ነሐሴ 25 ፣ 2015

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከ360 ሚልየን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ስምምነቶችን አፀደቀ

City: Addis Ababa

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ከብድር ስምምነቶች በተጨማሪ ከሩሲያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ህንድ፣ ፓኪስታን እና ሊባኖስ መንግስታት ጋር የተፈረሙ ስምምነቶችን አፅድቆ በህዝብ ተወካዮች እንዲፀድቁ መርቷል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከ360 ሚልየን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ስምምነቶችን አፀደቀ

የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር እና ከጣልያን መንግስት ጋር በተፈረሙ ከ361 ሚልየን ዶላር በላይ የብድር ስምምነቶች ላይ ተወያይቶ ማፅደቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ ልማት ማህበር ጋር በጥቅሉ 300 ሚልየን ዶላር ብድር ስለሚገኝባቸው ሁለት ስምምነቶች የተወያየ ሲሆን፤ 250 ሚልየን ዶላር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እና በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር የሚገኘው 50 ሚልየን ዶላር ብድር ደግሞ የሰው ሀብት ልማት አገልግሎቶች የሚውል እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስምምነቱ ከወለድ ነፃ መሆኑ፣ 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት መሆኑን እንዲሁም የ6 ዓመታት የችሮታ ጊዜና 38 ዓመታት ለክፍያ መሰጠቱን ተመልክቶ በማፅደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

በተመሳሳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከጣልያን መንግስት ጋር የተፈረመ የ56 ሚልየን ዩሮ (61 ሚልየን ዶላር ገደማ) የብድር ስምምነትን በማፅደቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

ከጣልያን መንግስት የተገኘው ብድር በቡና እሴት ማሻሻያ፣ በገጠር አካባቢዎች የስራ እድል ለመፍጠር፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም በአዋሽ እና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት አስተዳደር ለመዘርጋት እንደሚውል በውሳኔው ተመላክቷል።

ከጣልያን መንግስት የሚገኘው ብድርም ከወለድ ነፃ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የ16 ዓመታት የችሮታ ጊዜ በ30 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆናቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ መሰረት በዚህ በጀት ዓመት ለመንግስት በቀጥታ የሚሰጠውን ብድር ካለፈው ዓመት አንድ ሶስተኛ እንዳያልፍ ወስኖ ነበር። የገንዘብ ሚኒስቴርም ይህን አማራጭ የሚጠቀመው የግምጃ ቤት ሰነድ በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረብ ካልቻለ ብቻ መሆኑም ብሔራዊ ባንኩ ማስታወቁ ይታወሳል።  

ከብድር ስምምነቶቹ ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ከሩሲያ መንግስት ጋር የተፈረመውን የወታደራዊ-ቴክኒካል ስምምነት፣ የአፍሪካ መድኀኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት፣ በሊባኖስ የሚገዡ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ደህንነትና መብት ያስጠብቃል የተባለ ከሊባኖስ መንግስት ጋር የሚፈረም የስራ ስምሪት ስምምነት፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ህንድ መንግስታት ጋር የዲፕሎማት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን የሚያስቀር ስምምነት እና በመጨረሻም ከፓኪስታን መንግስት ጋር የተፈረመ የንግድ ስምምነትን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆ ወደ ፓርላማ ልኳል።
 

አስተያየት