ነሐሴ 17 ፣ 2015

ኢትዮጵያ በሳዑዲ-የመን ድንበር ተፈፀመ የተባለውን የዜጎቿን ግድያ አጣራለሁ አለች

City: Addis Ababa

ኢትዮጵያ በሳዑዲ-የመን ድንበር ተፈፀመ የተባለውን የዜጎቿን ግድያ አጣራለሁ ብትልም የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣን ክሱን ማስተባበላቸው ተሰምቷል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ኢትዮጵያ በሳዑዲ-የመን ድንበር ተፈፀመ የተባለውን የዜጎቿን ግድያ አጣራለሁ አለች

የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ እና የመን ድንበር ላይ ተገድለዋል ስለተባሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ምርመራ እንደሚያደርግ ቢያስታውቅም፤ የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት በሌላ በኩል ውንጀላውን አስተባብለዋል።

 

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዋች በሳዑዲ አረቢያ እና በየመን ድንበር ላይ የተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመራ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቆ በሳዑዲ አረቢያ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማዕቀብ እንዲጣል ሲልም ጠይቆ ነበር።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ “ትኩረታችን በሳዑዲ እና በየመን ድንበር ላይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል የተባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ተመልክቶ በቅርቡ በወጣው ሪፖርት ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመሆን ጉዳዩን በአስቸኳይ ያጣራል።” ብሏል።

 

ይሁን እንጂ የፈረንሳዩ የዜና ተቋም አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የሳዑዲ መንግስት ምንጮች የሂዩማን ራይትስ ዎች የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ገድለዋል ሲል ያቀረበውን ውንጀላ ማስተባበላቸውን ዘግቧል።
 

ዘገባውም “የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የመረጃ ምንጭ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፀው ክሱ መሠረተ ቢስ እንጂ በታማኝ ምንጮች ላይ የተመሰረተ አይደለም” ብሏል።    

 

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ የድንበር ጠባቂዎች “በከባድ እና ፈንጂ ምሳሪያዎች” ጭምር የታገዘ ጥቃት ተፈፅሟል ማለቱን የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ማስተባበላቸው ተዘገበ። 
 

ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ባለ73 ገፅ ሪፖርት ከፈረንጆቹ መጋቢት 2022 እስከ ሰኔ 2023 ድረስ ባሉት 15 ወራት ውስጥ ‹‹ቢያንስ በመቶዎች›› የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የየመን-ሳኡዲ አረቢያ ድንበርን ለመሻገር ሲሞክሩ በአካባቢው የድንበር ጠባቂዎች በሚፈፀም ጥቃት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ገልፆ “ከጊዜ ወደ ጊዜ የሟቾች ቁጥር እና የግድያ ስልቶች እየተበራከቱ መጥተዋል” ብሏል።
 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰኞ እለት እንዳስታወቀው ስለእነዚህ ውንጀላዎች ያላቸውን ስጋት ለሳዑዲ አረቢያ መንግስት ማቅረባቸውን ገልጿል። የአሜሪካ መንግስት የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጥልቅ እና ግልፅ የሆነ ምርመራ እንዲያካሄዱ እና በዓለም አቀፍ ህግ ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስቧል። እንድ ሂውማን ራይትስ ዎች መረጃ በአሁኑ ወቅት ወደ 750 ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ኑሮ እና ስራቸውን በሳውዲ አድርገው ይገኛሉ። 


 

አስተያየት