ግንቦት 4 ፣ 2015

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁም ሳያደርጉ ንፁሃን ዜጎችን ግን ለመጠበቅ ተስማሙ

City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

ከ750 በላይ ሰዎች የሞቱበት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲቆስሉ እንዲሁም እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነው ግጭት የተኩስ አቁም ላይ እስካሁን አልደረሰም፡፡

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁም ሳያደርጉ ንፁሃን ዜጎችን ግን ለመጠበቅ ተስማሙ

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለበርካታ ንፁሃን ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው በሱዳን የተፈጠረው ግጭት ተፋላሚ ኃይሎች ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማት ባይችሉም ንፁሃን ሰዎችን ለመጠበቅ ተስማምተዋል ተብሏል።

በአሜሪካ እና በሳኡዲ አረቢያ አስተባባሪነት በሳኡዲ አረቢያ ጂዳ ለአንድ ሳምንት ያህል በሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) መካከል በተደረገው ንግግር ነው እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት።

በተፋላሚ ኃይሎቹ መካከል የተፈረመው ስምምነት ወደሰላም አንድ እርምጃ ያስጠጋ ነው የተባለ ሲሆን ከጦርነት ቀጠና ለቀው ለሚወጡ ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ ለመፍቀድ፣ የእርዳታ ሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን በውጊያ ወቅት መደበቂያ ላለማድረግ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል። ይሁን እንጂ ተኩስ ለማቆም አልተስማሙም።

በሁለቱ የጦር አዛዦች መካከል የተደረሰው ስምምነት የመብራት፣ የውሃ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ የፀጥታ ሃይሎች ከህክምና ተቋማት እንዲወጡ እና የሞቱ ሰዎች በክብር እንዲቀበሩ ማድረኝ ይጨምራል። 


በዛሬው እለትም ቢሆን በዋና ከተማዋ ካርቱም የአየር ድብደባዎች እና የጥይት ድምፅ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲልም የቢቢሲ ዘገባ አክሏልአክሏል። አንደኛ ወሩን ሊደፍን ቀናት የቀሩት የሱዳን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ750 በላይ ሰዎች መሞታቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸው እና መፈናቀላቸው ተዘግቧል። አዲስ ዘይቤ ከዚህ ቀደም ግጭቱ በተጀመረ ሶስተኛ ቀን ድረስ ብቻ አምስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን እንዲሁም ዘጠኝ የሚሆኑ ሌሎች ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል።

በተጨማሪም በግጭቱ ቢያንስ 18 የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ተገድለዋል የተባለ ሲሆን በርካታ የተባብሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በካርቱም እና በዳርፉር የሚያደርጉትን ስራ እንዲያቆሙ አስገድዷል። አሁን የቀሩ ተቋማትም በከፊል ስራቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ነገር ግን ሁከቱ ከቀጠለ የተለየ እጣ ፋንታ አይኖራቸውም። 

የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚገመት ምግብ ተዘርፏል ሲልም ማስታወቁ የሚታወስ ነው። 

ባሳለፍነው ሳምንት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ50 የሚበልጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የሆኑ በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ መግለፁ ይታወሳል። 

በዚህም እስከ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ 12 ሺህ ስደተኞች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትም ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው ችግር ሳቢያ 61 ሃገራት ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲያስወጡ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።


 

አስተያየት