መስከረም 8 ፣ 2016

የመንግስታቱ ድርጅት አባላት ያፀደቁት 'ዘላቂ የልማት ግቦች' ችላ መባላቸው ዋጋ እያስከፈለ ነው ተባለ

City: Addis Ababa

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በፈረንጆቹ 2030 ለማሳካት የተያዘው ግብ አካሄድ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው ግጭቶች፣ ረሀብ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አሁንም ዓለም አቀፍ ስጋት መሆናቸውን አሳስበዋል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት አባላት ያፀደቁት 'ዘላቂ የልማት ግቦች' ችላ መባላቸው ዋጋ እያስከፈለ ነው ተባለ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በ'ዘላቂ የልማት ግቦች'  ከተያዙ እቅዶች እስካሁን 15 በመቶ የሚሆነው ብቻ መሳካቱን ገልፀው ግጭቶች፣ ረሀብ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች አሁንም ችላ መባላቸውን አሳሰቡ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ከስምንት ዓመታት በፊት ያፀደቀውን ዓለም አቀፍ 'ዘላቂ የልማት ግቦች' የተመለከተው 75ተኛው የህብረቱ ጉባዔ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የተመድ አባል ሀገራት የዘላቂ ልማት ግቦችን (SDGs) በ2030 ለማሳካት ወጥነው ነበር። 17 ዋና ዋና ግቦችን የያዘው እቅድ ድህነትን፣ የአመጽ ግጭቶችን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና የአካባቢ መራቆትን መንስኤዎችን ለመፍታት ውጤታማ መንገድ ናቸው የተባሉ ምክረ ሀሳቦችን የያዘ ነው።

ዘላቂ የልማት ግቦች የሚባሉት 17 እቅዶች በቀዳሚነት ድህነትን እና ረሃብን ማጥፋት ሲሆን ጠንካራ የጤና እና ደህንነት አገልግሎት፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ የፆታ እኩልነት፣ የንፁህ ውሃና ንፅህና ጥበቃ፣ በዋጋ ተመጣጣኝና አየር የማይበክል ታዳሽ ኃይል አጠቃቀም፣ በቂ የስራ እድል እና የኢኮኖሚ እድገት፣ ኢንዱስትሪ፤ ፈጠራና መሰረተ ልማት፣ ሁለገብ እኩልነት፣ የማያቋርጥ የከተማ እና ማህበረሰብ እድገት፣ ምርቶችን ማምረትና መጠቀም ላይ ኃላፊነት መፍጠር፣ የአየር ንብረት ጥበቃ፣ በውሃ ውስጥ ያሉ ህይወቶችን መጠበቅ፣ የመሬት ሀብትን መጠበቅ፣ ሰላም፤ ፍትህ እና ጠንካራ ተቋማት እንዲሁም እነዚህን ግቦች ለማሳካት መተባበር ናቸው።   

አንቶኒዮ ጉተሬስ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር “ከስምንት ዓመታት በፊት አባል ሀገራት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማፅደቅ በዚህ አዳራሽ የተሰበሰቡት ለዓለም ማህበረሰብ በሙሉ ጤና፣ እድገት እና ዕድል የሞላበት ዓለምን ለመገንባት፣ ማንንም ወደኋላ ላለመተው እና ይህን ለማሳካትም የሚከፈለውን ለመክፈል ቃል ኪዳን ተገብቶ ነበር” ሲሉ አስታውሰዋል።

የተገባው ቃል ኪዳን በሀገራት መሪዎች ፈቃደኛነት እርስ በእርሳቸው የተጋቡት ሳይሆን ለሰው ልጆች በሙሉ የተገባ ቃል ነው ሲሉም አሳሳቢነቱን አፅንዖት የሰጡት ዋና ፀሐፊው፤ ሀብት በተትረፈረፈበት ዓለም ሰዎች እየተራቡ መሆኑን፣ በድህነት መኮራመታቸውን፣ በግጭቶች፣ በረሃብ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ልጆች ትምህርት መማር እንዳልቻሉ እንዲሁም በበርካታ ምክንያቶች የሚፈናቀሉ ህዝቦች መብዛታቸው ትኩረት እንደሚገባው ተናግረዋል።

እነዚህ እቅዶች መላው ዓለም ያሉ ሰዎችን ተስፋ፣ ህልሞች እና መብቶች የተሸከሙ ናቸው ያሉት አንቶኒዮ ጉተሬስ አሁን 75ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌም የሚያስገድዳቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ከዘላቂ የልማት ግቦች እቅድ እስካሁን 15 ከመቶ የሚሆኑት ኢላማዎች ብቻ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን እቅዶቹን ለማሳካት ከሰባት ዓመታት ያነሰ ጊዜም ይቀራል። ይሁን እንጂ እንደ ተመድ ዋና ፀሐፊ ገለፃ ከእቅዱ 15 በመቶ ውጭ ያሉት “በተቃራኒ እየተጓዙ ነው”። ዋና ፀሐፊውም “ማንንም ወደ ኋላ ላለመተው ከተገባው ቃል ኪዳን ይልቅ፤ ራሱ ቃል ኪዳኑ እየተተው መሆኑን” ስጋታቸውን ገልፀው ዘላቂ የልማት ግቦቹ ዓለም አቀፍ “የማዳን ዕቅድ” ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ለእቅዶቹ መሳካት በተለይም ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን ቢያንስ በዓመት 500 ቢሊዮን ዶላር ለዘላቂ የልማት ግቦች ማነቃቂያ የሚውል ድጋፍ ያስፈልጋል። በመሆኑም ታዳጊ ሀገራት የእዳ ስረዛ፣ ረጅም የብድር ውሎችን እና ዝቅተኛ የወለድ ተመኖች እንዲደረግላቸው ነው ዋና ፀሐፊው የህብረቱን አባላት የጠየቁት።

በአሁኑ ወቅት ያለውን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስሪት “ጊዜ ያለፈበት፣ በሚገባ ያልተዋቀረ እና ፍትሃዊ ያልሆነ” ሲሉ የገለፁት አንቶኒዮ ጉተሬስ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አወቃቀር መሻሻል ለዘላቂ የልማት ግቦቹ መሳካት ቁልፍ ነው ብለዋል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በንግግራቸው መጭረሻ በሰጡት ምክረ ሀሳብ ህብረቱ በረሃብ ላይ ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድ፣ ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገው ሽግግር ለማፋጠን፣ የዲጂታል ዓለም ጥቅሞች እና እድሎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ፣ የትምህርት ስርጭት እና ጥራትን ለማሳደግ፣ ጥሩ የስራ እድል እና ማህበራዊ ዋስትና በየሀገራቱ ለማስፈን እንዲሁም ሰዎች በተፈጥሮ ላይ የከፈቱትን ጦርነት በማቆም እንክብካቤ ትኩረት እንዲያገኝ ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
 


 

አስተያየት