በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመከታተል የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች አሁን ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ከህግ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች እና ፆታዊ ጥቃቶች በሁሉም ታጣቂ ኃይሎች መፈፀም ቀጥለዋል አለ።
ከ500 የሚበልጡ የዓይን እማኞች ቃለ መጠይቅ የተደረጉበት ሪፖርት በትላንትናው እለት የቀረበ ሲሆን “የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ህገ መንግስትም ጭምር ግዴታው የሆነውን የዜጎቹን ደህንነትና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ እንደተሳነው” ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ሳቢያ ታኅሣሥ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. የተመሰረተው የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽኑ ለአንደ አመት እንዲቆይና እንደ አስፈላጊነቱ እንዲራዘም ተወስኖ ነበር የተቋቋመው። የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በጀመሩት ጦርነት ምክንያት የተቋቋመው ኮሚሽን ሰብሳቢ ሞሀመድ ቻንዴ እንደገለፁት፤ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ግጭቶችን በዘላቂነት ማስቆምም ሆነ ሰላም መፍጠር አልቻለም ብለው በታጣቂ ኃይሎች የሚፈፀሙ ወንጀሎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዙ ውጊያዎች፣ የፆታ ጥቃቶች፣ የጅምላ እስር እና ግድያ፣ የግዳጅ መፈናቀል እንዲሁም በሰብዓዊነት እና በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ የትምህርት፤ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች መሰረት ልማት መውደም ተባብሶ መቀጠሉን ኮሚሽኑ አሳስቧል።
ካለፈው ወር ጀምሮ ብቻ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ ከሌሎች አካባቢዎች የከፋ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መኖሩን የገለፀ ሲሆን “ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት በፌደራል መንግስቱ ተፈፅሟል” ሲል አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ እንዳሳሰቡትም ታማኝ፣ ሁሉንም አካታች እና ውጤት የሚኖረው የፍትህ ሂደት በኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ አሁን አስፈላጊ ሆኗል። ሰብሳቢው አያይዘውም በኮሚሽኑ ምርመራ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የሽግግር ጊዜ ፍትህ ሂደት በገዢው መንግስት ጫና ስር የወደቀ ነው።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሰብሳቢ የሆኑት ሞሀመድ ቻንዴ እንደገለፁት “በኢትዮጵያ በአስቸኳይ አካታች፣ ታማኝ እና ውጤታማ የፍትህ ሂደት ቢያፈልግም የሀገሪቱ የሽግግር ፍትህ ሂደት ከዚህ የራቀ ነው። የኮሚሽኑ አባላት ያነጋገሯቸው ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ተቋማት የሽግግር ፍትህ የማስፈን አቅምና ፍላጎት ላይ እንደማይተማመኑ ተናግረዋል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል። አሁን በኢትዮጵያ እየተሞከረ ያለው የፍትህ ሂደትም አካታችነት፣ ግልፀኝነት እና በገዢው መንግስት ፍላጎት በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ የሚሰራ መሆኑ እንደክፍተት ተጠቁሟል።
አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ እየተፈፀሙ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የጦር ወንጀሎችን መርምሮ በዓለም አቀፍ ጥራትና መስፈርት ፍትህ ማስፈን አይችልም የተባለ ሲሆን ከዚህ ባለፈ በኮሚሽኑ የሚደረጉ የምርመራ ጥረቶችን “ሆን ብሎ ለማደናቀፍ” መንግስት እንደሚሰራ ኮሚሽኑ ገልጿል።
መንግስት በራሱ ምርመራ የሚደረግበት አካል ሆኖ ሳለ በተለያዩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ፣ ኮማንድ ፖስት እና የተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮችን እየዘረጋ መቀጠሉ ይበልጥ ለመብት ጥሰቶች እንዳያጋልጥም ተሰግቷል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ አባላት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሽግግር ጊዜ ፍትህ ዙሪያ ለማነጋገር ባደረጉት ጥረት ከፌደራል መንግስት ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙም አስታውቀዋል። በመንግስት ጫና እንዲሁም በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ኮሚሽኑ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች እና ጉዳዮች እንደሚኖሩ ያስታወሰው ሪፖርቱ ከሶስት ወራት በኋላ የሚጠናቀቀው የስራ ዘመኑ መራዘም እንዳለበት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
በመጨረሻም የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አሁንም ተስፋፍቶ የቀጠሉ የመብት ጥሰቶችና ከህግ ውጭ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ የጦር ወንጀሎች እንዲሁም የብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ አግላይ ንግግሮች መኖራቸው ችግሮቹ ተባበሰው እንደሚቀጥሉ የሚያመላክቱ ሆነው ተገኝተዋል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተቋቋመው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈፀሙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች የተላለፉ ወንጀሎች እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕጎችን የጣሱ ወንጀሎችን በሁሉም ግጭት ላይ ባሉ ወገኖች በኩል በነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ማካሄድ፣ ተፈፀመዋል የተባሉ ክሶች እና የመብት ጥሰቶችን እውነታ እንዲሁም ሁኔታዎች ላይ ማስረጃን ማሰባሰብ፣ መጠበቅና ከተቻለ ወንጀል ፈፃሚዎችን መለየት፣ በሽግግር ጊዜ ፍትህ ላይ ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ማድረግና ምክረ ሃሳብ ማቅረብ፣ በሂደቱ የፆታ ስብጥር እና ተጎጂዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ከኢትይዮጵያ መንግስት፣ የክልል መንግስታት፣ የኤርትራ መንግስት፣ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት፣ የሚኒስትሮች የጋራ ግብረሃይል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ አፍሪካ ሕብረት፣ የአፍሪካ ህብረት ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽንና መንግስትዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ ከሚመለከታችው ሁሉም አካላት ጋር የመገናኘት ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም. የስልጣን ገደቡ የሚጠናቀቀው ኮሚሽኑ አሁንም ይበልጥ የተጠናከረ እና የተደራጀ ገለልተኛ ምርመራ የፍትህ አለመስፈን በራሱ ይበልጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና የጦር ወንጀሎችን እንዳያበራክት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከመስከረም 2021፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኤግዚኪዩቲቭ ኦርደር 14046 መሰረት በብሄራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ላይ የተደቀነ ስጋትን ለመቋቋም በሚል ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የጣለውን ማዕቀብ ከቀናት በፊት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል።
በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋም በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው ሪፖርት በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች ለጅምላ እስር መዳረጋቸውን ገልፆ የነበረ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ መንግስት የዜጎችን መብት እንዲጥስ እድል የሚሰጥ ነው ሲል አሳስቦ ነበር። ይሁን እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ከህግ ውጭ የሚፈፀሙ ተግባራት እንደሚጣሩ በመግለፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ማድረጉን በተደጋጋሚ እየገለፀ ይገኛል።