ታህሣሥ 21 ፣ 2014

ብሔራዊ ውይይቱ ስኬታማ እንዲሆን ምን ይደረግ?

አስተያየት

አስተያየቶች

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ብሔራዊ ውይይቱ ስኬታማ እንዲሆን ምን ይደረግ?

መኮንን ዛጋ

አገራችን ላለፉት ረጅም ዘመናት በቆየችበት የስርዓተ-መንግስት ግንባታ (State Building) ሂደት ዉስጥ በተፈጠሩ የታሪክ እጥፋቶች፣ ሳይፈቱ ያደሩ የመደብ ቁርሾዎች፣ በአግባቡ ያልተመለሱ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ወዘተ… ጥያቄዎች. የተነሳ ይህን መሰል አገራዊ የዉይይት መድረክ ለማሰናዳት ማሰብና ለተግባራዊነቱም መትጋት በአጉል ፉክክር ያልተዘጉ የዘመናት አጀንዳዎችን ለመፍታት በመንግስት በኩል ገቢራዊ ቁርጠኝነት ለመኖሩ አመላካች ነዉ፡፡ ባንጻሩ የእነዚህ ሳይመለሱ ያደሩ ዘመን ተሻጋሪ የሉአላዊ ዜጎችና የአጠቃላይ ማኅበረሰብ ዘርፈ-ብዙ መሻቶች በክሱት መኖር ብሔራዊ ዉይይት በራሱ ከሚኖርበት ባህሪያዊ ተግዳሮት በተጓዳኝ በዚህ መሠል ዉስብስብ አዉድ ዉስጥ መከወኑ ተጨማሪ የገመድ መጓተትና የማይፈታ ቅርቃር ጫና እንደሚያስከትል ሳይታለም የተፈታ ነዉ፡፡ ይህም ብሔራዊ ዉይይቶች በአዘገጃጀት፣ አደረጃጀት፣ በቅርፅና በአተገባበር ረገድ ባላቸዉ የፈርጀ-ብዙ አካታችነት ባህሪ የተነሳ የበርካታ ፍላጎቶችና መሻቶች መንጸባረቂያና የሃሳብ ፍጭቶች መድረክ ስለሚሆኑ በክንዉን ሂደታቸዉ ላይ በርካታ መሰናክሎች ይገጥማቸዋል ወይም ደግሞ በተቃራነዉ አሳላጭ ድጋፎችን ያገኛሉ፡፡

በዘርፉ ባለሙያዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግጭት፣ ጦርነትና የሽግግር ወቅት ቀዉስ በተከሰተባቸዉ የተለያዩ የዓለም አገራት ዉስጥ የተካሄዱ በርካታ ብሔራዊ ውይይቶችና የምክክር መድረኮች (ወይም ጉባኤዎች) በዋናነት ሦስት አበይት አስቻይ ወይም ገቺ ጉዳዮች ይገጥማቸዋል፡፡ እንደጥናት ሰነዶቹ ጥቁምታ ከሆነ በዉይይቶቹ አጀንዳዎችና የዉይይት ነጥቦች ላይ በአብዛኞቹ ተሳታፊ አካላት መካከል አጠቃላይ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻልና የስምምነት ማዕቀፎች የሚቀረጹ ቢሆንም እንኳ ከመካከላቸዉ ገሚሶቹ የዉይይት አጀንዳዎች ወይም ጉዳዮች በዉይይቱ በተደረሱ የስምምነት ማዕቀፎች መሠረት ተግባራዊ ሊደረጉ አልቻሉም፣ ገሚሶቹ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ብቻ ተግባራዊ ሆነዋል። ለእነዚህ ለክንዉን ሂደትና ተተግባሪነት አስቻይና ገቺ ሁኔታዎች መፈጠር በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም በዋናነት የሚጠቀሱት ከአጠቃላይ የፖለቲካ ተዋንያን ቁርጠኝነት፣ የአገራቱ የፖለቲካ አውድ እና ከብሔራዊ ዉይይቱ የአዘገጃጀት ሂደት ጋር የተያያዙ ነጥቦች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ነገረ-ምክንያቶች በተለየ መልኩ በብሔራዊ ውይይቶች ዉስጥ ስምምነት ለተደረሰባቸዉ ነጥቦች ወይም ዉጤቶች ተተግባሪነት አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ወይም እንዳይፈጸሙ በመገደብ ረገድ ጠቋሚ ሆነው ተገኝተዋል።

በሌላ መልኩ እነኚህን መሠል ዉይይቶች የሚመሩበት (የአካሄድ) ስርዓት (National Dialogue Procedure Manual) የሚሆን ምንም አይነት ወጥ የሆነ ፍኖተ-ካርታ ወይም ንድፍ የለም፡፡ ሆኖም ባለድርሻ አካላት በሌሎች አገራት ከተከናወኑ መሠል ዉይይቶች ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ትኩረት ቢሰጡ፣ ቁልፍ ተግዳሮቶችን አስቀድሞ ለመረዳትና የዉይይቶቹን ስኬታማነት ለማጎልበት ወይም ዉድቀቶችን ለመግታት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮችን በቀላሉ እንዲለዩ ሊረዳቸው ይችላል። እነዚህ አስቻይ ወይም ገቺ ምክንያቶችን በዝርዝር ስንመለከት፡-

  1. የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የፖለቲከኞች ቅንነት

በገዥው መንግስትና በሐቀኛ የሕዝብ ወኪሎች ዘንድ በእኩል ደረጃ ስለአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ የፖለቲካ ዉሳኔ አሰጣጥ ተሳትፎ፣ የወደፊት ፖለቲካዊ አካሄድና የፖርቲዎቹ መጻኢ ዕድል ባጠቃላይ ከችግሩ መዉጫ መንገድ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና የልሒቃን ስምምነት እንዲሁም እነኚህን ልዩነቶች በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ የመፍታት እሳቤ ካለ፣ ከዉይይቱ የተሳካ ውጤት የሚገኝ ሲሆን የመፍትሔ አቅጣጫዎች የአተገባበር ዕድልም በእጅጉ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡

ሆኖም መንግስት፣ ፖርቲዎችና ታጣቂ ቡድኖች የሚፈጥሩት ሁከትና የሜዳ ላይ ጦርነትን ለመቀጠል ወይም አገራዊ ውይይት ለመፈለግ እንዲወስኑ ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ እና ለጦርነቱ በሚያዉሉት ሀብታቸው ውስጥ ያለውን ለውጥ እንዴት ይገነዘባሉ? የሚለዉ ቁልፍ ነጥብ ነዉ፡፡ ይህ የዉሳኔ መነሻ ነጥብ ሁሉም ተወያይ ወገኖች ለዉይይቱ የሚኖራቸዉን እይታ መገለጫና የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸዉን እጅጉን የሚበይን መስፈንጠሪያ ነዉ፡፡ የዊልያም ዛርትማን 'ሁለቱንም ወገን እኩል-በጋራ የሚጎዳ አለመግባባት-mutually hurting stalemate' የሚለው አስተሳሰብ ፓርቲዎች ለምንና መቼ ወደ ዉይይትና ድርድር እንደሚገቡ ለመረዳት የሚያስችል ወሳኝ ተጽእኖ ፈጣሪ መለያ ነጥብ ነው፡፡ ይህም የሚፈጠረዉ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የጦር ሜዳ ትግሉን ለመቀጠል የሚያስከፍለው ዋጋ ከጥቅሙ በላይ ሲሆን እና ለውይይት ቅድሚያ ለመስጠት በቂ 'የሚያመረቅዝ ህመም-ቃንዛ' ሲሰማቸዉ ነዉ፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነን በኮሎምቢያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ነዉ፡፡ በኮሎምቢያ መንግስት እና የታጠቁ ቡድኖች የውይይት መንገድን ለመቃወም ሁለቱም ወገኖች በጦር ሜዳ እያጋጠማቸው የሚገኝን ወታደራዊ ሽንፈት እንዲሁም ቁሳዊና ስነ-ልቦናዊ ኪሣራ ወይም ህመም በየበኩላቸዉ በጭፍን ሲክዱና ሲያስተባብሉ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም ስልሳ አመታትን ከፈጀ ጦርነት በኋላ ለመነጋገርና አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ለመፈራረም በቅተዋል፡፡ ሁሉም ነገር የአገር ሃብትና የሰዉ ነፍስ ከወደመ በኋላ ሆነ እንጂ፡፡

አገራት በዚህ መሠል የግጭት አዙሪት ዉስጥ በሚሆኑበት ወቅት መንግሥት ከሚኖረዉ የኃይል የበላይነት በመነሳት በሆደ ሰፊነት ከወታደራዊ ስትራቴጂው የሚቀዳዉን የፖለቲካ ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳ ሁሉም ተናካሽ ኃይሎች ወደሠላማዊ የዉይይት መድረክ እንዲመጡ ተገቢዉን የወንድ በር መስጠት ይኖርበታል። ይህም ለዉይይቱ ለሚኖረዉ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አንዱ መገለጫ ነዉ፡፡

በዚህ ረገድ ሁሉም ተፋላሚ ፓርቲዎች ከወታደራዊ ፍጥጫቸው የመዉጫ የፖለቲካ በር (Political Exit) ያስፈልጋቸዋል፣ ይህም የአመጽ ተዋናይ ወገኖች ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር መነጋገር ይቻላል የሚል ስሜት እንዲያዳብሩ፣ ለታጠቁ ቡድኖች ደግሞ ከጦርነቱ በኋላ በአገራቱ የፖለቲካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ድርሻ እንዳላቸው እንዲሰማቸዉ ያደርጋል። ይህም ለብሔራዊ ዉይይቶች ስኬት ተገቢዉን መደላድል ወይም መሰናክል ይፈጥራል፡፡

2. የፖለቲካ አውድ ምክንያቶች

የአገራት የፖለቲካ አዉድ ለብሔራዊ ዉይይቶች ስኬት ወይም ዉድቀት መንስኤ የሚሆን ሌላዉ ጉዳይ ሲሆን በብሔራዊ ውይይቶች ውጤቶች ላይ ተጽዕኖ በማድረግ ረገድ ስድስት የፖለቲካ አውድ ምክንያቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡-

የአገራዊ ልሒቃን ተቃውሞ ወይም ድጋፍ፡-

በብሔራዊ ዉይይት ሂደት ዉስጥ ከሚኖራቸዉ ተጠቃሽ አዎንታዊና አሉታዊ ሚና አንጻር ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸዉ ከሚገቡ አካላት መካከል የአገራዊ ልሒቃን እሳቤ፣ አመለካከት እና ባህሪያት ጉዳዮች ተቀዳሚዎቹ ናቸዉ፡፡ እነዚህ የአገራዊ ልሒቃን ቡድኖች በማኅበረሰቡ ላይ ከሚያሳርፉት ትዕምርታዊ ተፅዕኖ እንዲሁም ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ሲነፃፀሩ ካላቸዉ ተገዳዳሪና ያልተመጣጠነ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ኃይል አንጻር በብሔራዊ ውይይቶች ስምምነት ላይ የመድረስ እና የዉጤቶቹ የመተግበር ዕድል ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ብቸኛና በጣም አስፈላጊ ኃይል (The necessary Angels and Unavoidable Devils) ሆነዉ ተገኝተዋል። 

ምንም እንኳን አብዛኞቹ ልሒቃን የለዉጥ ሀሳብ አመንጪዎችና አቀንቃኞች ቢሆኑም ቅሉ በለዉጥ ሂደት ዉስጥ በሚፈጠሩ ሳንካዎች፤ በለዉጡ ግብ ይዘትና ቅርፅ ግልጽነት እጦት እንዲሁም በለዉጡ እንዳላቸዉ ዙሪያ መለስ የተሳትፎ ሁኔታ የመንግስታዊ አስተዳደር ማሻሻያዎችን (Governance Reforms) ሊደግፉ ወይም ሊቃወሙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ‹‹አገራዊ ለውጥ ያስፈልጋል›› ብለው የሚከራከሩ ልሒቃን ተዋናዮችም ሆኑ ቡድኖች ለዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ ወይም ሽግግር ቁርጠኛ ደጋፊ ናቸዉ ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፣ ወይም አይገባም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወገኖች የለዉጥ ሂደቱን ከብዙኃኑ ፍላጎት ተቃርኖ በመጥለፍ ለግል ፍላጎታቸዉ ማሳኪያ ወይም ለፓርቲያዊ ጥቅማቸው ማሟያ ሊያደርጉት ይችላሉና ነዉ።

ስለሆነም እነዚህን ልሒቃዊ የፍላጎት ቡድኖች ካላቸዉ ሰፊ ተፅዕኖ አንጻር በመመዘን በብሔራዊ ዉይይቶች ዉስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄና የተካቶ መርህ ላይ በመንተራስ በየደረጃዉ ማሳተፍ ተገቢ ነዉ፡፡ የእነዚህ ልሒቃን ድጋፍ ወይም ተቃውሞ በተለያዩ የብሔራዊ ዉይይት ሂደት ደረጃዎች ማለትም የዝግጅት፣ የድርድር እና የትግበራ ደረጃዎችን ጨምሮ ሊገለጽ ይችላል።

በሌላ ጎኑ በብሔራዊ ውይይቶች የተገኙ አመርቂ ድሎች ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በልሒቃን ጉትጎታና ተፅዕኖ ይገለበጣሉ፡፡ ይህ የመቀልበስ ተግዳሮት እንደሚመጣ ቢታወቅም እንኳ የትግበራው ምዕራፍ በአገራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ተዋናዮች ዘንድ ችላ የመባል አዝማሚያ ይታያል። ስለሆነም ልሒቃኑን በተገቢዉ የዉክልናና ተካቶ መርህ (Representation & Inclusion Principle) በመለየት እንዲሁም የተፅዕኖ አድማሳቸዉ ብዙኃኑን መሻት በማይጋርድ መልኩ ማሳተፍ ይገባል፡፡

የምልዓተ-ህዝብ ድጋፍ ወይም ተቃዉሞ 

ሕዝባዊ ድጋፍ ሲባል በጥቅሉ ሕዝቡ አንድን የለዉጥ ሀሳብ በንቃት ለመደገፍ በቁርጠኝነት መነሳት፣ በውስጡ ለመሳተፍ በሙሉ ፈቃድ መቀበል፣ በዉጤቱ ለሚደርስበት ተፅዕኖም ፈቃደኛነት መኖር እንዲሁም ለትግበራዉ ያለዉ ቅን መሻት ነዉ፡፡ ለሀገራዊ ውይይት ሂደትና ተከታይ ውጤቱ ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ መኖርና ሀሳቡ በብዝሃ-ወገኖች ዘንድ መገዛት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው አጠቃላይ የማኅበረ-ፖለቲካ ሁኔታ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በተጓዳኝ የከባድ ሚዛን ፖለቲካዊ ተዋናዮችን አመለካከት በአዎንታዊ መልኩ እንዲቀየር ያደርጋል፡፡ የኃይሎች ሚዛን ማስጠበቂያም ይሆናል፡፡

በሌላ አገላለጽ በዉይይቱ ተግባቦት፣ በድርድር እና በስምምነቶች ትግበራ ሂደት ላይ የተሳታፊዎችን አዎንታዊ እርምጃዎችን ለማረጋገጥ የህዝቡ ሃሳቡን መግዛት እጅግ ወሳኝ ነው።

ባንጻሩ ደግሞ ዉይይቶች የሕዝቡን የሞቅታ ድጋፍ ጊዜያቶች ጠብቀዉ ወደፊት መንቀሳቀስ ካቃታቸዉ የተለገሱትን የድጋፍ መሠረትና ቅቡልነት ሊያጡ ይችላሉ፡፡ ይኽዉም ዜጎች በዉይይቱ መባቻ የሚደረሱ ስምምነቶች ወይም የሚገኙ ዉጤቶች በመዘግየታቸው ከተሰላቹ የዉይይቱ ቅቡልነቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ፣ እንዲሁም ደግሞ ዜጎች በዉይይቱ የአዎንታዊ እርምጃዎች እጦት ከተበሳጩ ለሂደቱ የሚደረገው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊቀንስ ይችላል። ስለሆነም አገራዊ ዉይይቶች እነኚህን የድጋፍና ተቃዉሞ ሚዛኖች ለማስጠበቅ በሚያስችል የጊዜ ማዕቀፍ መከናወን ያለባቸዉ ሲሆን በተቻለ መጠን አዎንታዊ የስምምነት ነጥቦች ላይ ለመድረስ መታተር ይገባቸዋል፡፡

የቀጠናዊ እና የአለምአቀፍ ተዋናዮች ድጋፍ ወይም ተቃውሞ

በፖለቲካል ኢኮኖሚ አዉድ ሲታይ ማንኛዉም አገር ከሌሎች ተነጥሎ የሚኖር ደሴት አይደለም፡፡ ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሌሎች አካላት የተፅዕኖ ጥላ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ደረጃ እንደሚያርፍበት ይታመናል፡፡ እነዚህ አካላት ደግሞ በአንድ አገር ሕልዉና ዉስጥ ሊያስጠብቁት የሚከጅሉት ጥብቅ ብሔራዊ ፍላጎት ያላቸዉ ክልላዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ቅርጽ የያዙ ሉዓላዊ አገራት እንዲያም ሲል የባለብዙ-መድረክ ተሳትፎ ያላቸዉ ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም በብሔራዊ ምክክሮች ውስጥ የተለያዩ የውጭ ተዋናዮች በቀጥታም ሆነ በውክልና (By proxy) ፣ በነቢብ ወይ በገቢር ይሳተፋሉ። እነዚህ ተዋናዮች ጎረቤት አገሮችን፣ ኃያላን አገራትን፣ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ቡድኖችን ወይም ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ሊያካትቱ ይችላል፡፡

ክልላዊ ተዋናዮች ብዙውን ጊዜ በቅርብ ባሉ ጎረቤት አገራት ዉስጥ በሚፈጠሩ ቀዉሶችና ወሳኝ የፖለቲካ ለዉጦች ላይ የሚያስጠብቋቸዉ ተጨባጭ ጥቅሞችና እጅግ የበለጡ አሳሳቢ ፍላጎቶች ስላሏቸው፣ በብሔራዊ ውይይቶች ለሚገኙ ውጤቶች አዎንታዊም አሉታዊም ተጽኖአቸው የበለጠ ወሳኝ ይሆናል። 

በዚህ የተነሳ በአንድ አገር ብሔራዊ ዉይይቶች በሚደረጉበት ወቅት ሂደቱን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በመደገፍም ሆነ በመቃወም ረገድ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና ለማሳደር ይዘጋጃሉ። እንዲሁም እነዚህ ወገኖች በግጭቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑ አካላት ጋር ቀደም ሲል በነበሩ ግንኙነቶች የተጠቀሙ ወይም ሲጠቀሙ የቆዩ አሊያም ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ባንጻሩ ደግሞ ዓለም-አቀፍ ተዋናዮች ዉይይቱን ለመደገፍ ወይም ለመቃወም የሚያስችል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ኃይል ሊኖራቸው ይችላል።

ስለሆነም ተገቢዉን ፖለቲካዊ ትንታኔና የስጋት ምደባ በመሥራት የፈርጀ-ብዙ ዉጫዊ ተዋናዮችን ፍላጎት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማይነካ መልኩ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሚገባዉ ልክ መረዳት እና ጥቅማቸዉን ለማካተት መሞከር አለበት።

የውይይት ባህል

ባብዛኛዉ ጊዜ የእርስ በርስ ግጭት የሚመጣው ማኅበረሰቡ ቀደምት ባህሉንና ታሪካዊ የዕርቅ፣ የሽምግልናና የፍርድ አሰጣጥ ስርዓቱን እየዘነጋው ስለሚመጣ ወይም በዘዉትራዊ የኑሮ ዳራዉ ስለማይጠቀመዉ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን መሠል ብሔራዊ ዉይይቶች ባንድ በኩል ማኅበረሰቡ ወደ ቀደምት ባህሉ እንዲመለስ እንዲሁም የወንድማማችነት አብሮነት ዘመኑን እንዲያስታዉስ መነሻ  ይሆናሉ፡፡ ወግ፣ ልማድ፣ ባህል ውስጥ መከባበር፣ መቻቻል፣ የዕርቅ ሥርዓት፣ እንዲሁም ትክክለኛ የዳኝነት ሥርዓት አለ፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን ያሏትን ዕምቅ ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊታዊ የዉይይት ባህሎች እንደየተጨባጭ አዉዳቸዉ በመመዘንና በመጠቀም ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ማድረግ ትችላለች፡፡ እያንዳንዱ ሰው በባህሉ መሠረት የሌሎች ወገኖችን እሳቤ እንዲያከብር፣ የማያከብር ደግሞ በባህሉ መሠረት የሚገሰፅበትን ባህላዊ ዳኝነትና ምክር ለትውልዱ በማስተማር አሁን ያለው አለመረጋጋት መፍታት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የሰላም ባህልን መነሻ ሐሳቦችና ፍትሕን በማረጋገጥ አሁን ያለውን ትውልድና መጪውን ትውልድ በማስተማር ሰላምን ማረጋገጥ ያስችላል፡፡

ከዚህ መንደርደሪያ አንጻር ብሄራዊ ውይይቶች በቅድመ ድርድርም ሆነ በድርድር ደረጃዎች እያሉ በአንድ ሀገር ውስጥ ካሉ የውይይት ልምዶች፣ ወግና ባህሎች (ለምሳሌ በአካባቢያዊ ደረጃ ከሚፈጸም የዕርቅና ሽምግልና ሂደት) በርካታ ተሞክሮዎች እንዲወስዱ ማድረግ ለዉይይቱ ስኬታማነት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ልምድ ያካበቱ የአገር ውስጥ የዉይይት አስተባባሪዎችና አሸማጋዮች ማሳተፍ የተገባ ሲሆን፣ እነዚህ አስተባባሪዎች በብሔራዊ ውይይቶች በውስጥም ሆነ በውጭ በመሥራት ተወያይ ወገኖችና ፓርቲዎችን ወደሚያግባባ አማካይ ቦታ ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ከቀደሙ ዉይይቶች/ድርድሮች የሚገኙ ተሞክሮዎች

ያለፉትን ስህተቶች ላለመድገም ከቀደምት ዉይይቶችና ድርድሮች የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ እንደትምህርት መጠቀም በአገራዊ ውይይቶች ላይ ውዝግብ እንዳይፈጠርና ያለመግባባት ቅርቃሮችን ለመፍታት ያግዛል።

አመጽና ግጭት

ለብሔራዊ ዉይይት አንዱ ሳንካ የሚሆነዉ ከዉይይት አዳራሹ ዉጭ ያለዉ የጦር ሰበቃ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህም ተወያይ ወገኖች ሁለት ባላ ተክለዉ ስለሚገቡ ባንዱ ሲረቱ ሌላዉን እየተጠቀሙ የዉይይቱን አዉድ ሲያዛቡ ይታያል፡፡ በሃሳብ የሚረቱበት ሁኔታ ሲፈጠር ለጦር ዉረድ እንዉረድ ይዘጋጃሉ፡፡ ስለሆነም ለብሔራዊ ዉይይቶች አንዱ ቅድመ-ሁኔታ መሆን የሚገባዉ በቅድመ-ድርድር ሂደት የሚደረግ የነፍጥ መድፋት ስምምነት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ ካየነዉ ግጭት በብሔራዊ ውይይቶች ሂደት ስምምነቶችን የመድረስ እና የመተግበር ችሎታ ላይ ጉልህ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ነገር ግን በአመጽ ደረጃዎች እና በብሔራዊ ውይይቶች ውጤቶች መካከል ግልጽ የሆነ የእኩል ተመዛዛኝነት ንድፍ አይገኘም።

3. የብሔራዊ ዉይይቶች የንድፍ ወይም የሂደት ነገረ-ምክንያቶች

ከፖለቲካዊ አውድና ቁርጠኝነት ሁኔታዎች ጎን ለጎን፣ የብሔራዊ ዉይይቶች የንድፍ ወይም የአዘገጃጀት ሂደት ነገረ-ምክንያቶች ማለትም የአዘገጃጀት፣ የአደረጃጀት፣ የአካሄድ ወይም የተሳትፎ ሂደት ጉዳዮች በዉይይቱ ጅማሮ ወይም መባቻ ዘላቂ ስምምነቶች የመደረስ ዕድል ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የብሔራዊ ውይይት ንድፍ በሂደቱ ውስጥ የሚኖረውን የወካይነት ደረጃ እና የስልጣን ድርሻ ክፍፍል ይቀርፃል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በመሆኑም በብሔራዊ ዉይይት ዉጤታማነት ላይ ጉልህ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ስድስቱ የሂደት ቁልፍ ጉዳዮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ እነርሱም፡-

ውክልና፣ ቁጥር እና የተዋንያን ምርጫ አሰራር

በብሔራዊ ውይይቶች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለሚታጩ ወገኖች የሚቀመጡ የመምረጫ መስፈርቶች እና መመዘኛዎች፣ የሚሰጡ የኮታ ድልድሎች እና የምርጫ አሰራር ቅደም-ተከተሎች የተለያዩ የማህበራዊና የፖለቲካ የፍላጎት ቡድኖችን በሚጠብቁት ስፋትና መጠነ-ልክ የሚኖራቸዉን የተወካይነት ሚና ሊደግፉ ወይም ሊያደናቅፉ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም በመመዘኛዎቹ፣ በምርጫ አሰራሩና በኮታ ምደባ ላይ የግልጽነት አለመኖርና የጋራ መሥፈርት አወጣጥ ስርዓት አለመዘርጋት የዉይይቱን ሕያዊነትና ቅቡልነት ያሳጣል፡፡ በተቃራኒዉ በዚህ መልክ የሚፈጠር ግልጽነት ለዉይይቱ ስኬታማነት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ 

ስለሆነም ተሳታፊዎች አስቀድመዉ እርስ በራሳቸው በመስፈርቶቹ ላይ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው። ባንጻሩ በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ የምርጫ ቅደም-ተከተል ሂደቶች በልሒቃኑ ይጠለፋሉ፡፡ በዚህም በብሔራዊ ውይይት ውስጥ እንዲሳተፉ ለእነርሱ ታማኝ የሆኑትን ተሳታፊዎችን በሚመርጡ ልሂቃን የተቀናጁ ይሆናሉ።

የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች

በብሔራዊ ውይይት ውስጥ የሚቀረጹ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች የትኞቹ ተዋናዮች የመወሰን ስልጣን እንዳላቸው እና ውሳኔዎች በድርድሩ እንዴት እንደሚረጋገጡ ቢያንስ በወረቀት ላይ ይወስናሉ። እነዚህ ሂደቶች በብሄራዊ ውይይቶች ላይ ለተነሱ ሃሳቦች በቀላሉ ስምምነት ለመድረስ እና/ ወይም ዉሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸው ወይም የሚገድቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ህጋዊ የስምምነት ውጤቶችን ለማስገኘት እጅግ ወሳኝ ናቸው። በብሔራዊ ዉይይቶች ዉስጥ አብዛኛውን ጊዜ የመጨረሻ ውሳኔዎች የሚወሰዱት በስምምነት ሲሆን፣ ይህም በሃሳቦች መካከል የጋራ መግባባት መፈጠር፣ አጀንዳዎችን ለማስፋትና አብዛኛውን ጊዜም የተገለሉ ድምፆችን ለማካተት የሚያግዝ ነዉ፡፡ ነገር ግን ባንዳንድ ሁኔታዎች የውሳኔ አሰጣጥ ልማዶች ከተቀመጡ መደበኛ አካሄዶች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነዉ በተለይም ባንድ በኩል ልሂቃን ከጠቅላላ ጉባኤው ውጭ ካሉ አካላት ጋር ተወያይተዉ ውሳኔ ሲያደርጉ፣ በሌላ በኩል በተለይም በጦር ሜዳ እየተፋለሙ ከሚገኙ አካላት ጋር ሲሆን በውጤቱም ሌሎች ተሳታፊዎችን ሳያካትት ይቀራል። በዚህ መሠል ሁኔታ ዉስጥ መግባባት አለመቻል የግጭት ወይም አለመግባባት እንቅስቃሴው ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል መፍቀድ ማለት ሊሆን ስለሚችል መግባባት ላይ መድረስ አለመቻል የበለጠ በጦር የተቋቋሙ ኃይሎችን ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል በስምምነት ላይ ከተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ በተጨማሪ እንደ የቴክኒካዊ ሥራ ቡድኖችን ያሉትን በመጠቀም መሰል አለመግባባቶች በሚፈጠሩባቸው ጊዜያትም በሌሎች ሳይንሳዊ የተግባር ዘዴዎች እንዲቀየሱ በማድረግ መግባባት ላይ እንዲደረስ ማድረግ አለባቸው፡፡

የአወያዮችና የአመቻቾች ምርጫ

ይህን መሠል አገራዊ ውይይቶች ሁል ጊዜም ቢሆን መዘጋጀት ያለባቸዉ እንዲሁም የድርድር ማዕቀፎችም መመቻቸት ያለባቸዉ በገለልተኛ፣ ተአማኒና ቅቡል አካል ነው፡፡ የዉይይቱ አመቻቾች ወይም አስተባባሪዎች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ መጠን የፖለቲካና ማኅበራዊ ቅቡልነት ያላቸው ሰዎች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ የዉይይት ሂደቱን በማስጀመር እና በድርድር ወቅት ውጥረቶችን በመቀነስና የሃሳብ ቅርቃሮችን መፍቻ የሚሆኑ አማራጭ መንገዶችን በመጠቆም ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆን ይገባቸዋል፡፡ 

በተለይ ከልሒቃን ጋር ባላቸው ግንኙነትና በተግባቦት ረገድ የአወያዮች፣ የድርድር አመቻቾች ወይም አስታራቂዎች አቅም የብሔራዊ ውይይቶችን የዉጤትና ትግበራ ሂደት በእጅጉ ሊቀርጽ ይችላል። እነዚህ አመቻቾች/አወያዮች ተሳታፊ ልሒቃኑን በዉጥረትና አስማሚ ጉዳይ በሚጠፋበት ጊዜ ዉስጥ እንኳ መደራደራቸውን እንዲቀጥሉ አሳምነዉ ወይም የህብረተሰቡን ስብጥር እና ወግ የሚያንፀባርቅ ሂደት ይቀርጻሉ።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት (ግለሰቦች ወይም ቡድኖች) ዙሪያ መለስ ተሳትፎን ለማስጠበቅ እና ሊፈጠሩ የሚችሉ አድሏዊ አመለካከቶችን ለማስወገድ፣ በሁሉም አካላት ዘንድ ተዓማኒ ሰብሳቢ ወይም አወያይ አካል መሰየም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሰብሳቢ አካል እንደየሁኔታዉ አንድ ግለሰብ፣ የሰዎች ስብስብ፣ ተቋም ወይም የተቋማቶች ጥምረት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል። 

ይህ ሰብሳቢ አካል በተቻለ መጠን በአብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቀባይነት ያለዉና የተከበረ መሆን ያለበት ሲሆን ከሚከናወነዉ ዉይይት ጋር ግልጽ የሆነ የጥቅም ግጭት የሚያመጡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ መሻቶች ወይም ግቦች ሊኖሩት አይገባም፡፡ በቅርብ ጊዜያት በቱኒዚያ እና በሴኔጋል የተካሄዱት ብሔራዊ ዉይይቶች በየሂደቶቹ ስኬታማነት የተመዘገበዉ ባብዛኛዉ በሰብሳቢዎቹ ተዓማኒነት በመሆኑ አወያዩ አካል ለዚህ ስኬት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ 

ስለሆነም በማኅበረሰቡ ዘንድና በሁሉም ተወያይ ወገኖች ሙያዊ ልምድና ተሞክሮ ያለው፣ ፅኑ እምነት የሚጣልበት፣ በሰፊው ተቀባይነት ያለው፣ ገለልተኛ፣ የተከበረና ግርማ ሞገስ ያለዉ፣ ማራኪ አቀራረብ የሚከተል ሰብሳቢ፣ አስታራቂ ወይም አመቻች መሰየም የብሔራዊ ውይይቱን ጥንካሬ በከፍተኛ ሁኔታ ሊወስን ይችላል፣ ይህም በሂደቱ ውስጥ መሳተፍ ያለውን ከባድነት እና የተሳታፊዎችን እምነት ያመለክታል፡፡

የቆይታ ጊዜ 

የብሔራዊ ውይይቶች የቆይታ ጊዜ መርዘምም ሆነ ማጠር ተሳታፊ አካላትን ስምምነት ላይ ለመድረስ አያስችላቸውም ወይም ከመስማማትም አያግዳቸውም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አገራት በተከናወኑ መሠል ሁነቶች ላይ የተሠሩ ግምገማዎች እንደሚያመለክቱት ብሄራዊ ውይይቶች አጫጭር በሚሆኑበት ጊዜ (ቢያንስ እስከ 250 ቀናት ማለትም ከአንድ አመት በታች) የተደረሱ ስምምነቶች የመተግበር የበለጠ እድል አላቸው። ስለሆነም ሚዛናዊ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸዉ ተደርጎ መቀረጽ አለባቸዉ፡፡

ለተሳተፊ አካላት ወይም ተዋናዮች ድጋፍ ሰጪ መዋቅሮች

የድጋፍ መዋቅሮች የሚባሉት በአለም አቀፍ፣ ክልላዊ ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተቋቋሙና በብሔራዊ ውይይት ውስጥ የተወሰኑ የተሳታፊ መደቦችን ወይም ክፍሎችን ሚና እና ተፅዕኖ ለማጠናከር ያለሙ አደረጃጀቶች ናቸዉ። እነኚህ የድጋፍ መዋቅሮች የዉይይቱ ተሳታፊዎች በአጀንዳ ከሚመስሏቸዉ ወገኖች ጋር ጥምረቶችን እንዲፈጥሩ ሊረዳቸው የሚችል ሲሆን፣ ይህም በጋራ አቋሞች ላይ በጋራ ለመስማማትና ተፅዕኖ መፍጠሪያ ጊዜና አቅም እንዲያጎለብቱ መንገድ ይከፍታል፡፡ እንዲሁም በብሔራዊ ውይይት ውስጥ ለመሳተፍ በሚያስፈልጉ ቴክኒካዊ መስፈርቶች ረገድ ድጋፍ ይሰጣሉ፣ እነዚህም እንደ የህግ ቋንቋ መረዳት፣ ለዉይይት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ የፅሑፍ ሰነዶችን ማዘጋጀት እና ማተም እንዲሁም በአጀንዳዎች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ናቸዉ። ይህም ተሳታፊ ቡድኖች ለቆሙለት የማኅበረሰብ መደብ ጥቅም አበክረዉ እንዲሟገቱ ያስችላቸዋል፣ ይህም በመጨረሻው ስምምነት ላይ የተወሰኑ ድንጋጌዎችን በማካተት የሚተረጎም ይሆናል።

በበርካታ አጋጣሚዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ መዋቅሮች ብሔራዊ ውይይቶችን አላግባብ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሰሩ ፖለቲካዊ አሻጥሮችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በመደገፍ የበኩሉን የግብር-አበርነት ሚና ተጫዉቷል፣ ይኽዉም እውነተኛ ሽግግርና ለውጥን ለማዘግየት እና ለአፋኝና ጨቋኝ መንግስታት እንዲሁም ለኃይል አማጺያን ተጨማሪ የሃሳብና የጊዜ ድጋፍን ለመግዛት ለታቀዱ ብሄራዊ ውይይቶች ድጋፍ ወይም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም ስለዓለም አቀፍ ተዋንያን ብሔራዊ ውይይትን ለመደግፍ ወይም ላለመደገፍ በሚወሰኑበት ጊዜ ብሔራዊ ውይይቱ በአገር መሪዎች በኩል በቅን ልቦና የታቀደ፣ በሐቀኛ የህዝብ ወኪሎች መካከል የሚካሄድ፣ በጽኑ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የታገዘ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡

በዉይይቱ በተካተቱ ተዋናዮች መካከል ጥምረት መፍጠር

በብሔራዊ ውይይቶች ክንዉን ሂደት ውስጥ ተመሳሳይ አቋም፣ የጋራ ጥቅምና ፍላጎትና አጀንዳ ባላቸዉ ተሳታፊዎች መካከል ጥምረት መፍጠር ተዋናዮቹ ድምፃቸው በጉልህ ተሰሚነት እንዲኖረዉና ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ኃይለኛ ስልት ሆኖ ተገኝቷል። አንዳንድ ጊዜ በብሔራዊ ውይይት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋናዮች እና ቡድኖች  ለአንድ የተወሰነ ጉዳይ ወይም ስልታዊ ፍላጎት በማሰብ እንደ አንድ ወጥ ስብስብ ለመደራደር ይሰበሰባሉ። ይህ ለምሳሌ በተለያዩ ልዑካን ሴቶች መካከል ወይም ባልታጠቁ እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል ሊከስት ይችላል።

ስለሆነም ከላይ ከሞላ ጎደል የተዘረዘሩ ነጥቦችን በጥልቀት በመረዳት መንግስትና ተሳታፊ ወገኖች በቀጣይ ለሚከናወነዉ የብሔራዊ ዉይይት መድረክ ተገቢዉን ድጋፍ በማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን በስፋትና በጥልቀት በማመቻቸት እንዲሁም ገቺ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ተንትኖ በመረዳትና በማስወገድ ስኬታማነቱን ማረጋገጥ የጋራ አገራዊ ኃላፊነታቸዉ ይሆናል፡፡

አስተያየት