስቀመጫ)፣ ሌማት (ቀለም  ሻሽ) የተባሉት እቃዎች ዋና ዋናዎቹ  ናቸው፡፡ 

ሌላው ዋናው የነገዴ ማህበረሰብ ሰዎች የስፌት ስራ ውጤት ታንኳ ነው። ይህ ዘመናዊ ጀልባን የሚተካ ታንኳ በወንዶች የሚዘጋጅ ሲሆን ግብሩ ከሌሎች የስፌት ውጤቶች የተለየ ነው። በኢትዮጵያ በስፋቱ በአንደኝነት የሚታወቀው የጣና ሃይቅ ላይ በአሳ ማስገር ስራ የተሰማሩ ሰዎች ይህን የስፌት ታንኳ በብዛት ሲጠቀሙበት ይታያሉ።  

ነገዴዎች የስፌት ስራዎቻቸውን ለመስራት የተለያዩ ጥሬ ቁሶችን እና ባህላዊ የሆኑ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ፡፡

በስፌት ስራ እራሷን እና ቤተሰቧን የምታስተዳድረው ወ/ሮ እቴነሽ ገላው ነገዴዎች የስፌት ስራቸውን ለመስራት ስለሚጠቀሙባቸው ጥሬ እቃዎችና እና ባህላዊ መሳሪያዎች ስታስረዳ “ደንገል፣ ግራምጣ እና አለላ የተባሉትን የሳር አይነቶች እንጠቀማለን፤ የምንሰፋው ደግሞ በወስፌ ነው” ትላለች። 

ደንገል ከጣና ሃይቅ እና ዓባይ ወንዝ ዳር የሚገኝ፣ ለስፌት ስራ አገልግሎት የሚውል የሳር ዝርያ ሲሆን፣ ግራምጣ ደግሞ ከሳራማ ሜዳዎች የሚገኝ ሌላ አይነት የሳር ዝርያ ነው። እነዚህን የሳር አይነቶች ሴቶች በዋነኝነት ለስፌት የሚጠቀሙባቸው ሲሆኑ አለላ በተሰኘና ልዩ ልዩ ቀለሞች በተነከረ የሳር አይነት ደግሞ የተለያዩ ዲዛይኖችን በማውጣት ስፌቶቻቸውን ያሸበርቋቸዋል።    

ወ/ሮ እቴነሽ እንዳለችው በአብዛኛው ለስፌት ስራ የሚውሉትን እንደ ደንገልና ግራምጣ ያሉ ጥሬ ቁሶች ከዓባይና ጣና ሃይቅ ዳር አጭደው ያመጣሉ። 

አሰራሩ አድካሚ እና የቡድን ስራ የሚበዛበት ነው የምትለው ወ/ሮ እቴነሽ "በመጀመሪያ ከዓባይና ጣና ዳር ያመጣነውን ደንገል በፀሀይ እናደርቀዋለን። ከዚያም በታዘዝነው የስፌት አይነት በወስፌ እየሰነጠቅን በእኩል እርዝመት በተወሰነ ብዛት ሰብስበን በመያዝ በወስፌ እየወጋን በላዩ ላይ አለላውን እናዞረዋለን” በማለት አብራርታልናች። ዲዛይኑን በራሳቸው ፍላጎት ወይም በደንበኞች ትዕዛዝ ይሰሩታል።    

ፎቶ፡አብነት ቢሆነኝ

የነገዴ ማህበረሰብ ሴቶች የስፌት ስራውን በብዛት በሚሰሩበት ቦታ የተገኘ ታዛቢ የመቁረጥ፣ የማድረቅ፣ የመስፋት እና የማስጌጥ ተግባራትን ይመለከታል፡፡ እያንዳንዱ የአሰራር ሂደት የወ/ሮ እቴነሽ እና መሰል ባለሙያዎችን ጉልበት፣ ጊዜ፣ ገንዘብና ጥበብ የሚጠይቅ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ በአብዛኛው የሰፌት ስራዎቹን የሚያከናውኑት ለገበያ በመሆኑ በሚሰፉትበት ሰዓት ሰብሰብ ብለው በአንድነት ይሰራሉ። 

ፎቶ፡አብነት ቢሆነኝ

ባህር ዳር እና አካባቢዋ የሚገኙ የነገዴ ማህበረሰብ አባላት በመስራት ከሚታወቁባቸው ሀገረሰባዊ ቁሶች መካከል የድንጋይ ወፍጮ ይገኝበታል፡፡ አንድ የድንጋይ ወፍጮ ሰርቶ ለመጨረስ የራሱ የሆነ የአሰራር ሂደት አለው፤ ለዝግጅቱም ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሶች የተለዩ ናቸው። 

አቶ አህመድ ሀሰን የተባሉት የነገዴ ማህበረሰብ አባል እና በድንጋይ ወፍጮ ስራ የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው አባት እንደነገሩን የድንጋይ ወፍጮ ለመስራት የሚጠቀሙበት የድንጋይ አይነት ለየት ያለ ሲሆን በከተማዋ በተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ የሚገኝ፣ ከመሬት ስር ተቆፍሮ የሚወጣ ነው። ይህን ጥቁር ድንጋይ መዶሻ እና ማሳ የተባሉ የብረት መቆፈሪያ እና መቀጥቀጫዎችን በመጠቀም ከመሬት ፈልፍለው ያወጡና በመጥረብ እንዲሁም ቅርፅ በማስያዝ ወፍጮውን ያዘጋጃሉ። በስፌቱ ስራ ላይ ሴቶች እንደሚሰማሩት ሁሉ በዚህ የድንጋይ ወፍጮ ስራ ደግሞ በዋነኝነት ወንዶች ይሳተፋሉ።  

ለወፍጮው መስሪያ የሚያገለግለው ድንጋይ የሚገኝበት ስፍራ ከከተማው ራቅ ይላል። ጥሩ ነው ተብሎ የሚታሰበውን፣ ሻካራና በጥቃቅን ዓይኖች የተሸፈነ የመሰለ ውጫዊ ገጽታ ያለው ድንጋይ ተመርጦ፣ በማሳ ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ ይወጣል። ድንጋዩ ተፈልፍሎ ከወጣ በኋላ በትልቅ መዶሻ ይጠረባል፡፡ የተጠረበውም ድንጋይ በድጋሚ በመዶሻ ቅርፅ እንዲኖረው በደንብ "መጠብጠብያ" በሚባል ብረት ይጠበጠባል፡፡ 

ፎቶ፡አብነት ቢሆነኝ
ፎቶ፡አብነት ቢሆነኝ

የድንጋይ ወፍጮ ሁለት ክፍሎች አሉት፤ አንደኛውና ትልቁ መሬት ላይ የሚቀመጠው ወፍጮ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትልቁ ወፍጮ ላይ የሚደረግን እህል እየተመላለሰ የሚፈጨው መደቆሻ ተብሎ የሚታወቀው ትንሹ ወፍጮ ነው። ትንሹ መደቆሻ የሚሰራው መጠኑ ይነስ እንጂ እንደ ትልቁ ድንጋይ ተመሳሳይ ሂደትን በመከተል ነው። 

የድንጋይ ወፍጮ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ወፍጮ ቤቶች እየተስፋፉ በመምጣታቸው እንደበፊቱ በብዛት አይሰራም። በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀመው ዘመናዊውን ወፍጮ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ያሉ ሰዎች ግን አሁን ደረስ ይጠቀሙበታል። 

ወ/ሮ ብርቄ ገላው የተባሉ የባህር ዳር ከተማ የቀበሌ 16 ነዋሪ እንደነገሩን “በአሁኑ ጊዜ  አብዛኛውን ጊዜ እህል የሚፈጨው በዘመናዊ ወፍጮ ቢሆንም አሁንም ግን በአብዛኞቻችን ቤት የድንጋይ ወፍጮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል” ብለዋል። በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት ወቅት፣ ለምሳሌ አዋዜ ለማዘጋጀት ባህላዊውን የድንጋይ ወፍጮ እንደሚጠቀሙም ጨምረው ነግረውናል።      

ፎቶ፡አብነት ቢሆነኝ

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስፌትና የድንጋይ ወፍጮ የመሳሰሉ ቁሶችን መጠቀም እድሜ ጠገብ ክዋኔ ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ ባህላዊ ቁሶች በድንበር ተሻጋሪ ዘመነኛ ቁሶች በመተካታቸው ቀደም ሲል ይሰጡት የነበረው አገልግሎት እየቀነሰ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም የነገዴ ማህበረሰብ ህይወትና ኑሮ ዛሬም ድረስ ከነዚህ ባህላዊ ቁሶች ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ 

እንደ ወ/ሮ እቴነሽ እና አቶ አህመድ ገለፃ በብዙ ድካም የተሰሩትን የስፌት ስራ ውጤቶች እና የድንጋይ ወፍጮዎች በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ አሁንም ችግር አለ፡፡ ለዚህም የሚመለከተው አካል ከባህር ዳር ውጪ ወስደን እንድንሸጥ የገበያ ትስስር ሊፈጥርልን ይገባል ይላሉ፡፡

በዘመናዊ ቁሶች ተተክተውና ተገልጋይ አጥተው ነገዴዎችም ሆኑ ሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦች የሚሰሯቸው የእጅ ስራ ወጤቶች ምርት እየቀነሰ መምጣቱን መታዘብ ቀላል ነው። ነገር ግን አቶ አህመድና ወ/ሮ እቴነሽ እንደሚሉት እነዚህ እቃዎች የኢትዮጵያ ባህል መገለጫዎች በመሆናቸው ስራቸው መቋረጥ የለበትም፤ ተጠቃሚ እንኳን ቢያጡ የቱሪዝም አንድ መስህብ ሊሆኑ ይችላሉ። 

የእነዚህ የሃገረሰብ ጥበብ ውጤቶች አሰራር ሂደት፣ ለስራዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት ቁሶች እንዲሁም የሚከተሏቸው ክህሎቶች በእይታና በልምድ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህ ባህላዊ እውቀት እንዳይጠፋ የእጅ ስራ ውጤቶቹ አሰራር ሂደትና ጠቀሜታ በፅሁፍና በምስል ተሰንዶ መቀመጥ አለበት ይላሉ የነገዴ ማህበረሰብ አባላት። ጉዳዩ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ በቁሳዊ ባህል ጥናት መስክ የተሰማሩ አካላት ትኩረት ቢያደርጉበት ሲሉም ጠቁመዋል።  

የነገዴዎች የአኗኗር ዘይቤ

አብዛኞቹ የነገዴ ማህበረሰብ አባላት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ሲሆኑ በጣም ጥቂት የማህበረሰቡ አባላት ደግሞ የክርስትናን ዕምነት ይከተላሉ። 

የነገዴ ማህበረሰብ ኑሮ ከጣና ሃይቅና ከአባይ ወንዝ ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው፡፡ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ዓሳ ማስገር፣ የድንጋይ ወፍጮ መውቀር፣ ታንኳ ከደንገል መስራት እና የማገዶ እንጨት ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ማቅረብ ነው፡፡

የማህበረሰቡ አባላት ሌላው በጣም የሚታወቁበት ተግባር አንድ ሰው በጣና ሀይቅ ወይም በአባይ ወንዝ ሰጥሞ ቢሞት፣ አስከሬኑን በርካታ ቀናትን ቢፈጅ እንኳን በፍለጋ ማውጣት ነው። በባህር ዳር ከተማ እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ክስተት ሲፈጠር ከነገዴዎች ውጭ አቅምና ክህሎቱ ያለው ሰው ባለመኖሩ የሁሉም ምርጫ እነሱ ናቸው፡፡ 

የነገዴ ማህበረሰብ ሴቶች ዋነኛ የኢኮኖሚ አበርክቶ የስፌት ስራዎቻቸው ሲሆኑ እነሱን ለገበያ በማቅረብ ቤታቸውን ያስተዳድራሉ፡፡

የባህር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንደሚስማሙትና መታዘብ እንደሚቻለው ነገዴዎች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተቀላቅሎ የመኖር የህይወት ዘይቤ የላቸውም፡፡ ከረጅም ዘመን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ፣ ሌላው ህብረተሰብ ለእነሱ በሚያሳየው አሉታዊ አመለካከት እና አስተሳሰብ የተነሳ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ሳይቀላቀሉ ኖረዋል። 

የነገዴን ማህበረሰብ የጋብቻ ሁኔታ በተመለከተ አቶ አህመድ ሲያጫውቱን ከዚህ ቀደም የነገዴ ወንዶችና ሴቶች "በማጭዴ በወስፌሽ" ተባብለው ይጋቡ ነበር፡፡ “በማጭዴ በወስፌሽ” ማለት “ሀብትሽ በሀብቴ፤ እኔም አንቺም እንደየሞያችን ሰርተን እንኖራለን” እንደማለት ነው፡፡ “ወንዱ ከዓባይና ጣና ሃይቅ ዳርቻ ደንገል በማጭዱ አጭዶ ያመጣል፤ ሴቷ ደግሞ ደንገሉን  አድርቃ በመስፋትና በመሸጥ ትዳራቸው ይመሩ ነበር” ያሉን አቶ አህመድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሌሎች የንግድ ስራዎች መሳተፍ  መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ በባህር ዳር ከተማ ባጃጅ በማሽከርከርና ጫት በመሸጥ የሚተዳደሩም አሉ። ጥቂትም ቢሆኑ ተምረው የመንግስት ስራ ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ የማህበረሰቡ አባላትም ይገኛሉ።  

የነገዴ ማህበረሰብ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ በጎጃምና በጎንደር አካባቢ በስፋት አንድ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ በባህር ዳር ቀበሌ 03 እና 16 በብዛት ይኖራሉ፤ በጎንደር ደግሞ እንፍራዝ፣ ደንቢያ፣ ጎርጎራ፣ አሌዋ፣ ደልጊ፣ ደንገል በር እና ቁንዝላ በተባሉት አካባቢዎች በአንድ መንደር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

የተለየ የራሳቸው የሆነ የአሰተዳደር ስርዓት የሌላቸው የነገዴ ማህበረሰብ አባላት በቁጥር በርካታ መሆናቸውን በምልከታ መታዘብ ቢቻልም ትክክለኛ ብዛታቸውን ለመገመት የሚያስችል መረጃ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡

አስተያየት