ነሐሴ 15 ፣ 2015

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳኡዲ አረቢያ ድንበር ላይ መገደላቸው ተገለፀ

City: Addis Ababaዜና

መነሻቸውን ከአፍሪካ ቀንድ አድርገው በኤደን ባህረ ሰላጤ ከየመን ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሚገቡ ስደተኞች ውስጥ ኢትዮጵያውያን 90 ከመቶውን ይይዛሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳኡዲ አረቢያ ድንበር ላይ መገደላቸው ተገለፀ

የየመን - ሳውዲ አረቢያ ድንበርን ለመሻገር የሞከሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳውዲ አረቢያ ድንበር ጠባቂዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ገልፀ።

 

ከፈረንጆቹ መጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ባሉት 15 ወራት ውስጥ ‹‹ቢያንስ በመቶዎች›› የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የየመን-ሳኡዲ አረቢያ ድንበርን ለመሻገር ሲሞክሩ በአካባቢው የድንበር ጠባቂዎች በሚፈፀም ጥቃት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የገለፀው ሪፖርቱ፤ “ከጊዜ ወደ ጊዜ የሟቾች ቁጥር እና የግድያ ስልቶች እየተበራከቱ መጥተዋል” ብሏል።

 

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋሙ ባወጣው ባለ 73 ገፅ ሪፖርት ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ሰፋ ያለ ጥቃት በስተደኞች ላይ እየተፈፀመ ስለመሆኑ አስታውቋል። 

“የሳዑዲ አረቢያ የድንበር ጠባቂዎች ፈንጂ መሳሪያዎችንም ጭምር በመጠቀም ብዙ ስደተኞችን ለመግደል የተጠቀሙ ሲሆን አንዳንዶቹን ስደተኞች ደግሞ በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው በመተኮስ በርካታ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ሰፊ እና ስልታዊ በሆነ የጥቃት እርምጃ ገድለዋል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሳዑዲ አረቢያ ጠረፍ ጠባቂዎች ስደተኞችን የትኛው አካላቸው ላይ እንደሚተኩሱ እየጠየቋቸው እና በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ተኩሰውባቸዋል።” ሲል ሂዩማን ራይት ዋች ገልጿል።
 

የድንበር ጠባቂዎቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊገቡ ከሚሞክሩ ስደተኞች በተጨማሪ ጥቃቱን በመሸሽ እንዲሁም በቅርቡ ከሀገሪቱ ጊዜያዊ እስር ተፈትተው ወደ የመን በሚጓዙ ስደተኞች ላይ በከባድ መሳሪያ ጭምር ጥቃት እንደሚፈፅሙም ሪፖርቱ አመላክቷል። 
 

ሂዩማን ራይትስ ዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ በየመን እና ሳውዲ አረቢያ ድንበር ላይ በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሲመዘግብ መቆየቱን የገለፀው የመብት ተሟጋች ተቋሙ፤ “አሁን ላይ በጥቃቶቹ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ግድያ ቁጥር እንዲሁም የሚፈፀሙበት መንገድ እየተባባሰ” መምጣቱን ጠቁሟል።

 

ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት፣ ድርጊቱ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚከተለው ፖሊሲ አካል ሆኖ እየተተገበረ ከሆነ በሰብዓዊነት ላይ እየተፈፀመ ያለ ወንጀል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሎ፤ በተጨማሪም የሀገሪቱ መንግስት መሰል ኢ-ሰብዓዊ ፖሊሲን በአስቸኳይ መሻር አለበት ሲል አሳስቧል። 

 

በድንበር አካባቢ ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ በሰብአዊነት ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎች ከተቀረው ዓለም በግልፅ የሚታይ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ የሚደርሰውን በደል እና ግድያ ለማስቆም በተባበሩት መንግስታት የሚደገፍ ምርመራ ሊደረግ እንደሚገባም አስታውቋል።

 

መነሻቸውን ከአፍሪካ ቀንድ አድርገው በኤደን ባህረ ሰላጤ ከየመን ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሚገቡ ስደተኞች ውስጥ ኢትዮጵያውያን 90 ከመቶውን የሚይዙ ሲሆን ይህ የጉዞ መስመርም አደገኛ የሚባለው መሆኑንም በሪፖርቱ ተመላክቷል። እንድ ሂውማን ራይትስ ዎች መረጃ በአሁኑ ወቅት ወደ 750 ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ኑሮ እና ስራቸውን በሳውዲ አድርገው ይገኛሉ።

 

የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በመላው ዓለም በተከሰተበት ወቅት በ2020 በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለእስር ተዳርገው የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን  ወደሀገር መመለስ ጀምሮ እንደነበረ ይታወሳል። 


 

አስተያየት