ሐምሌ 10 ፣ 2013

የኮቪድ-19 ጥንቃቄ፣ ከተጋነነ ፍርሃት እስከ መዘናጋት

City: Hawassaኮቪድ 19ማህበራዊ ጉዳዮች

የወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ መጥፋት ባልታወቀበት ሁኔታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጊዜያዊ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ በቸልታም ይሁን ባለማወቅ የኮቪድ 19 ስጋትን ወደጎን በመተው በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ተቋማት የመሰባሰቡና መቀራረቡ ሁነት ደርቷል።

የኮቪድ-19 ጥንቃቄ፣ ከተጋነነ ፍርሃት እስከ መዘናጋት

የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የካቲት ወር ውስጥ 2012 መከሰትን ተከትሎ በርካቶችን ማስደንገጡ ይታወሳል፡፡ አፍሪካን አይነካም፣ ኢትዮጵያን አይደፍርም፣ ነጭ ሽንኩርት እና ሚጥሚጣ መድኃኒቶች ናቸው የሚለው የተሳሳተ ልማዳዊ አባባል ተሽሮ የሞት እና በቫይረሱ የመጠቃት ዜናዎች የየዕለት ገጠመኞች መሆን መጀመራቸው ከአንድ ዓመት እጅግም ያልዘለለ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አንድ ሺህ ታማሚዎችን የሚያስተናግደው ሚሊንየም አዳራሽ ሞልቷል የተባለው በጥቂት ወራት ልዩነት ነበር፡፡ በከፊል የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከሐገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ተሻግሮ የክልል ከተሞችን ማዳረስ ሲጀምር እኛን አይነካም የሚለው መዘናጋት ባልተገባ ፍርሃት ተተካ፡፡

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው ለጠነከረ ሐገራት “አካላዊ ጥግግታችሁን ቀንሱ” የሚለው ትእዛዝ አስቸጋሪ ነበር፡፡ አብዛኛው ሰው በተጠጋጋ እና በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ መሆኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያግዙ መመሪያዎችን መተግበርን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ነዋሪ ዓለም አቀፉን ትእዛዝ በመተግበር እና የኖረ ልማድን በመተው ፈተና ላይ ወድቋል፡፡

ይህ ሁሉ ቢሆንም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ነዋሪ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ)፣ የእጅ ማጽጃ (አልኮል/ ሳኒታይዘር) ይጠቀም ነበር፡፡ በብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች የሚገለገሉ ተሳፋሪዎች እጃቸውን በአልኮል እንዲያጸዱ ተደርጓል፡፡ ሰዎች በሚተላለፉባቸው ጎዳናዎች እጅን በሳሙና የማስታጠብ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከመጫን አቅማቸው 50 በመቶ ቀንሰዋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ምርጫን የመሰሉ ሐገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችን ወደ ሌላ ጊዜ እስከማሻገርም ደርሷል፡፡ ይህ የቅርብ ጊዜ ትላንታችን ታሪክ ነው፡፡ አሁንስ? በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች እና ክልሎች ሁኔታው ተመሳሳይነት ቢኖረውም ይህንን ጉዳይ ከሐዋሳ ከተማ አንጻር ለመቃኘት እሞክራለሁ፡

ዛሬ?

ቫይረሱን 85 በመቶ ይከላከላል የተባለ ክትባት ተገኝቷል፡፡ ለሁሉም የዓለም ሀገራት በግዢ እና በእርዳታ እየተከፋፈለ ክትባቱን ለማዳረስ ጥረት ተደርጓል፡፡ የወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ መጥፋት ባልታወቀበት ሁኔታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጊዜያዊ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ አንዳንድ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የማኅበራዊ ትስስር ተቋማት፣ ሁነቶች፣ የደስታ እና የሀዘን ክንውኖች፣ ተቋማዊ ስብሰባዎች፣ ፌስቲቫሎች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ዓመታዊ እና ወርሀዊ ሀይማኖታዊ በአላት፣ በአጠቃላይ ሰዎች በብዛት ተሰባስበው የሚፈጽሟቸው ሁነቶች ተጀምረዋል፡፡ በቸልታም ይሁን ባለማወቅ የኮቪድ 19 ስጋትን ወደጎን በመተው መሰባሰቡና መቀራረቡ ደርቷል።

አዲስ ዘይቤ ጥቂት የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎችን፣ የማኅበራዊ ተቋማት አመራሮችን እና የጤና ባለሙያዎችን ለማነጋገር ሞክራለች።

ወይዘሮ ፅጓ ባዩ የሐዋሳ ከተማ የሴቶች መረዳጃ እድር ጸሐፊ ሲሆኑ አካላዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ የኮሮና ቫይረስ የስርጭት መጠንን ለመቀነስ ያለውን ጠቀሜታ አስታውሰው እድርተኛውም ሆነ ለቀስተኛው የጥንቃቄ ተግባራትን ማከናወን ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚመለከቱ ነግረውናል፡፡ “በአጭሩ በሽታው ተረስቷል ማለት ይቻላል፡፡ በቀብር ስነ-ስርአቶች ላይ የነበረው ጥንቃቄም እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ለቅሶ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰርግ ስነ-ስርአቶች ላይም ጥንቃቄው እንደመጀመርያው ቢቀጥል መልካም ነው›› በማለት ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡

ሌላው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ታምሩ ባዩ መዘናጋቱ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የሚታይ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ “ይሔኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከዚህኛው ይሻላል ማለት አይቻልም፡፡ መዘናጋቱ የሁሉም ነው፡፡ በሐይማኖት በዓላት፣ በስፓርታዊ ጨዋታዎች፣ በግብይት ስፍራዎች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በህዝብ ትራንስፖርቶች የጥንቃቄ መመሪያዎች ሲተገበሩ ዐይታይም፡፡ መንግሥትም ነገሩን ችላ ያለው ይመስላል” ብሎናል፡፡

የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ደግሞ “እንደ ባንክ ባሉ የመንግሥት ተቋማት ውሃ እና ሳሙና በር ላይ ይቀመጥ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው የእጅ ንጽህናውን ጠብቆ እና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አድርጎ ነበር የሚስተናገደው፡፡ ማስክ ካላደረጉ አናስተናግድም የሚል ጽሑፍም ለጥፈዋል፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ ተረስቷል፡፡ ለመታጠቢያ የተዘጋጁት ባልዲዎች ውሃ የላቸውም፡፡ የሳሙና ማስቀመጫዎቹም የሉም፡፡ ጥበቃዎችም ተገልጋዩ እንዲታጠብ አያስገድዱም”።

የቫይረሱን ወደ ሐገሪቷ ውስጥ መግባትን ተከትሎ በግማሽ አቅማቸው ይጭኑ የነበሩት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በአሁኑ ወቅት ከመጫን አቅም በላይ እየጫኑ ነው፡፡ ሳኒታይዘር ወይም አልኮል ሳያስነኩ ወደ ተሽከርካሪያቸው የማያስገቡ ሾፌሮች ማስክ ላላደረገ ሰው ግድ ማጣት ጀምረዋል፡፡ “ቸልተኝነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የተማረውም ያልተማረውም፣ የከተማም የገጠርም ነዋሪ፣ ሁሉም ዝንጉነት ውስጥ ገብቷል፡፡ መንግሥት የጥንቃቄ መመሪያዎች በአግባቡ መጠበቃቸውን በተመለከተ ሲያካሂድ የነበረውን ክትትል ማጠናከር ይገባዋል” የሚል ሐሳብ የሰጡን የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማሩ አቶ ውብሸት አያሌው ናቸው፡፡ 

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎችን ሐሳብ የምትጋራው ወ/ት ቤዛዊት በቤተሰቧ ያለን የስኳር ታማሚ እንደ ምሳሌ በማንሳት ከተጓዳኝ ሕመሞች ጋር የሚኖሩ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ሳይቀሩ የመዘናጋቱ አካል ስለመሆናቸው ነግራናለች፡፡

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዶ/ር ዋዜማ ውቤ “አሁን ላይም በኮቪድ -19  የሚመጡ ኬዞች አሉ” ይላል፡፡ “በሽታው በባህሪው ተለዋዋጭ ነው። ይህም አሁን ላይ ሰዎች ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ሲከውኑ፣ ሲሰባሰቡ፣ በስራ ቦታዎች እና የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጭምር ያለ ጥንቃቄ መንቀሳቀሱ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል፡፡ መጠንቀቅን የህይወት መመሪያችን ማድረግ ሁልጊዜም የማንተወው ተግባራችን መሆን አለበት” የሚል ምክር አስተላልፏል።

አስተያየት