መስከረም 26 ፣ 2015

የወላይታ ድቻ ክለብ በስሜት ተነሳስቶ የክለቡን ስያሜ ቀይረዋል ያላቸውን ስራ አስኪያጅ ከኃላፊነታቸው አነሳ

City: Hawassaወቅታዊ ጉዳዮችስፖርት

በክለቡ ስራ አስኪያጅ የተደረገው የስያሜ ለውጥ የተሻረ መሆኑንና የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ በቀድሞ ስያሜው የሚቀጥል መሆኑን ክለቡ አስታውቁዋል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የወላይታ ድቻ ክለብ በስሜት ተነሳስቶ የክለቡን ስያሜ ቀይረዋል ያላቸውን ስራ አስኪያጅ ከኃላፊነታቸው አነሳ
Camera Icon

ፎቶ፡ Addis Zeybe

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች የብሔር እና የሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸዉ ስያሜዎችን እንዲቀይሩ ማለቱን ተከትሎ የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ መጠሪያውን ወደ "ድቻ ስፓርት ክለብ" መቀየሩን የሚገልፅ ደብዳቤ ስህተት መሆኑ ተገለፀ።

በስፖርት ክለቡ ፕሬዝዳንት በአቶ ወንድሙ ሳሙኤል በተፃፈ እና ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተላከዉ ደብዳቤ ላይ ወላይታ ድቻ ስያሜዉን ዲቻ ስፖርት ክለብ በሚል ማስተካከያ ማድረጉን ማሳወቃቸው ተመላክቷል።

ለአዲስ ዘይቤ በደረሰዉ እና በስራ አስኪያጁ ተፃፈ በተባለዉ ደብዳቤ ላይ ከመስከረም 11 ቀን 2015 ዓ.ም. "የዞኑ ስራ አስፈፃሚ እና የክለቡ የቦርድ አባላት በክለብ ስያሜ ዙሪያ ተወያይተዉ ከዚህ ቀደም በወላይታ ድቻ ክለብ የሚጠራውን ስያሜ ወደ ድቻ ስፖርት ክለብ በሚል እንዲቀየር ዉሳኔ ማስተላለፉን" ይገልፃል።

በደብዳቤዉ ላይ ይህ ይባል እንጂ  ቦርዱ ግን የስያሜ ለዉጡ የወላይታ ህዝብን እና ደጋፊዎችን ያሳዘነ ነዉ ብሎታል።

የእግር ኳስ የፌዴሬሽን የክለብ በስያሜዉ ላይ ለዉጥ ማድረጉን ተቀብሎ ያፀደቀ ሲሆን የፌዴሬሽኑ መመሪያ በመቀበል የወላይታ ድቻ የመጀመሪያው ክለብ መሆኑን ገልጿል።

በ 2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘዉ ክለቡ በአዲሱ ስያሜ መጠራት መጀመሩን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃዉሞ ሲያስተናግድ መቆየቱን አዲስ ዘይቤ ከደጋፊዎቻቸዉ ሰምታለች።

በትላንትናው ዕለት መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ይህን አስመልክቶ ዉይይት ያደረገዉ የክለብ ቦርድ የወላይታ ድቻ እግርኳስ ክለብ ስያሜ ለውጥን መሻሩን የሚገልፅ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል ።

"በክለቡ ስራ አስኪያጅ የተደረገው የስያሜ ለውጥ የተሻረ መሆኑን እየገለፅን የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ በቀድሞ ስያሜው የሚቀጥል መሆኑን እናሳዉቃለን" ይላል ደብዳቤው።

ከዚህ በተጨማሪ በአቶ ወንድሙ ሳሙኤል የተፃፈዉ ደብዳቤ የአሰራር ስርዓትን የጣሰ እና በግለሰብ ስሜት የተፈረመ እንዲሁም የተፃፈ መሆኑን በመጥቀስ በዞኑ ስራ አስፈፃሚ እና ቦርድ አባላት ዉይይት ያልተደረገበት እንደሆነም ጠቅሷል።

ደብዳቤዉን ለፌዴሬሽኑ ፅፈዋል የተባሉት የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንድሙ ሳሙኤል መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ ሲደርሳቸዉ በምትኩ ደግሞ አቶ ምትኩ ኃይሌ የክለቡ ጊዜያዊ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ መወከላቸዉን ለማወቅ ተችሏል።

አስተያየት