በትግራይ ትልቁ የህዝብ ሆስፒታል የሆነው የመቀሌ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በትግራይ ያሉ የስኳር ህሙማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ እንደሆኑ በመግለጽ ለነዚህ ታማሚዎች የሚውል የስኳር በሽታ ህክምና ግብአቶች በአስቸኳይ እንዲቀርብላቸው ተማጽኗል።
ሆስፒታሉ ለኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር በላከው ደብዳቤ በትግራይ የስኳር ህመምተኞች የተጋረጠባቸውን አስከፊ ሁኔታ እና ያጋጠመውን ከፍተኛ የስኳር በሽታ ህክምና ግብአቶች እጥረት በዝርዝር በመግለጽ የህክምና አቅርቦቶች በአስቸኳይ እንዲላክለት ጠይቋል።
“እርዳታን በአየር በማድረስም ሆነ በሚቻለው በየትኛውም መንገድ የስኳር በሽታ ህክምና አቅርቦቶችንና በደምስር የሚወሰድ የግሉኮስ ፈሳሽ መድሃኒቶች እንዲላኩልን በማድረግ የሰው ልጅ ከዚህ አስከፊ ሁኔታ መውጣት ይችል ዘንድ ሚናውን እንዲጫወት የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበርን እንማፀናለን” በማለት ሆስፒታሉ ጥሪውን አቅርቧል።
ለስኳር በሽተኞች የሚሰጥ አንዲት የኢንሱሊን መርፌ እንኳን ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደደረሰ በደብዳቤው ያስታወቀው ዓይደር ሆስፒታል ከዚህም ባለፈ የኩላሊት እጥበትም ሆነ በበሽታው የተጎዱ የሰውነት አካላትን ቆርጦ ለማስወገድ እንኳን አስፈላጊ ቁሳቁሶችና የህክምና ግብአቶች ማጣቱን ገልጿል።
እንደ ዓይደር ሆስፒታል መረጃ በትግራይ 26,768 የስኳር ህመምተኞች ያሉ ሲሆን፣ 16,420ዎቹ የType-1 በሽተኞች ሙሉ በሙሉ የኢንሱሊን መድሃኒት ጥገኛ ናቸው። ከነዚህም 8,224 የሚሆኑት እድሜያቸው ከ14 አመት በታች የሆኑ ህፃናት ሲሆኑ 10,348 ሰዎች ደግሞ የType-2 ህመምተኞች ናቸው።
“የስኳር በሽታ ታማሚዎች ከበርካታ የክልሉ አከባቢ ወደሆስፒታሉ እየመጡ ስለሆነ የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በየሳምንቱ 12 የስኳር ህመምተኞች እየሞቱ ሲሆን በየቤቱ ህይወታቸው እያለፈ ስላለ ሰዎች መረጃው ስለሌለን መናገር ያዳግተናል” ሲል የትግራይ የስኳር ታማሚዎች ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ ሆስፒታሉ ገልጿል።
የዓይደር ሆስፒታል የእርዳታ ጥሪውን ያቀረበበትን ደብዳቤ በአባሪነት በተጨማሪ ለአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌደሬሽን፣ ለአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማሕበር እና ለአለም ምግብ ፕሮግራም የተጎጂዎችን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ ቢያቀርብም ጉዳዩን በዋናነት የሚመለከተውን የዓለም ጤና ድርጅት ግን በደብዳቤው ተቀባዮች ዝርዝር ውስጥ አላካተተዉም።
“የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን በስኳር በሽታ ህክምና አቅርቦቶች እጥረት በትግራይ ላጋጠመው አስከፊ የንጹሃን ህይወት እልቂት አፋጣኝ መልስ እንደምትሰጡ እናምናለን። ለዚህ አስቸኳይ ህወትን የማዳን ጥሪም ያለ ምንም መዘግየት ምላሽ እንደምናገኝም እምነት ጥለንባችኋል” በማለት አይደር ሆስፒታል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ሃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ አለም አቀፍ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና ተደራሽነት እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የጤና አጠባበቅ ግብአቶች ላይ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ሁለት ዓመት ሊሞላ ሳምንት ብቻ የቀረው ጦርነት መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ በማድረግ የትግራይ ክልል በዝግ ሁኔታ ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል።
ከአምስት ወራት የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ባለፈው ነሐሴ ወር እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸማጋይነት ይካሄዳል የተባለዉ የሰላም ንግግር ተስፋ ላይ ጥላ አጥልቶበታል።
የአፍሪካ ህብረት ባቀረበው የሰላም ድርድር ጥሪ መሰረት መስከረም 28 ቀን በደቡብ አፍሪካ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው የሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ እንደሆኑ ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች መግለፃቸው ይታወሳል። ሆኖም ከድርድሩ ቀድሞ በወጣው መረጃ በሎጂስቲክስ ክፍተት የድርድሩ መጀመሪያ ቀን መራዘሙ ታውቋል።