ነሐሴ 24 ፣ 2015

ንግድ በአርምሞ: መስማትና መናገር የተሳነው መፅሐፍ ነጋዴ

City: Addis Ababa

ሶስት መፅሀፎችን ለህትመት ያበቃው የመፅሀፍ ነጋዴ ኑሮውን ለመምራት እና ትምህርቱን ለመከታተል በቂ ገቢ ባጣበት ወቅት ትምህርቱን ለማቋረጥም ተገዶ ነበር።

Avatar: Mikiyas Alemu
ሚኪያስ አለሙ

Mikiyas Alemu is a Journalist and Junior researcher at Addis Zeybe.

ንግድ በአርምሞ: መስማትና መናገር የተሳነው መፅሐፍ ነጋዴ

የሰዎችን የእርስ በእርስ መስተጋብር በሚጠይቅበት፤ ሻጭ ከገዢ ገንዘብን ፣ገዢ ከሻጭ ንብረትን በሚለዋወጡበት በግብይት ሂደት ውስጥ ተነጋግሮ መግባባት ተደማምጦ መስማማት የንግድ ልዩ ባህሪ ነው። የተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ኖሮባቸው በንግድ ዘርፍ ተሰማርተው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥቂት አይባሉም። 

መናገር እና መስማት የተሳነው ሰው ሆኖ፤ ተነጋግሮ የተፈለገውን ለማቅረብ እና በዋጋ ተስማምቶ ስራውን ማቀላጠፍ በሚጠይቀው የንግድ ስራ ላይ ያውም በመፅሀፍት ንግድ መሰማራትን “ይቻላል” የሚል ኢትዮጵያዊ ባለታሪክን በአዲስ አበባ ከተማ አግኝተናል።

ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ነው። ወጣት ታዬ መስማትና መናገር ቢሳነውም ንግድን በአርምሞ እያከናወነ ኑሮውን እየገፋ ይገኛል። ታዬ አለምነው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አሁን ከአዲስ ዘይቤ ጋር የተገናኘበት ሳሪስ በተባለው ሰፈር፤ አደይ አበባ አካባቢ አሮጌ መጻህፍትን ይዞ በመውጣት መሸጥ እንደጀመረ ነግሮናል።

የማንበብ ልምድ እንደነበረው የሚናገረው ታዬ፤ ለማንበብ የሚገዛቸውን መፃህፍት መልሶ በመሸጥ እንዲሁም የሚያውቁት ሰዎች ያነበቡትን መፅሀፍት ሲሰጡት እሱን በመሸጥ በአምስት አሮጌ መፅሀፍት የጀመረውን ስራ ለማስፋት እየጣረ ነው።

እስከ 6ተኛ ክፍል ድረስ መናገር እና መስማት እንደልቡ ይችል የነበረው የዛኔው ታዳጊ ታዬ ጊዜውን ሲያስታውስ፤ “በ1996 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የታይፎድ እና የቢጫ ወባ ህመም ገጥሞኝ ለአራት ቀናት ህክምና ሳላገኝ በመቆየቴ ምክንያት መናገር እና መስማት ተስኖኛል” ይላል። በዚህ ያልተበገረው ታዬ ግን መፅሀፍት ከሚገዙት ደንበኞች ጋር ሃሳባቸውንና ፍላጎታቸውን በወረቀት እየጻፉለት እሱም መልሱን እና ሀሳቡን መልሶ ወረቀት ላይ በመፃፍ ስራውን በአግባቡ ያከናውናል።

 

ይሁን እንጂ የሰዎች ባህሪ የተለያየ በመሆኑ ለግብይት የሚመጡ አንዳንድ ሰዎች ፅፈው ሀሳባቸውን ከገለፁለት በኋላ የእሱን መልስ እስከሚፅፍ እና በዋጋ ለመደራደር በትእግስት መጠበቅ የማይችሉ ሰዎች በስራው ላይ የሚገጥመው ፈተና እንደሆነም ታዬ አለምነው ይናገራል። አልፎ አልፎም ፊደል ያልቆጠሩ ነገር ግን ለልጆቻቸው ወይም ለሌላ ሰው መፅሀፍ ለመግዛት የሚመጡ ሰዎች ጋር በፅሁፍ መግባባት የማችሉበት ሁኔታ እንደሚገጥመውም ወጣቱ ያስረዳል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ደንበኞችን እንዳፈራ የሚገልፀው ታዬ በጤናው ላይ ያጋጠመውን እክል ተከትሎ ትምህርቱን ሊቀጥል ባለመቻሉ ህመሙ ካጋጠመው ከሁለት ዓመት በኋላ በ1998 ዓ.ም የትውልድ ቦታውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ መፅሀፍትን በመሸጥ ስራ ላይ ከተሰማራ 12 ዓመታት ገደማ ተቆጥረዋል።

ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ትምህርቱን ከመቀጠል ጎን ለጎን ኑሮን ለመግፋት በቀጥታ ወደ ጫማ መጥረግ ስራ ገብቶ የነበረው ታዬ፤ መፅሀፍትን ከመሸጥ ባሻገር ማንበብን የዘወትር ስራው አድርጓል። ከመፅሀፍት ፍቅር እስከ መቃብርን፣ ከደራሲያን ደግሞ ሀዲስ ዓለማየሁ እና ዓለማየሁ ዋሴ ምርጫዎቹ እንደሆኑም ይናገራል።

ታዬ ከመርካቶ፣ አራት ኪሎ እና ከሌሎችም ቦታዎች እያመጣ የሚሸጣቸው መፃህፍት ኑሮውን ለመግፋት የገቢ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ የንባብ ባህሉን ለማዳበር ጠቅመውታል። ያነበባቸው መፃህፍት እውቀትን ከማካበት በተጨማሪ የራሱን መፅሀፍት እንዲፅፍ መሰረት ሆነውት በ2005 ዓ.ም የመጀመሪያ ስራውን  'በአባይ ወንዝ እንወቅ' የሚል የግጥም መድብል መፃፍ ችሏል። በ2009 ዓ.ም 'ሁለት እጅ' የተሰኘ መፅሐፍ እና በ2011 ዓ.ም. ደግሞ 'ምሩቁ ተማሪ' የተሰኘውን ስራ በማሳተም እስካሁን ሶስት ስራዎችን ለህትመት አብቅቷል። 


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የባይሎጂ ትምህርትን መከታተል ጀምሮ የነበረው ታዬ፤ ሲተዳደርበት የነበረውን የመፃህፍት ሽያጭ ስራ የሚሰራለት ሰው በማጣቱ ትምህርቱን ከሁለት ወር በላይ መማር አልቻለም ነበር። ወጣቱ ኑሮውን ለመምራት፣ ቤት ተከራይቶ ለመኖር እና ትምህርቱን ለመከታተል በቂ ገቢ ስለሌለው ትምህርቱን አቋርጦ የመፅሀፍ መሸጥ ስራውን በብቸኝት እያከናወነ ለመኖር ተገዷል።

አዲስ ዘይቤ በታዬ ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን ስታነጋግር፤ መፅሀፍቱን ከሌሎች ቦታዎች በንፅፅር በቅናሽ ዋጋ ከማቅረቡ ባለፈ ገንዘብ ሳይኖራቸውና መፅሀፍ ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ሲገጥሙት ሌላ መፅሀፍ አምጥተው በሚፈልጉት ቀይረው እንዲወስዱ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

“የዋህነት፣ ደግነት እና የንባብ ባህል እንዲዳብር መፈለግ” የታዬ መገለጫው ነው የሚሉት በአቅራቢያው የሚሰሩ እና አብረውት የሚውሉ ሰዎች፤ በአቅም ከእርሱ በታች የሆኑትን እና የእለት ጉርስ የማያገኙትን በአገኘው አጋጣሚ ካለው ላይ በማካፈል የሚኖር መሆኑን ይመሰክራሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳተመው 'በአባይ ወንዝ እንወቅ' የግጥም መድብል የጀርባ ገፅ ላይ የወደፊት ዓላማው “በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ሰዎችን መርዳት” እንደሆነ የፃፈው ወጣት ታዬ አለምነው፤ የወደፊት እቅዱ የመፃህፍት መሸጥ ስራውን ማስፋት ነው። 

አሁን ላይ የመናገር አቅሙ መሻሻል ቢያሳይም ከሰዎች ጋር ለመግባባት የሚያስችለው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ታዬ የመስማት ችሎታውን በህክምና ለመመለስ ወደ 500 ሺ ብር ገደማ ተጠይቋል፤ ህክምናውን ቢያገኝ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ እንደሚችል በማመን የመፅሀፍት ንግዱን ከዚህም በላይ አጠናክሮ መስራትን ዓላማው አድርጎ ጥረቱን ቀጥሏል።


 

 

 

 

አስተያየት