ነሐሴ 27 ፣ 2015

በከባድ አውሎ ንፋስ መሃል በሆንግ ኮንግ ያረፈው የኢትዮጵያ አውሮፕላን የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል

City: Addis Ababa

በጠቅላላው ወደ 460 የሚጠጉ በረራዎች በተሰረዙበት እና በአምስት ዓመታት ውስጥ ያልታየ ይሆናል በተባለ አውሎ ንፋስ መሀል ሲያርፍ በዓለም ደረጃ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ተከታትለውታል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በከባድ አውሎ ንፋስ መሃል በሆንግ ኮንግ ያረፈው የኢትዮጵያ አውሮፕላን የዓለም መነጋገሪያ ሆኗል

ወደ ሆንግ ኮንግ በረራ ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት በርካታ በረራዎች በተሰረዙበት ወቅት በአስገራሚ ሁኔታ ማረፉ ተገልጿል።

ትላንት አርብ ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የደረሰ ብቸኛው አውሮፕላን ሆኖ የተመዘገበው ቦይንግ 787 ድሪምላይነር የበረራ ቁጥር ET608 ሆንግ ኦንግ ሲደርስ ከተማዋ በኃይለኛ አውሎ ንፋስ እየተመታች ነበር።

ምሽት ላይ እንዳረፈ የተገለፀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን በሆንግ ኮንግ አውሮላን ማረፊያ ከመድረሱ በፊት የመጨረሻው የመንገደኞች አውሮፕላን ከሶስት ሰዓታት በፊት ማረፉ እና ከዛ በኋላ የአየር ሁኔታው ለእንቅስቃሴ አዳጋች በመሆኑ በረራዎች እንዲሰረዙ ግድ ሆኖ ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአቪዬሽን ዘርፉ መነጋገሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET608 ወደ ሆንግ ኮንግ ያደረገውን ጉዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ6 ሺህ 400 በላይ ሰዎች FlightRadar24 በተሰኘ የበረራ መከታተያ ድረ ገፅ የተመለከቱት ሲሆን ይህም በወቅቱ ከነበሩ በረራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፈተኛ ተከታታይ የነበረው በረራ ለመሆን በቅቷል። 

 

 

በአቪዬሽን ዘርፉ ባለሙያዎች በአንድ በኩል በከባድ የአየር ሁኔታ ውስጥ አደጋ ሳይደርስ አውሮፕላኑ ማረፉ በመልካም ጎን ሲነሳ፤ በሌላ በኩል ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች በተሰረዙበት ወቅት መብረሩን የሚተቹም አልጠፉም።

በአየር ማረፊያው የአየር ሁኔታ መረጃ ስርዓት መሰረት የአውሮፕላን ማረፊያው እርጥበታማ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን በጠቅላላው ወደ 460 የሚጠጉ በረራዎች አርብ ዕለት ተሰርዘዋል ሲል የሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ ባለስልጣን አስታውቋል።

ሆንግ ኮንግ ብሔራዊ አየር መንገዴ ነው የምትለው ካቴይ ፓሲፊክ አየር መንገድ ሁሉንም የሆንግ ኮንግ በረራዎች አርብ ከምሽቱ 2 ሰአት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ 10 ሰአት ድረስ ሰርዟል። በከተማዋ ውስጥ አብዛኛው የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎትም ተቋርጧል።

‘ሳኦላ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋስ 210 ኪ.ሜ በሰዓት የሚነጉድ ንፋስ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን ሆንግ ኮንግ በአምስት ዓመታት ውስጥ ካጋጠሟት አውሎ ንፋስ አደጋዎች ከባዱ እንደሚሆን ከአሁን ትንበያዎች እያሳዩ ነው።

የሆንግ ኮንግ ራስ ገዝ አስተዳደር ለአውሎ ንፋሶች ባስቀመጣቸው አምስት ደረጃዎች 1፣ 3፣ 8፣ 9 እና 10 ተብለው የተከፈሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለው የንፋስ ደረጃ 8 ወይም መካከለኛ ላይ ነው።
 

 



 

 

አስተያየት