ታህሣሥ 20 ፣ 2014

ሰሞኑን የተሰራጨው የጉንፋን መሰል ህመም ኦሚክሮን የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ተባለ

ኮቪድ 19

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የላብራቶሪ ምርመራ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በትላንትናው እለት የተመዘገበው ከ5 ሺህ ሰዎች በላይ በወረርሺኙ መያዝ ከኦሚክሮን ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ሰሞኑን የተሰራጨው የጉንፋን መሰል ህመም  ኦሚክሮን የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ተባለ

በአዲስ አበባ በስፋት የተሰራጨው የጉንፋን መሰል ምልክቶች ያሉት ህመም የኦሚክሮን የኮቪድ 19 ዝርያ የመሆን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያዎች ገለፁ።

የኮቪድ 19 ምላሽ ግብረኃይል ዋና አስተባባሪ የሆኑትን ዶክተር መብራቱ ማሴቦን አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ አዲስ የሆነ ወይም በጤና ሚኒስቴር የተለየ የጉንፋን ወረርሺኝ ባለመኖሩ መሰል የህመም ስሜቶች ከኮቪድ 19 ጋር የሚያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

"በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አሁን እየታየ የሚገኘው የጉንፋን መሰል ምልክት ያለበት ማንኛውም ግለሰብ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አድርጎ ነጻ (ኔጌቲቭ) ውጤት ካላገኘ በስተቀር ኮሮና ቫይረስ መሆኑን ማሰብ የተሻለ እና ተገቢ ነው።''

በህብረተሰቡ ዘንድ ከሚታየው መዘናጋት ጎን ለጎን የኮሮና ቫይረስ ተለዋዋጭ ባህሪያት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው ያሉት ዶክተር መብራቱ፤ ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት የሚኖራቸው እና የሞት ችግር የሚያስከትሉት አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያ የሆኑት ዴልታ እና ኦሚክሮን ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የብሔራዊ ግብረኃይሉ ዋና አስተባባሪ እንደገለጹት ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ ታማሚዎች ቁጥር እጅግ እየጨመረ ሲሆን በአንድ ሳምንት ውስጥ በጽኑ ህክምና ክፍል የሚገኙ ታማሚዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን በመጥቀስ የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። ያልተከተቡ ሰዎች፣ እድሜያቸው የገፉ ሰዎችና ተጓዳኝ ህመሞች ያሉባቸው ሰዎች ሞት እየጨመረ እንደሚገኝም ዋና አስተባባሪው ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

እየተመዘገበ ባለው አሃዝም በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድል ባለፈው ሳምንት ከነበርበት ከሚመረመሩት ውስጥ 3 በመቶ በእዚህ ሳምንት ወደ ከ28 እስከ 33 በመቶ ወይም አንድ ሶስተኛው በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑን ያመለክታል። በዓለም ጤና ድርጅት ስሌት ከ5 በመቶ ካለፈ አስቸጋሪ ነው ቢባልም አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከእዚህ የከፋ መሆኑን ዋና አስተባባሪው  አስረድተዋል።

እንደ ብሔራዊ የኮቪድ ምላሽ ግብረኃይል ዋና አስተባባሪ ገለጻ የቁጥሩ መጨመርም የኦሚክሮን ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ የምልክቶች መመሳሰል ያመለክታል ያሉ ሲሆን ቀደም ሲል የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ላይ ከሚስተዋለው የጀርባ ህመም ይልቅ ወደ ጉንፋንነት ማድላት፣ ከሳምባ ይልቅ ወደ አንገት አካባቢ ምልክቶች መታየትን በምሳሌነት አቅርበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የላብራቶሪ ምርመራ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በትላንትናው እለት የተመዘገበው ከ5 ሺህ ሰዎች በላይ በወረርሺኙ መያዝ ከኦሚክሮን ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።

የኦሚክሮን ዝርያ በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ ለማረጋገጥ የተለያዩ ምርምሮች እየተደረጉ ሲሆን በእዚህ ሳምንት አልያም በቀጣዩ ሳምንት ዉጤቱ ይፋ ይደረጋል ያሉት ዋና አስተባባሪው በመላው ዓለም በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘው የኦሚክሮን ዝርያ በኢትዮጵያ የመከሰቱ ጉዳይ ሰፊ እድል መሆኑንም ባለሙያው ገልፀዋል። 

አሁን ለሚታየው የወረርሺኙ መባባስ የሕብረተሰቡ ቸልተኛነት እጅግ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን ሁሉንም የጥንቃቄ እርምጃዎች መተግበር፤ በተለይም በመኖሪያ ቤቶች የሚደረጉ መሰባሰቦች ችላ ተብለዋል ተብሏል።

እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 10 ሚልየን የሚጠጋ ህዝብ ክትባት እንዲያገኝ የተደረገ ቢሆንም የክትባት ሽፋኑ አሁንም ከተጠበቀው በታች መሆኑን የገለጹት ዶክተር መብራቱ አሁንም ቢሆን ክትባት አማራጭ የሌለው ቀዳሚው መፍትሔ በመሆኑ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ በሙሉ እንዲሁም ክትባት ከወሰዱ 6 ወራት ያለፋቸው ሰዎችም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዙር ክትባት መዉሰድ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

አስተያየት