የካቲት 29 ፣ 2015

ለሁለት ዓመታት ገደማ ያለደሞዝ ያገለገሉት የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ህይወት

City: Mekelleየአኗኗር ዘይቤኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

በመምህርነት ለ25 ዓመታት ያገለገሉ አንድ አስተማሪ በጦርነቱ ሳቢያ ክፍያቸው በመቋረጡ ስድስት ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር የጉልበት ሰራተኛ ሆነዋል፣ ለረሃብና ሞት የተዳረጉም መኖራቸው ተሰምቷል

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

ለሁለት ዓመታት ገደማ ያለደሞዝ ያገለገሉት የትግራይ ክልል የመንግስት ሰራተኞች ህይወት

ትግራይ ክልል፣ ክልሉን በሚያስተዳድሩ ኃይሎች እና በፌደራል መንግስት መካከል ከተፈጠረው ጦርነት አስቀድሞ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት እና ዜጎች ተንቀሳቅሰው የፈለጉትን ሰርተዉ የሚገቡበትና የሚኖሩበት ሁኔታ ነበር። 

በክልሉ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ ዜጎችም ለማህበረሰባቸው አገልግሎት እየሰጡ ማህበራዊም ሆነ የግል ኑሯቸውን በጥሩ ሁኔታ ሲመሩ እንደነበረ የተወሰኑ ሰራተኞች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። መምህራን ተማሪዎችን በአግባቡ እያስተማሩ፣  የህክምና ባለሞያዎች ታካሚያቸውን በተገቢው መንገድ ተቀብለው የሚያስተናግዱበት እንዲሁም በሌሎችም ተቋማት የህዝብ አገልግሎቶችን በአግባቡ ይሰጡ ነበር።

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የኑሮ ሁኔታቸው የበፊቱ ተቃራኒ ሆኖ ለተለያዩ ጫናዎች ተዳርገዋል። በስራ ተቋማት መውደምና መፍረስ፣ ራስን ከጦርነት አካባቢዎች ለማራቅ በሚደረጉ መፈናቀሎች እንዲሁም ሌሎች በሰላማዊ ጊዜ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጦርነቱ ሳቢያ የተገደቡ በመሆናቸው፣ አይደለም ለስራ ለመኖር እንኳን ፈታኝ ወቅት ላይ ተደርሶ ነበር። 

የመንግስት ሰራተኞች በስራ ገበታቸው የማይገኙበት ሁኔታ ሰፊ ሲሆን የትምህርት ተቋማት እና የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች ዋነኞቹ ተጎጂዎች ነበሩ። በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ለ20 ወራት ያለ ደመወዝ በመስራታቸው በፊት ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው እና ለወገኖቻቸው ይደርሱ የነበሩት የመንግስት ተቀጣሪዎች አሁን እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። 

ከነዚህ የመንግስት ሰራተኞች መካከል ለልመና እየተዳረጉ የሚገኙት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። አንዳንዶች ለረሃብ እና ለሞት መዳረጋቸውን አዲስ ዘይቤ ሰምታለች። በተለይም በህክምና እና በፍርድ ቤት የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች በከፊል እየሰሩ ያሉበት ሁኔታ ቢኖርም ለስራቸው ክፍያ ሳይጠይቁ በነፃ እያገለገሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በአስገዳጅ ሁኔታዎች ሳቢያ ከስራ ወጥተው የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ ሌላ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ።

በመንግት ሰራተኝነት ለ25 ዓመታት በመምህርነት ሞያ ኑሯቸው የመሩት መምህር ታደሰ ሃይሉ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በጦርነቱ ሳቢያ ክፍያቸው በመቋረጡ ለራሳቸው ለስድስት ቤተሰቦቻቸው ለመድረስ የጉልበት ስራ መስራት ጀምረዋል። በሒሳብ መምህርነት ረጅም ጊዜ ያገለገሉት መምህር ታደሰ “አሁን ላይ በትግራይ በደረሰው የጦርነት ሳብያ ምምህራን ደመወዛቸው እየተከፈላቸው አይደለም፣ በግል ለማስተማርም የማይቻልበት ሁኔታ በትምህርት ተቋማት መውደምና ከጥቅም ውጪ መሆን ተፈጥሯል” ይላሉ። 

መምህር ታደሰ ሃይሉ ስራ አጥ ሆነው ከሰዎች እርዳታ ለመጠበቅ የተገደዱ ቢሆንም የሚያገኙት እርዳታ ለቤተሰቦቻቸው በቂ ባለመሆኑ ቤተሰባቸውን ለማገዝ እንደኣባወራነታቸው የጉልበት ስራ ለመስራት መገደዳቸውን ገልፀዋል። በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል የጉልበት ስራ መብዛቱን አዲስ ዘይቤ ታዝባለች። ኪሳራ እና ለመነገድ ወጥተው ሳይሸጡ ወደ ቤት መመለስ የተለመደ ሆኗል። 

መምህር ታደሰ ሲናገሩ የሚሰሩት የጉልበት ስራ ለለውጥ እንኳን ባይሆን የቤተሰባቸውን የዕለት እንጀራ ለመሸፈን ግን በቂ ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ። የፌዴራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ሲሉም መምህር ታደሰ ሃይሉ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደጉረት ቆይታ ጥሪ አቅርበዋል።

በያዝነው የካቲት ወር አጋማሽ ላይ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ለመመስረት የተቋቋመው ኮሚቴ ትኩረት አድርጎ ይሰራባቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ የክልሉን ሉዓላዊ ግዛት ማስመለስና ማስከበር እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጉዳይ እንደሆኑ ተገልፆ ነበር።

የኮሚቴው አስተባባሪ የሆኑት ጀነራል ታደሰ ወረደ በጊዜያዊ መንግስት ምስረታው ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች መገባደዳቸውን ገልፀው “ከምንም በላይ አሁን ላይ የጊዜያዊ መንግስት መቋቋም ከመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጋር የተያያዘ መሆኑን” አስረድተው ነበር።

ለ20 ወራት ያለ ደመወዝ እያገለገሉ የቆዩት የመንግስት ሰራተኞች በመኖራቸው በትግራይ ክልል የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል። በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ከጦርነቱ በፊት ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለተቀረው ማህበረሰብ አጋዥ እንደነበሩ ይገልፃሉ። 

አስተያየት