መስከረም 25 ፣ 2015

ኦሜድላ- የቤኒሻንጉሏ የአፄ ኃይለስላሴ ማስታወሻ

City: Assosaታሪክአስተያየት

ወደ ዲዛ ዛፍ ተጠግተው ሲመለከቱ በትልቁ የተቀረፀ አቀራረፅ ቀ.ኃ.ሥ የሚል እና በውል የማይለይ ዓመተ ምህረት ዛፉ ላይ ተቀርፆ ይታያል

Avatar: Afework Solomon
አፈወርቅ ሰለሞን

አፈወርቅ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪ ሲሆን የተለያዩ ፅሁፎችን በአዲስ ዘይቤ ያጋራል

ኦሜድላ- የቤኒሻንጉሏ የአፄ ኃይለስላሴ ማስታወሻ
Camera Icon

ፎቶ፡ ዘ ታይምስ (የጉባ ወረዳ ገፅታ)

የቀ.ኃ.ስ (የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በር በመባል ትታወቃለች። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በ330 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው የኦሜድላ ቀበሌ። ኦሜድላ በጉባ ወረዳ ካሉት 18 ቀበሌዎች መካከል አንዷ እና ታሪካዊ ቀበሌም ጭምር ናት። ከጉባ ወረዳ ዋና ከተማ ማንኩሸ በ125 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ስትሆን በዚች ቀበሌ አብረሙላ በመባል የሚታወቁት የጉሙዝ ጎሳዎች የሚገኙ ሲሆን የመግባቢያ ቋንቋቸው አብረሙለኛ ይባላል።

በርካታ የሀገራችን ድርጅቶች፣ ትላልቅ ሆቴሎች እና አንዳንድ የሥራ ተቋማት የዚህች ቀበሌ መጠርያ የሆነውን ኦሜድላ የሚለውን ስያሜ ለድርጅቶቻቸው መጠርያነት  ተጠቅመውበታል።

የኦሜድላ ቀበሌም የምትዋሰነው የሱዳን፣ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው።

ኦሜድላ ከስያሜዋ ብንጀምር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደት ከቆዩባት ከእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በሱዳን በኩል አንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ከሱዳንም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በዚች ቀበሌ ውስጥ በማለፍ ነበር። በመሆኑም ከስደት ሀገር ሲመጡ መጀመሪያ የረገጧት የኢትዮጵያ መሬት ይህችው ዛሬ የማስቃኛችሁ የኦሜድላ ቀበሌ ናት።

አሜድላ ማለት በአረብኛ ፍቺው እድለኛ ማለት ሲሆን ከኢትዮጵያ መሬቶች ውስጥ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ መጀመሪያ የረገጧት ቦታ በመሆኗ እድለኛ ቦታ በመሆኗ ኦሜድላ የሚለው ስያሜ እንደተሰጣት የአካባቢው የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ።

በተቃራኒው ግን ከሌሎች አፈታሪኮች የሚሰማው ደግሞ ይህ ስያሜ ለቀበሌዋ የተሰጠው አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ እዚህ ስፍራ ከመምጣታቸው በፊት እንደነበረ እና ከምን አንፃር ይህ ስያሜም አንደተሰጠ በውል እንደማይታወቅ ነው የሚናገሩት። ምንም እንኳን ስያሜዋ አሁን ከማስቃኛችሁ ታሪካዊ ቦታ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም ጉዳዩ አያጣላንም። ከዚች የቀኃሥ በር ወይም ኦሜድላ ቀበሌ አምስት ያህል ደቂቃዎችን አንደተጓዙ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን የሚያካልል ትልቅ ወንዝ ያገኛሉ። ከወንዙ ዳርም “ዲዛ” የሚባል ግዙፍ ዛፍ ይገኛል።

የዲዛ ዛፍ ምናልባትም በውፍረታቸው በዓለም ከሚታወቁ ዛፎች መካከል ቀዳሚው ሳይሆን እንደማይቀር ይነገራል። የጉባ ወረዳም በዚህ የዲዛ ዛፍ በስፋት ይታወቃል።

በዚህ በኦሜድላ ቀበሌ የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ የሚገኘውን እና ዛሬ የማስቃኛችሁን ታሪካዊውን የዲዛ ዛፍ በሩቅ ሲመለከቱት እንደማንኛውም ዛፍ በግዝፈት ይታያል። ጠጋ ሲሉም መዝጊያ ያልተሰራለት በር በዛፉ መሀል ይታያል። አሁንም ወደ ዛፉ ተጠግተው ሲመለከቱት ደግሞ በትልቁ እና በማራኪ የፈደል አቀራረፅ ቀ.ኃ.ሥ የሚል እና በውል የማይለይ ዓመተ ምህረት ዛፉ ላይ ተቀርፆ ይታያል። በዚህ የዲዛ ዛፍ በር ላይ ከዛፉ አካል በእጅ ተቦርቡረው የተሰሩ ሁለት መቀመጫዎች ይታያሉ። ወደ ዛፉ ውስጥ ሲገቡም እስከ 20 ሰዎችን ሊያስተናግድ የሚችል እና ጣሪያ የሌለው የዛፍ ዋሻ ሆኖ ያገኙታል። ከዚህ ዛፍ ተቦርቡሮ ከተሰራው መቀመጫ ላይ ሲቀመጡም ከፊት ለፊቱ የሁለት ሀገራት ድንበር የሆነው ትልቁ ወንዝ የተፈጥሮ አየሩን እየለገሰ የአካባቢውን መልክአ ምድር እያስጎበኘ ውብ የተፈጥሮ ሙዚቃን በአዕዋፍት ዜማ እያጀበ የተፈጥሮን ውበት በሰፊው ያስቃኛል።

ግንቦት 13/1933 ዓ.ም. አካባቢ ኢትዮጵያ ወራሪው ጣሊያንን ከሀገር ካስወጣች በኃላ ንጉሠ ነገሥቱ ተሰደው አምስት ዓመታት ያህል ከኖሩበት እንግሊዝ ሀገር በእንግሊዝ  ጀኔራሎች እና ወታደሮች ታጅበው በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት ወቅት ነበር።

ታድያ ንጉሡም በእነዚህ በውጭ ጄነራሎች በክብር ታጅበው ሲመጡ መጀመርያ የረገጧት የኢትዮጵያ መሬት ኦሜድላ ስትሆን በዚች ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው የዲዛ የዛፍ ቤት ውስጥ ለሰባት ያህል ቀናት በማደር ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ይነገራል።

በወቅቱ የጉባ አካባቢ አስተዳደር የነበሩት እና በንጉሡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተሰሚነት፣ ታማኝነት እና ተቀባይነት የነበራቸው ደጃዝማች ባንጃው /አቡሽክ/ ወደ ቦታው በመሄድ ንጉሡን ተቀብለው መንገድ በመምራት በቻግኒ አድርገው ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ መርተዋቸዋል። በዚህም የተነሳ ይመስላል የቤኒሻንጉል እና የአማራ ክልል አዋሳኝ ከተማ የሆነችው ቻግኒ በቅፅል ስሟ የቀ.ኃ.ስ በር በመባል የምትታወቀው።

በነገራችን ላይ ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ መሬት ወደሆነችው ወደ እዚህች የኦሜድላ ቀበሌ ከመምጣታቸው አስቀድመው የአካባቢውን ሰላም እንዲቃኙላቸው በርካታ ወታደሮችን ወደ ስፍራው ከላኩ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ነበር ወደ ኢትዮጵያ ኦሜድላ የመጡት።

ንጉሡም በዚች ቀበሌ በቆዩባቸው 7 ቀናት ውስጥ ሕብረተሰቡን ሊያገለግል የሚችል ትምህርት ቤት በዚሁ አካባቢ አስገንብተዋል።

ምንም እንኳን ትምህርት ቤቱ ለአካባቢው ማሕበረሰብ ለረጅም ጊዜያት አገልግሉት ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም በእንክብካቤ ጉድለት የተነሳ የቤቱ ጣራ በመፈራረሱ አገልግሎት መስጠቱን በማቆሙ ይህንን ጽሑፍ እስካዘጋጀሁበት ሰዓት ድረስ የአካባቢው ተማሪዎች ይህንን ትምህርት ቤት በመተው በሳር በተሰራ የዳስ ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር። 

ይህ የቀ.ኃ.ስ ማስታወሻ የሆነው የዲዛ ዛፍም እስካሁን ምንም ዓይነት ትኩረት አልተሰጠውም። ስለ ቦታው እንኳን አብዛኛውን የወረዳውን ነዋሪዎች ብትጠይቅ ምንም መረጃ የላቸውም።

ስለ ስፍራው ታሪካዊነት እንወቅ እንኳን ቢባል ምንም የምናገላብጠው መጽሐፍ ወይም የታሪክ መዝገብ የለም። ይህ ደግሞ ለቦታው ምንም ዓይነት ትኩረት አለመሰጠቱን እና ምንም ዓይነት ጥናት እንዳልተካሄደበት አመላካች ነው። ታሪክ እንዲህ ሲሆን የታሪክ መሸራረፍን እና ልዩነቶችን ያመጣል።

አንዱ ፅሀፊ “እንዲህ ተባለ” ሲል ሌላው ጸሐፊም “እንዲህ ነበረ፡ ሲል በመሀከል የታሪክ መዘበራረቅን ያስከትላል።

ይህ ቦታ ደግሞ ታሪካዊ ቦታ ቢሆንም ምንም ዓይነት ጥበቃ እና እንክብካቤ አልተደረገለትም።

ይህን ለማለት የቻልኩበት ምክንያትም በዚህ ዛፍ ላይ በወቅቱ ከተፃፉ ማስታወሻዎች ባሻገር በየጊዜው አዳዲስ ጽሑፎች ዛፉ ላይ መቀረፃቸው ነው። ከዚህ ውጪም ንጉሱ መቼ ወደዚህ ስፍራ እንደመጡ በትክክል የሚያመላክተው ቀን በዛፉ ውፍረት ምክንያት መጥፋቱ ነው።

በወቅቱ አነዚህ ነገሮች ተመዝግበው ተይዘው ቢሆን  “አሉ” እና “ተባለ” የሚሉትን ግምቶች በታሪክ ጽሑፎቻችን ባልተጠቀምን ነበር። ነገር ግን ምንም ዓይነት የተያዘ መረጃ ባለመኖሩ እነዚህን የግምት መግለጫዎች ለመጠቀም ተገደናል። ይህ ደግሞ የታሪክ መዛባትን ማስከተሉ እሙን ነው።

እነዚህ የተሸራረፉ መረጃዎች ደግሞ ጥናት ለመስራት ለሚፈልጉ አካላት ፍንጭ ከመስጠት ባሻገር የጎላ ፋይዳ አይኖራቸውም።

ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላትም እንደነዚህ ዓይነት ታሪካዊ ሁነቶችን የመመዝገብ፣ የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና የማስተዋወቅ ስራዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የመሥራት ግዴታ የነበረባቸው ቢሆንም ትኩረት ሰጥተው መረጃዎችን መዝግበው ሲያስቀምጡ ግን አይታይም።

ለምሳሌ ያህልም በወረዳው ላይ የተለያዩ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ እንዲሁም ጥናት ያልተደረገባቸው እና ወደፊት በጥናት ሊለዩ የሚገባቸው ጉዳዩች በስፋት የሚገኙ ቢሆንም ትኩረት ሲሰጣቸው አይታይም።

ይህን የወረዳውን ድክመት ካነሳሁ አይቀር በዚህ ወረዳ የታዘብኩት አንድ ነገር ቢኖር በወረዳ የሚገኙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በብዛት የሚገኙት በግለሰቦች ቤት እንክብካቤ ሳይሰጣቸው መሆኑ አግራሞትን ያጭራል።

ይህን በተመለከተ ችግሩን በመረዳት እና ለቅርሶቹ ሙዝየም በመገንባት ቅርሶቹን በማሰባስብ እና በመጠበቅ ለጎብኚዎች እና ለአጥኚዎች ክፍት መደረግ ይገባል።

ከዚህም ባሻገር ለአንድ ሀገር እና ማኅበረሰብ ታሪክና ማንነቱን ከምንም ነገር በላይ የሚገልፁ በመሆናቸው ቅርሶቹን በሚገባ ጠብቀን ማንነታችንን ማቆየት እና ለትውልድ በማውረስ የቱሪዝም የገቢ ምንጭ የማድረግ ኃላፊነት አለብን።

አስተያየት