መስከረም 25 ፣ 2015

የተዘነጉት የኢትዮጵያ መምህራን

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ መምህራን ከማስተማር ስራቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መስመር በመቀየር ትልቁን ድርሻ ውስደዋል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የተዘነጉት የኢትዮጵያ መምህራን
Camera Icon

ፎቶ፡ ፋና ብሮድካስቲንግ

በአንድ ወቅት አንድ ከፍተኛ የመንግስት እንደራሴ ስለመምህርነት ሞያ ሲናገሩ “የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣ ወሰዳት አስተማሪ” ሲባል በልጅነታቸው እንደሰሙ በመጥቀስ ባደጉበት አካባቢ ህዝቡ ለመምህራን የነበረውን ላቅ ያለ ክብር ያስታውሳሉ። 

መምህርነት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ አንጋፋ ሞያ ነው። ለዚህም ይመስላል ብዙዎች መምህርነት የሙያዎች ሁሉ አባት” ሲሉ የሚደመጠው። በኢትዮጵያ ከጥንት ልማዳዊ፣ ሐይማኖታዊ ትምህርቶች እስከ ዘመናዊ ትምህርት ድረስ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መምህራን በየዘመኑ ዘርፈ ብዙ አስተዋጾ አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ከማስተማር ስራቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያን ፖለቲካና ታሪክ መስመር በመቀየር ትልቁን ድርሻ ወስደዋል። በተለይ በ1960ዎቹ የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ከሌላው የሙያ ዘርፍ በላቀ መልኩ መምህራን ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ ታሪክ ያስረዳል። 

ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ደረጃ ተሰሚነት የነበረው የመምህራን ማህበር ዛሬ ላይ ድምጹ አይሰማም። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉት መምህራን አሁን ካለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና ተቀያያሪ ሁኔታ አንጻር እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። 

ለአብነትም በቅርቡ በዩኒቨርሲቲ መምህራን እና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል የተፈጠረውን እና እስከ አሁንም የዘለቀው የደሞዝ ማሻሻያ ጥያቄን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

የተባበሩት መንግስታት በአውሮጳዊያኑ 1993 ዓ.ም በዓለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) ሀሳብ አመንጪነት በየዓመቱ ጥቅምት 5ን ዓለም አቀፍ የመምህራን ቀን ሲል ሰይሞታል።

የመምህራን ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ለ22 ጊዜ “The Trasformation of Education Begins with Teachers” (የትምህርት ለውጥ በመምህራን ይጀምራል) በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

የኢትዮጵያ መምህራን ብዛት እና አበርክቶ ተቆጥሮ ባያልቅም ለትውስታ ያክል ብቻ በጣም ጥቂቶቹንና በአስተዋፅዖዋቸው አንጋፋዎቹን በዓለማቀፉ የመምህራን ቀን ላይ ልናስታውሳቸው ወደናል፤

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

“የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ” መማሪያ መጽሐፍትን ያደራጁ እና ለረጅም ዓመታትን ያስተማሩ ብርቱ መምህር ናቸው። መምህር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ፖለቲከኛ ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሚሉት ማዕረጎች ከስማቸው ፊት ቢቀመጥ ሰው የማይከራከርበት ስራዎቻቸው ናቸው። 

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በእድሜያቸው ሙሉ የትምህርትን እና የምሁርነትን ልዕልና በትውልድ አዕምሮ ውስጥ ቀርጸው ያለፉ ብርቱ የቀለምም የህይወትም መምህር ናቸው።

ሚያዚያ 15/1922 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ አካባቢ የተወለዱት ፕሮፌሰር መስፍን የትምህርት ህይወታቸው የተጀመረው በቄስ ትምህርት ቤት ነው። 

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን አዳሪ ት/ቤት፣ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በ21 ዓመታቸው በእቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት የመምህርነት ስራቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እስከ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የዘለቀ በመምህርነት እና ተመራማሪነት ለረዥም ዓመታት ሰርተዋል።

በህንድ ፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፍልስፍን እና ጂኦግራፊ የሰሩት ፕ/ር መስፍን በማስከተል ሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአሜሪካው ክለርክ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ አግኝተዋል::

በ1950ዎቹ በካርታና ጅኦግራፊ ኢንስቲትዩት ሥራቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰር መስፍን “ለምንድን ነው የዕውቀት ጠላት የሆንነው?” በማለት በመጠየቅ ይታወቃሉ።

በሰማኒያዎቹ ትውልዶች ከመምህርነታቸው ይልቅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው እና ዘጠናዎቹ በፖለቲካ ታሳትፏቸው የሚታወቁት ፕ/ር መስፍን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው An introductory geography of Ethiopia , Preliminary Atlas of Ethiopia, an Atlas of Ethiopia እና የመሳሰሉ የኢትዮጵያን ጂኦግራፈ የሚያሳዩ መጽሐፍትን ጽፈው ትውልድን አንጸውበታል።

 

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ

(የባዮሎጂ መማሪያ መጽሐፍትን ያዘጋጁ የባዮሎጂ ምሁር)

በሀዲያ ዞን መጋቢት 2/1942 ዓ.ም ሾኔ ከተማ የተወለዱት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሾኔ፣ በሆሳዕና እና በኩየራ አድቬንቲስት ት/ቤት ተምረዋል። 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዳማ ገላውዴዮስ ትቤት ተከታትለዋል።

በ1959 ዓ.ም የያኔውን ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉት ፕ/ር በየነ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን  አግኝተዋል።

በ1965 ዓ.ም ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እጅ በእዮቤልዩ ቤተ-መንግስት ከተመረቁ የመጨረሻዎቹ ተማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። እንደተመረቁም በዩኒቨርሲቲው በረዳት መምህርነት ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። 

የአራት አስርት ዓመታት የማስተማር፣ የጥናት እና ምርምር እንዲሁም የመጽሐፍ ዝግጅት ላይ የቆዩት አንጋፋው መምህር በትምህርት አመራር እና የፖለቲካ ተሳትፏቸው የሽግግር መንግስቱ ምክትል ትምህርት ሚኒስቴር እስከ መሆን ደርሰዋል።

የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ ሀገር በባዮሜዲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የተከታተሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የባዮሎጂ ዲፓርትመንት ዲን ሆነው አገልግዋል።

በብዙ ህዝብ ዘንድ በሚታወቁበት የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው የህዝብ ተወካይ ሆነው አገልግለዋል። ፕ/ር በየነ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ምርምር ዋና ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡

መምህር አትርሳው ጣሰው  

አንድ ቀን ብሪትሽ ካውንስል ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የተፈጠረች ክስተት በ1980ዎቹ ለነበሩ ተማሪዎች ልዩ ትዝታን ፈጥራ አልፋለች።

መምህሩ ለማስተማር በገቡበት አፍታ በክፍሉ ውስጥ የተቀደደ የፔሬዲክ ቴብል ተመለከቱ። “ለተማሪዎቼ ከዚህ የተሻለ ነገር ማዘጋጀት አለብኝ” በማለት ለኬሚስትሪ ትምህርት ወሳኝ የሆነውን ፔሬዲክ ቴብል ለተማሪዎች በሚመች መልኩ አዘጋጁ። ይህ ያዘጋጁት ፔሬዲክ ቴብል በወቅቱ ገበያ እስከ 2 ብር እንደተሸጠ ይነገራል።

“እውቀት የማያልቅ ጸጋ መሆኑን አትርሳው … አትርሳው ጣሰው” የሚል የግርጌ ጽሑፉም ለብዙዎች በተነበበ ቁጥር በልብ ውስጥ እያቃጨለ የእውቀትን ብርታት የሚያስተጋባ ዐ/ነገር ነው።

ተመርቀው ከተመደቡበት ከጋሞ ጎፋ ት/ቤት ጀምሮ በየካቲት 12 (መነን) ት/ቤት፤ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ት/ቤት፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ት/ቤት፤ በነገው ሰው አካዳሚ እና በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ በኬሚስትሪ መምህርነት ሰርተዋል። 

በመምህር አትርሳው የተሰናዳው ፔሬዲክ ቴብል ስራቸው የህትመት ፀሐይ ከወጣለት 1981ዓ.ም በኋላ ሌላ በተማሪዎች የኬሚስትሪ ትምህርት ላይ የተመለከቱትን ችግር መፍትሔ ለማበጀት የቆረጡት መምህሩ በ1982 ዓ.ም “Calculations in Chemistry” የሚል መጸሐፍ አሳትመዋል። 

ከዚህ ሌላ “Understanding Secondary School Chemistry” በሚል ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተጨማሪ የመርጃ መጸሐፍ ያዘጋጁ ሲሆን ከዓመታት በፊትም “ምርጥ የኬሚስትሪ መምህር” ተብለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው

(የህጻናት መጸሐፍ ደራሲው መምህር)

ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው በሩሲያ ሞስኮ 1960 ዓ.ም ነው የተወለዱት። በ1979 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩቨርሲቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ-ጽሑፍ በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ተሸላሚ ነበሩ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሀገረ- እንግሊዝ እንዲሁም ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ ፕቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ -ጽሑፍ አግኝተዋል።

በአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ በያኔው ከተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ለ9 ዓመታት ያስተማሩት ዶ/ር ማይክል ከ40 በላይ የህጻናት መጽሐፍት ጽፈዋል። ዶ/ር ማይክል ከአሳተሟቸው መጽሐፍት መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፣

Tales of Toteet፣ Butu Lord Of The Ants፣ A Cluster Of Rejections፣ Shadows፣ Alemayehu፣ Adey’s Pigeons ፣ Cheray’s Great Run፣ Tales of Abuna Aregawi፣ Welcome To Addis፣ Animal Tales From Sidama ፣Blame Me Not፣ Traditional Sidama Tales፣ የሚጣ ሚስጥር፣ ካሣ፣ ኩኩሉ እና ሌሎችንም መጽሐፍት አዘጋጅተዋል።

በ45 ዓመታቸው ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በተርጓሚነት፣ በኤክስፐርትነት፣ ኮርሶችን በመቅረጽና ማንዋሎችን በማዘጋጀት ሙያዊ አገልግሎት ላይ ተሳትፈዋል።

መምህር ዘነበ ደነቀ

በ1980ዎቹና 90 ዎቹና አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደ ሂሳብ ትምህርት አጋዥ መፅሃፍት አድርገው የተጠቀሙባቸውን Mathematics A Systematic Approach ተከታታይ መጻህፍት አዘጋጅተው ለተማሪዎች በማድረስ የሚታወቁት መምህር ዘነበ ደነቀ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቭዥን ላይ የሂሳብ ትምህርትን ለታዳጊዎች ያስተምራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በአስቴር ነጋ የትምህርት አጋዥ መጽሐፍት አታሚ ተቋም ውስጥ የሒሳብ መጽሐፍትን አዘጋጀተው ለተማሪዎች አቅርበዋል።

አስተያየት