ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት ኬንያ ውስጥ “የፖሊስ ደንብ ልብስ” በለብሱ ሰዎች ተወስዶ እስካሁን ያለበት አልታወቀም የተባለው የአቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ ክስ መሰረቱ።
የመንግስት አካላቱ ላይ የተከፈተውን ክስ በተመለከተ በዛሬው እለት የአቶ ሳምሶን ባለቤት ወ/ሮ ሚለን ሀለፎም እንዲሁም በፌደራል እና በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ የሆኑት አቶ ዳባ ጩፋ (ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ወ/ሮ ሚለን ሀለፎም እንደተናገሩት ከባለቤታቸው መሰወር በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የተወሰኑ ጥረቶች ቢያደርግም አንድ ዜጋ በውጭ ሀገር መብቱ ሲጣስ ማድረግ ከሚገባውው አንፃር በቂ ባለመሆኑ ክስ መክፈቱ አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል።
ጉዳዩን የያዙት የህግ ባለሞያ አቶ ዳባ ጩፋ በበኩላቸው “ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የመጣበት ምክንያት እነዚህ የተከሰሱ አካላት ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ነው። ፍርድ ቤት በህግ አግባብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማስገደድ የሚችል በመሆኑ እንደሚያስገድዳቸው እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ሚለን እስካሁን በተደረገው ጥረት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንም ያገኙት ፍንጭ እንደሌለ አንዳንዴም በሶስት ወራት ውስጥ እናስለቅቀዋለን የሚሉ ምላሾች በተደጋጋሚ መሰጠታቸው ምንም ያህል ርቀት መጓዝ እንዳልተቻለ የሚያመላክት ነው ሲሉ ገልፀዋልገልፀዋል።
በኢትዮጵያም ሆነ በኬንያ የተፈረሙ “ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የጣሰ ድርጊት ነው” የሚሉት ጠበቃው አቶ ዳባ ጩፋ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጋውን ማክበር፣ መጠበቅ እና ማሟላት ይገባው ነበር ብለዋል።
አዲስ ዘይቤ ለአቶ ሳምሶን ባለቤት ወ/ሮ ሚለን ግለሰቡ እንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲፈፀምበት የሚያስችል ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ጠይቃ ነበር።
ወ/ሮ ሚለን “አቶ ሳምሶን ወንጀል እና ሱስ ነክ ነገሮች ዙሪያ የለም፣ በስራ ጉዳይም እንደዚህ አይነት ስጋት አልጠብቅም። ምናልባት እሱን ለዚህ የሚያጋልጠው መልካምነቱ ነው” ሲሉ መልሰዋል። የአቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ጠበቃም ጉዳዩን ለመያዝ ሲቀበሉ አቶ ሳምሶን ለ19 ዓመታት በኖረበት ኬንያ ከወንጀል ነፃ መሆኑን የሚመሰክር እውቅና አለው ብለዋል።
“ሳምሶን የተወሰደው በፖሊሶች እንጂ በዱርዬዎች አይደለም” የምትለው ባለቤቱ ወ/ሮ ሚለን፣ በህግ የሚፈለግ ከሆነ በህግ አግባብ እንዲጠየቅ ካልሆነም ነፃ ከሆነ ከቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል ማድረግ እንዲቻል “የኢትዮጵያ መንግስትን እለምናለሁ” ብላለች።
ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የሰብዓዊ መብት ችሎት በቀረበው ክስ መንግስት ዜጋውን ከመጠበቅ አንፃር ግዴታውን እንዲወጣ እና የአቶ ሳምሶን እና የቤተሰቦቹ መብት እንዲጠበቅ የሚጠይቅ መሆኑ ተገልጿል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፍትህ ሚኒስቴር ውክልና ሰጥቶ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ የገልፁት ጠበቃው አቶ ዳባ፣ ቀጣይ ቀጠሮ ለነገ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም መሰጠቱን ገልፀው የኢድ አልፈጥር በዓል በነገው እለት ከሆነ ቀጠሮው ወደ ሰኞ ሚያዝያ 16 ይዞራል ብለዋል።
ጠበቃው አክለውም ከዚህ የክስ ሂደት ሁለት ነገር እንደሚጠብቁ ገልፀው “ከመንግስት በኩል ጉዳዩን በፍርድ ቤት ደረጃ በመያዛችን ሊያከብረን ይገባል የመጀመሪያው ሲሆን በሌላ በኩል መፍትሄ ማግኘት እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኬንያ መንግስት ጉዳዩን በፍጥነት እንዲያጣራ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን የኬንያ መንግስት የኢትዮጵያንም ሆነ ዓለም አቀፍ መርማሪዎች አናስገም ማለቱም በወቅቱ ሲዘገብ ነበር። የአቶ ሳምሶን ቤተሰቦችም ከተሰወረ ከሶስት ወራት በኋላ ፍትህ ለመጠየቅ በናይሮቢ ጎዳና ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ከዓመት ከስድስት ወራት በፊት በኬንያ ኪሌሌሽዋ በተባለ አካባቢ ሲያሽከረክር ሲቪል የለበሱ እና የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ መንገድ በመዝጋት ወደሌላ ተሽከርካሪ ካስገቧቸውቧቸው በኋላ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።