ሚያዝያ 12 ፣ 2015

ከባህር ዳር ወደ ጎንደር ተጓዦች ከታሪፍ በላይ በመክፈላቸው እየተማረሩ ነው

City: Bahir Darዜናወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

ከባህር ዳር- ጎንደር ተጓዦች ለሚከፍሉት ከታሪፍ በላይ ክፍያ ራሳቸው ተባባሪ ሰለመሆናቸው ተገልጿል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ከባህር ዳር ወደ ጎንደር ተጓዦች ከታሪፍ በላይ በመክፈላቸው እየተማረሩ ነው

ከባህር ዳር ወደ ጎንደር የሚጓዙ መንገደኞች ከታሪፍ በላይ እየከፈሉ በመሆኑ ቢያማርሩም አሽከርካሪዎች ግን ተሳፋሪዎች ራሳቸው ለመክፈል ተባባሪ ስለመሆናቸው ይገልጻሉ።

አዲስ ዘይቤ በባህር ዳር መናኸሪያ ተገኝታ ያነጋገረቻቸው መንገደኞች እንደሚሉት አጫጫኝ ደላሎች እና ረዳት የስምሪት ባለሞያ ወይም የትራፊክ ፖሊስ “መንገድ ላይ ከጠየቋችሁ 165 ብር መክፈላችሁን ተናገሩ” በማለት ያስጠነቅቋቸዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከታሪፍ በላይ እስከ 200 ብር እየከፈሉ ይሳፈራሉ በሚል አሽከርካሪዎች እና የስምሪት ባለሞያዎች ተሳፋሪዎችም ተባባሪ ናቸው በማለት ይጠቁማሉ።  

በባህር ዳር መናኸሪያ ያገኘናቸው አሽከርካሪ አቶ ሀይሌ ፋንታሁን “በየመናኸሪያው ያለው ሕገ ወጥነት እና የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ አለመሆን”  የችግሩ ምክንያት ነው ይላሉ።

አሽከርካሪዎች መናኸሪያ ውስጥ ተራቸውን ጠብቀው በነፃነት ባለመጫናቸው ሕገወጥ ደላሎች ከእያንዳንዱ አሽከርካሪ ትርፍ እኩል በመካፈል አሽከርካሪው ከታሪፍ በላይ እንዲያስከፍል መንስዔ በመሆናቸው ህጋዊ አሽከርካሪዎች መንገደኞችን መጫን አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

የድጎማ ነዳጅ የምንቀዳበት የቴሌ ብር ክፍያ ነበር የሚሉት አሽከርካሪው፤ አንዳንድ ባለንብረቶች ከአሽከርካሪዎች ጋር በሚፈጠር አለመግባባት ክፍያውን ከሾፌሮች ላይ እጅ በእጅ በማድረጋቸው በመደበኛው ታሪፍ ነዳጅ ለመቅዳት መገደዳቸውን ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ።

የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን የመናኸሪያ አስተዳደር ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አበባው ፋንታ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከመናኸሪያ ግቢ ከመውጣቱ በፊት የስምሪት ባለሙያዎች ምርመራ ሲያደርጉ ተሳፋሪዎች ከታሪፍ በላይ ከፍለው ነገር ግን በታሪፍ ከፍለናል በማለት በመተባበራቸው ችግሩን ለመፍታት ተቸግረናል ብለዋል።

በማጫጫን ሰበብ ተሳፋሪዎች ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ ጫና የሚፈጥሩ ደላሎችን ለመቆጣጠርና ነፃ አሠራር ለመተግበር መታቀዱንም ገልፀዋል።

ማንኛውም አሽከርካሪም ሆነ ረዳት ወደ መናኸሪያ ለመግባት መለያ ባጅ እና የማኅበሩን መለያ ልብስ እንዲጠቀም አስገዳጅ አሰራር ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

አስተያየት