ሚያዝያ 11 ፣ 2015

በሀዲያ ዞን በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰማ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

በዞኑ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ደመወዝ ባለመከፈሉ በመንግስት ሰራተኞችና መምህራን ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሀዲያ ዞን በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰማ

በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከጀመሩ ሁለተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል፡፡

በዞኑ ባደዋቾ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ ከ ሰባት ሰዓት በላይ በተደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ አበባን ከአርባ ምንጭ  የሚያገናኘዉ መንገድ ዝግ ሆኖ ሲውል ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ሰልፈኞችን ለመበተን በዞኑ ፓሊሶች ተኩስ መከፈቱን የአዲስ ዘይቤ ምንጮች ገልጸዋል።

በሾኔ ከተማ ሰልፉን ለመበተን በተወሰደዉ እርምጃ አንድ የፓሊስ አባል በእራሱ ተኩሶ ጉዳት ሲደርስበት ሶስት ሰዎች ድብደባ ተፈፅሞባቸዉ በከተማዋ ወደሚገኘዉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መወሰዳቸዉን ምንጮቻን ተናግረዋል። 

በሰልፉ ምክንያት  የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል ተብሏል።  

ከሚያዘያ 10 ጀምሮ እየተካሄደ ነው በተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች አገልግሎት መቋረጡ የተገለፀ ሲሆን የሚመለከተው አካል ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ የስራ ማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ ይቀጥላል ብለዋል ሰለፈኞቹ። 

ሰልፉን ለመበተን የተወሰደዉ እርምጃ ቁጣን እንደቀሰቀሰ የሚናገሩት ሰለፈኞቹ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉን ነግረዉናል።

"ስልጣን የህዝብ ነዉ፣ የሰራተኛዉ የላብ ዉጤት ይከፈለዉ ፣ ልጆቻችንን መመገብና ማስተማር አልቻልም፣ የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶናል እንዲሁም ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጠን እንገኛለን" የሚሉት ሰልፈኞቹ የያዟቸው መልእክቶች ናቸው፡

አዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ላይ የዞኑን አስተዳደር እና አመራሮችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገችዉ ጥረት አልተሳካም። በቀጣይ ምላሽ ካገኘን ይዘን የምንመለስ ይሆናል

አስተያየት