መስከረም 26 ፣ 2015

በ12ተኛ ክፍል ፈተና ምክንያት ከግቢ እንዲወጡ የተደረጉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለችግር ተጋልጠናል አሉ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮች

በተለይ ከትግራይ ክልል፣ ከአማራና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች እንዲሁም ከወለጋ ዞኖች መጥተው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ከ850 በላይ ተማሪዎች ለ15 ቀናት አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በ12ተኛ ክፍል ፈተና ምክንያት ከግቢ እንዲወጡ የተደረጉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለችግር ተጋልጠናል አሉ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ሀገር አቀፉን የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንዲሰጥ ወስኗል። ይህን ተከትሎ ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች የመጡ እና ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የማይችሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለ15 ቀናት የሚሆን አስቸኳይ የምግብ እና የመጠለያ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ያቦነሽ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል።

“የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ውስጥ ፈተናቸውን ይወስዳሉ በመባሉ እኛ ከግቢዉ እንድንወጣ ተደርገናል” የሚሉት ተማሪዎቹ መሄጃ በማጣት ግራ መጋባታቸውን ገልፀዋል። ሀገር አቀፉ ፈተና ተጠናቆ ወደ ግቢ እስኪመለሱም ድረስ ለቀጣይ 15 ቀናት ምግብ እና መጠለያ እንዲመቻችላቸዉ የሚመለከተው አካላት ድጋፍ ጠይቀው መልስ እየተጠባበቁ ነው

ጦርነት እና አለመረጋጋት ካለባቸው አካባቢዎች ማለትም ከትግራይ፣ ከአማራና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች እንዲሁም ከወለጋ ዞኖች ለትምህርት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ከ850 በላይ ተማሪዎች በአሁን ሰዓት እርዳታ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት እና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሚካኤል ያቦነሽ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረው “ከትግራይ ክልል ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ውጪ በሌሎች የትምህርት ተቋማት ውስጥ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ነገር ግን በተከሰተው አለመረጋጋት ቤተሰቦቻቸው ጋር መሄድ ያልቻሉ ተማሪዎች ለ15 ቀናት የሚሆን አስቸኳይ የምግብ እና የመጠለያ እርዳታ ይፈልጋሉ” ብሏል።

ይህ ችግር ሊፈጠር የቻለዉ መንግስት የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 30/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሰጠት በመጀመሩ “ማንኛውም ተማሪ በተቋሙ ውስጥ እንዳይኖር” ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ተናግሯል።

አሁን በኢትዮጵያ ከ 45 በላይ ዩኒቨርስቲዎች በመደበኛነት ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ላይ የሚገኙ ሲሆን በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ግጭት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን በግቢው ውስጥ እንዲቆዩ ማድረጋቸው ይታወቃል። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ከትግራይ ክልል እና ከአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ወደ ሐዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የመጡ ተማሪዎች እንደሚሉት በሀገሪቱ ጦርነት ከተከሰተ ወዲህ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው እንደማያዉቁ እና የእረፍት ቀናትን በዩኒቨርስቲዎቹ  እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል ።

በ18 ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ከ850 በላይ ተማሪዎችን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትር የትምህርት ተቋማቱ ለተማሪዎቻቸው አማራጮችን እንዲፈልጉ ማሳሰቡ ተሰምቷል።

ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ አብዛኛው ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሚካኤል “ችግሩን ለመፍታት በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በጎ ፍቃደኞች ተመድበው ለተማሪዎች የአደራ ቤተሰብ እየተፈለገ ነዉ” ብሏል። 

አንድ ቤተሰብ ለ15 ቀናት አንድ ተማሪን እንዲሁም ድርጅቶች በፍቃደኝነት 10 ተማሪዎችን እንዲያግዙ የማግባባት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተማሪ ሚካኤል ገልጿል። 

ለተማሪዎቻቸዉ በራሳቸው ወጪ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ እና ሌላ አማራጭ ያላፈላለጉ ዩኒቨርስቲዎች መኖራቸውም ታውቋል። ከእነዚህ መካከል የጂንካ፣ የዋቻሞ፣ የወራቤ እና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲዎች ለ15 ቀናቶች ተማሪዎች በአካባቢው ላይ እንዲቆዩ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል።

ትምህርት ሚኒስተር ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የ12ተኛ ክፍል የሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና በሁለት ዙር ይሰጣል። ለዚህም ከመስከረም 26 ጀምሮ ተፈታኞች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርስቲ መግባት እንደሚኖርባቸው ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።

አስተያየት